7

1 ንጉሡ በቤቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣ 2 ለነቢዩ ለናታን ንጉሡ እንደዚህ አለው፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው፡፡ 3 ከዚያ በኋላ ናታን ለንጉሡ፣ “እግዚአብሔር ካንተ ጋር ስለሆነ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው፡፡ 4 ነገር ግን በዚያች ሌሊት እንደዚህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ፣ 5 “ሂድና ለባሪያዬ ለዳዊት እንደዚህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር የሚልህ እንደዚህ ነው፣ የምኖርበትን ቤት አንተ ትሠራልኛለህን? 6 የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ካወጣሁበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳን ማደሪያ ውስጥ ሆኜ እንቀሳቀስ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ ኖሬ አላውቅምና፤ 7 በመላው የእስራኤል ሕዝብ መካከል በተመላለስሁባቸው በሁሉም ስፈራዎች ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ከሾምኋቸው መሪዎች ለአንዱ ስንኳ፣ ‘ከዝግባ እንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?’ ብያለሁን? 8 እንግዲህ አሁን ለባሪያዬ ለዳዊት እንደዚህ በለው፣ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህንን ነው፣ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ ከመስክ በጎችን ትከተል ከነበርህበት ስፍራ ወሰድሁህ፤ 9 በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ’፤ በምድር ላይ ስማቸው ታላቅ እንደሆነው እንደ አንዱ ለአንተ ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ፡፡ 10 ከእንግዲህ ወዲያ በራሳቸው መኖሪያ እንዲኖሩ እንጂ እንዳይናወጡ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፣ በዚያም እተክላቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በፊት እንደሆነውም ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቁናቸውም፤ 11 መሳፍንትን በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ባዘዝሁበት ጊዜ እንዳደረጉባቸው ከእንግዲህ ወዲህ አያደርጉባቸውም፤ ከጠላቶችህም ሁሉ አሳርፍሃለሁ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ እኔ እግዚአብሔር ቤት እንደምሠራልህ እነግርሃለሁ፡፡ 12 ዕድሜህ በሚጠናቀቅበት ጊዜና ከአባቶችህ ጋር በምታርፍበት ጊዜ ከአብራክህ የሚወጣ ዝርያ አስነሳልሃለሁ፣ መንግሥቱንም አጸናለሁ፡፡ 13 እርሱ ለእኔ ቤት ይሠራልኛል፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ፡፡ 14 እኔ አባት እሆነዋለሁ፣ እርሱም ልጄ ይሆናል፡፡ ኃጢአት በሚያደርግበት ጊዜ በሰዎች በትር እቀጣዋለሁ፣ የሰው ልጆች በሚገረፉበትም ግርፋት እገርፈዋለሁ፤ 15 ከፊትህ ካስወገድሁት ከሳኦል ላይ እንደወሰድሁ ኪዳናዊ ታማኝነቴ ከእርሱ አይርቅም፡፡ 16 ቤትህና መንግሥትህ በፊትህ ለዘላለም የጸና ይሆናል፤ ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል፡፡” 17 ናታን ለዳዊት እንደዚህ ተናገረ፣ ይህንንም ሁሉ ነገር ነገረው፤ ጠቅላላውንም ራእይ ገለጸለት፡፡ 18 ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባና በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጠና እንደዚህ አለ፣ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፣ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ደረጃስ ታደርሰኝ ዘንድ ቤተሰቤስ ምንድን ነው? 19 ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህ በፊትህ ታናሽ ነገር ነው፡፡ ስለ ባሪያህ ቤተሰብ እንኳን ለረጅም ጊዜ የሚሆነውን ተናገርህ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ከዚህ በኋላ የሚኖረውንም ትውልዴን አሳየኸኝ! 20 እኔ ዳዊት ከዚህ በላይ ለአንተ ምን እላለሁ? ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ባሪያህን አክብረኸዋል፡፡ 21 ስለ ቃልህ ብለህ፣ ዓላማህንም ትፈጽም ዘንድ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ለባሪያህም ገልጸህለታል፡፡ 22 ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ታላቅ ነህና እንደ አንተ ያለም የለም፤ በገዛ ጆሮቻችንም እንደ ሰማን ከአንተም በቀር አምላክ የለም፡፡ 23 አንተ እግዚአብሔር መጥተህ ለራስህ እንዳዳንከው በምድር ላይ እንዳለው እንደ ሕዝብህ ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? ይህንን ያደረግኸው ለራስህ ሕዝብን ታስነሳ ዘንድ፣ ለራስህም ስምህን ታስጠራ ዘንድና ታላቅና አስፈሪ ነገር በምድርህ ታደርግ ዘንድ ነው፡፡ ከግብፅ ከዋጀኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብንና ጣዖቶቻቸውን አባረርህ፡፡ 24 እስራኤልን ሕዝብህ አድርገህ ለዘላለም አጸናህ፣ አንተም፣ እግዚአብሔር ሆይ አምላክ ሆንህላቸው፡፡ 25 አሁንም ባሪያህንና ቤተሰቡን በሚመለከት የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም አጽናለት፤ እንደተናገርኸውም አድርግለት፡፡ 26 የእኔ፣ የባሪያህ የዳዊት ቤት በፊትህ በሚጸናበት ጊዜ ሕዝቦች፣ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው’ ይሉ ዘንድ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሁን፡፡ 27 አንተ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የእስራኤል አምላክ ለባሪያህ ቤት እንደምትሠራለት ገልጸህለታልና፤ ለዚህ ነው እኔ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት ያገኘሁት፡፡ 28 አሁን፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ አምላክ ነህ፣ ቃሎችህም የታመኑ ናቸው፤ ይህንን መልካም የተስፋ ቃል ለባሪያህ ገብተህለታል፡፡ 29 በፊትህ ለዘላለም የሚቀጥል ይሆን ዘንድ፣ እንግዲህ አሁን የባሪያህን ቤት መባረክ አንተን ደስ ያሰኝህ፡፡ አንተ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ተናግረሃልና በበረከትህ የባሪያህ ቤት ለዘላለም የተባረከ ይሆናል፡፡”