9

1 ዳዊትም፣ “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳዖል ቤት የቀረ ሰው ይኖር ይሆን?” በማለት ጠየቀ፡፡ 2 በሳኦል ቤተሰብ ውስጥ ሲባ የሚባል አንድ አገልጋይ ነበረ፤ እነርሱም ወደ ዳዊት እንዲሄድ ነገሩት፡፡ ንጉሡም፣ “አንተ ሲባ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ሲባም፣ “አዎን፣ እኔ አገልጋይህ ነኝ” ብሎ መለሰ፡፡ 3 ንጉሡም፣ “የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው የለምን?” በማለት ጠየቀው፡፡ ሲባም ለንጉሡ፣ “ዮናታን እግሩ ሽባ የሆነ አንድ ልጅ አለው” ብሎ መለሰ፡፡ 4 ንጉሡም፣ “ወዴት ነው ያለው?” አለው፡፡ ሲባም ለንጉሡ፣ “ሎዶባር በተባለ ስፍራ በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ብሎ መለሰለት፡፡ 5 በዚህን ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ሎደባር ወደሚገኘው ወደ ዓሚኤል ልኮ ከማኪር ቤት ሜምፊቦስቴን አስመጣው፡፡ 6 የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት መጥቶ ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት ለዳዊት አክብሮቱን ገለጠ፡፡ ዳዊትም፣ “ሜምፊቦስቴ” ብሎ ጠራው፡፡ እርሱም፣ “እነሆ፣ አገልጋይህ” አለ፡፡ 7 ዳዊትም፣ “አትፍራ፤ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል በእርግጥ ቸርነት አደርግልሃለሁና፡፡ የአያትህንም የሳኦልን ምድር በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም ከገበታዬ ትበላለህ፡፡” አለው፡፡ 8 ሜምፊቦስቴም ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፣ “እንደ ሞተ ውሻ የሆንኩትን እኔ አገልጋይህን በሞገስ ትመለከተኝ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?” 9 ከዚያም ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ሲባን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “የሳኦልና የቤተሰቡ የሆነውን ሁሉ ለጌታህ ልጅ ሰጥቼዋለሁ፡፡ 10 አንተ፤ ልጆችህና አገልጋዮችህ የጌታችሁ የልጅ ልጅ የሚበላውን እንዲያገኝ መሬቱን እረሱለት፣ ምርቱንም አግቡለት፡፡ የጌታህ የልጅ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ምን ጊዜም ከገበታዬ ይበላል፡፡” በዚያን ጊዜ ሲባ ዐሥራ አምስት ልጆችና ሃያ አገልጋዮች ነበሩት፡፡ 11 ከዚያም ሲባ ንጉሡን፣ “ጌታዬ ንጉሥ፣ አገልጋዩን ያዘዘውን ሁሉ፣ አገልጋይህ ይፈጽመዋል” አለው፡፡ ንጉሡም በተጨማሪ፣ “ሜምፊቦስቴ በበኩሉ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከገበታዬ የሚበላ ይሆናል” አለ፡፡ 12 ሜምፊቦስቴ ሚካ የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ ነበረው፤ የሲባ ቤተሰቦች በሙሉ የሜምፊቦስቴ አገልጋዮች ነበሩ፡፡ 13 ስለዚህ ሜምፊቦስቴ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነበር፣ ሁለት እግሮቹም ሽባ ቢሆኑም ሁልጊዜ ከንጉሡ ገበታ ይበላ ነበር፡፡