5

1 የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፣ “እነሆ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቁራጭ ነን፤ 2 ሳኦል በእኛ ላይ ነግሦ በነበረበት ባለፈው ጊዜ የእስራኤልን ሠራዊት የምትመራ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፣ በእስራኤልም ላይ ገዥ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር፡፡” 3 ስለዚህም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም ኬብሮን ላይ በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት፡፡ 4 ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረr፤ አርባ ዓመትም ገዛ፡፡ 5 በኬብሮን በይሁዳ ላይ ለሰባት ዓመት ከስድስት ወር፣ ኢየሩሳሌም ሆኖም በመላው እስራኤልና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ፡፡ 6 ንጉሡና ሰዎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች በሆኑት በኢያቡሳውያን ላይ ለመዝመት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፡፡ እነርሱም ለዳዊት፣ “በዕውሮችና በአንካሶች ልትመለስ ካልሆነ በስተቀር አንተ ወደዚህ አትገባም፤ ዳዊት እዚህ መምጣት አይችልም” አሉት፡፡ 7 ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን አምባ ያዘ፤ ይህችም አሁን የዳዊት ከተማ የሆነችው ነች፡፡ 8 በዚያን ጊዜ ዳዊት እንደዚህ አለ፣ “ኢያቡሳውያንን የሚያጠቃ በውሃ መተላለፊያው ሽቅብ መውጣት አለበት፤ በዚያም ዳዊትን የሚጠሉትን ዕውሮችንና አንካሶችን ያገኛል፡፡” እንግዲህ ሰዎች፣ “አንካሶችና ዕውሮች ወደ ቤተ መንግሥት መግባት አይችሉም” ያሉት ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ 9 በመሆኑም ዳዊት በአምባይቱ ኖረ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት፡፡ ከሸንተረሩ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ምሽግ ገነባባት፡፡ 10 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ፣ ዳዊት እጅግ እየበረታ ሄደ፡፡ 11 በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም መልእክተኞችን፣ የዝግባ እንጨት፣ አናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን ወደ ዳዊት ላከ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤት ሠሩለት፡፡ 12 እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ሲል መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገለት ዳዊት አወቀ፡፡ 13 ኬብሮንን ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ በኋላ ዳዊት በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ቁባቶችን አስቀመጠ ሚስቶችንም አገባ፤ ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም በኢየሩሳሌም ተወለዱለት፡፡ 14 በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ስም፣ ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ 15 ኢያቤሔር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ናፍያ፣ 16 ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባሉ ነበር፡፡ 17 ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ለመፈለግ በሙሉ ኃይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ግን ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ፡፡ 18 በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ፡፡ 19 ዳዊትም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ ሲል ዕርዳታ ጠየቀ፣ “ፍልስጥኤማውያንን ወጥቼ ልውጋቸውን? በእነርሱስ ላይ ድል ትሰጠኛለህ?” እግዚአብሔርም ለዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ በእርግጥ ድል እሰጥሃለሁና ውጋቸው” አለው፡፡ 20 ስለዚህ ዳዊት በበአልፐራሲም ወጋቸው በዚያም ድል አደረጋቸው፡፡ እርሱም፣ “የጎርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” በማለት ስሜቱን ገለጸ፡፡ ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም በአልፐራሲም ተባለ፡፡ 21 ፍልስጥኤማውያን ጣዖቶቻቸውን እዚያ ትተው ስለነበር ዳዊትንና ሰዎቹን ወሰዷቸው፡፡ 22 ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ በድጋሚ ተበታትነው ሰፈሩ፡፡ 23 ስለዚህ ዳዊት እንደገና ከእግዚአብሔር ዕርዳታ ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “በፊት ለፊት በኩል አትውጋቸው፤ ይልቁኑ በስተኋላቸው በኩል በመክበብ በበለሳኑ ዛፎች ፊት ለፊት ግጠማቸው፡፡ 24 በበለሳኑ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጉዞ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ለመምታት እግዚአብሔር ቀድሞ ወጥቶአልና በዚያን ጊዜ በኃይል አጥቃ” አለው፡፡ 25 ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ፍልስጥኤማውያንን ከገባዖን እስከ ጌዘር ድረስ ገደላቸው፡፡