1 ዳዊት እንደ ገና ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች ሰበሰበ፡፡ 2 ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች ሁሉ በኪሩቤል ላይ በዙፋኑ በተቀመጠው በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ለማምጣት በይሁዳ ወዳለው ወደ በአል ሄዱ፡፡ 3 የእግዚአብሔርን ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው በኮረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፡፡ ልጆቹ ዖዛና አሒዩ አዲሱን ሠረገላ ይመሩ ነበር፡፡ 4 የእግዚአብሔርን ታቦት በላዩ ላይ አኑረው ሠረገላውን በኮረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ አሒዩ ከታቦቱ ፊት ለፊት ይሄድ ነበር፡፡ 5 ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በጥድ እንጨት በተሠሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ማለትም በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጸናጽልና በቃጭል መጫወትና ደስታቸውን መግለጽ ጀመሩ፡፡ 6 ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለተደናቀፉ፤ ዖዛ የእግዚአብሔርን ታቦት ለመያዝ እጁን ዘረጋ በእጁም ያዘው፡፡ 7 ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ በዚያም ስፈራ እግዚአብሔር ስለ ኃጢአቱ መታው፡፡ ዖዛም በዚያ በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ ሞተ፡፡ 8 እግዚአብሔር ዖዛን ስለመታው ዳዊት ተቆጣ፤ የዚያን ቦታም ስም ፔሬዝ ዖዛ ብሎ ጠራው፡፡ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፔሬዝ ዖዛ ተብሎ ይጠራል፡፡ 9 ዳዊት በዚያን ቀን እግዚአብሔርን ስለ ፈራ፣ “የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ሊመጣ ይችላል?” ብሎ ጠየቀ፡፡ 10 ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከእርሱ ጋር ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈቀደም፤ በዚህ ፋንታ አቅጣጫ ለውጦ የጌት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው፡፡ 11 የእግዚአብሔርም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እርሱንና ቤተሰቡንም ሁሉ እግዚአብሔር ባረካቸው፡፡ 12 በዚህ ጊዜ፣ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የአቢዳራን ቤተሰብና ያለውን ሁሉ እግዚአብሔር ባረከለት” ብለው ለዳዊት ነገሩት፡፡ ስለዚህ ዳዊት ወደዚያ ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከኦቤድ ኤዶም ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣው፡፡ 13 የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ስድስት እርምጃ በሄዱ ቁጥር አንድ በሬና አንድ የሰባ ጥጃ ይሠዋ ነበር፡፡ 14 ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ብቻ በወገቡ ታጥቆ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽብ ነበር፡፡ 15 ስለዚህ ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት እልል እያሉና ቀንደ መለከት እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘውት መጡ፡፡ 16 የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ እየገባ ሳለ የሳዖል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሥ ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልና ሲጨፍር አየችው፤ ከዚያ በኋላም በልቧ ናቀችው፡፡ 17 ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን በተዘጋጀለት በማዕከላዊ ስፍራ አኖሩት፡፡ ከዚያ በኋላም ዳዊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ፡፡ 18 ዳዊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ በፈጸመ ጊዜ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም ባረከ፡፡ 19 ከዚያ በኋላ ለመላው እስራኤል፣ ለሕዝቡ ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እንጀራ፣ አንዳንድ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ፡፡ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ ወደየቤቱ ሄደ፡፡ 20 ከዚያ በኋላ ቤተሰቡን ለመባረክ ተመለሰ፡፡ የሳዖል ልጅ ሜልኮልም ዳዊትን ልትቀበለው መጣችና እንደዚህ አለች፣ “ራሳቸውን ከሚያራቁቱ ባለጌዎች እንደ አንዱ ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ መካከል በነበሩት ገረዶች ፊት ራሱን በማራቆቱ ምን ያህል የተከበረ ነበር!” 21 ዳዊትም ለሜልኮል እንዲህ ሲል መለሰላት፣ “እኔን ከአባትሽና ከቤተሰቡ ሁሉ በላይ በመረጠኝና በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ መሪ አድርጎ በሾመኝ በእግዚአብሔር ፊት ያንን አድርጌአለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሐሴት አደርጋለሁ! 22 እንዲያውም ከዚህም የበለጠ ራሴን ዝቅ አደርጋለሁ፣ ከዚህም የባሰ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ ነገር ግን በጠቀስሻቸው ገረዶች ፊት እከብራለሁ፡፡” 23 ስለዚህም የሳኦል ልጅ ሜልኮል እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር፡፡