8

1 ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው ድልም አደረጋቸው፡፡ ስለዚህ ዳዊት ጋትና መንደሮችዋን ከፍልስጥኤማውያን ቁጥጥር ነጻ አወጣት፡፡ 2 ከዚያ በኋላም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረገ፤ በመሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው፤ በገመድ ከተለኩትም ሁለት እጅ ሲገድል፣ አንድ እጅ ግን በሕይወት ይተው ነበር፡፡ ስለዚህ ሞዓባውያን የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ፣ ግብርም ገበሩለት፡፡ 3 ከዚህ በኋላ ደዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛቱን ለማስመለስ ይጓዝ በነበረበት ጊዜ የሱባን ንጉሥ የረአብን ልጅ አድርአዛርን ድል አደረገው፡፡ 4 ዳዊትም ከእርሱ ላይ 1700 ሠረገሎችና 20,000 እግረኞች ማረከ፡፡ ለመቶ ሠረገሎች የሚሆኑትን አስቀርቶ ዳዊት የሠረገሎቹን ፈረሶች ሁሉ ቋንጃዎች ቆረጠ፡፡ 5 ከደማስቆ አራማውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ሃያ ሁለት ሺህ አራማውያን ሰዎችን ገደለ፡፡ 6 ከዚያም የደማስቆ ክፍል በሆነው በአራም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ አራማውያንም ለእርሱ አገልጋዮች ሆነው ተገዙለት፣ ግብርም ገበሩለት፡፡ ዳዊት በሄደበት ሁሉ እግዚአብሔር ድልን ሰጠው፡፡ 7 የአድርአዛር አገልጋዮች ይዘዋቸው የነበሩትን የወርቅ ጋሻዎች ዳዊት ወሰዳቸው ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣቸው፡፡ 8 ቤጣህና ቤሮታይ ከተባሉ ከአድርአዛር ከተሞችም ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፡፡ 9 የሐማት ንጉሥ ቶዑ ዳዊት መላውን የአድርአዛርን ሠራዊት ድል ማድረጉን በሰማ ጊዜ፣ 10 ዳዊት ከአድርአዛር ጋር ስለ ተዋጋና ድል ስላደረገው ደግሞም አድርአዛር ከቶዑ ጋር ተዋግቶ ስለ ነበረ፣ ቶዑ ልጁን ዮራምን ሰላምታ ይሰጠው ዘንድና ይባርከው ዘንድ ወደ ዳዊት ላከው፡፡ ዮራምም ከእርሱ ጋር የብር፣ የወርቅና የናስ ዕቃዎች ይዞ መጣ፡፡ 11 12 ንጉሥ ዳዊትም ድል ካደረጋቸው መንግሥታት ሁሉ ማለትም ከአራም፣ ከሞዓብ፣ የአሞን ሕዝብ፣ ከፍልስጥኤማውያን ከአማሌቅ እንዲሁም ከሱባ ንጉሥ ከረአብ ልጅ ከአድርአዛር ከበዘበዛቸው ዕቃዎችና ካገኛቸው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ለእግዚአብሔር ቀደሰ፡፡ 13 ዳዊት የጨው ሸለቆ በተባለው ስፍራ ከአሥራ ስምንት ሺህ ሰዎቻቸው ጋር የነበሩትን አራማውያንን ድል አድርጎ ከተመለሰ በኋላ ስሙ ገነነ፡፡ 14 በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ኤዶማውያን ሁሉ የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ስፈራ ሁሉ ድልን ሰጠው፡፡ 15 ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሕዝቡንም ሁሉ በፍትሐዊነትና በጽድቅ አስተዳደረ፡፡ 16 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሠራዊቱ አለቃ ሲሆን፣ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥም ታሪክ ጸሐፊ ነበረ፡፡ 17 የአኪጦብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቢሜሌክ ካህናት ሲሆኑ፣ ሠራያ ጸሐፊ ነበር፡፡ 18 የዮዳሔ ልጅ በናያስ የከሊታውያንና የፈሊታውያን አለቃ ሲሆን፣ የዳዊት ወንዶች ልጆች ደግሞ የንጉሡ ተቀዳሚ አማካሪዎች ነበሩ፡፡