1 አበኔር በኬብሮን መሞቱን የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በሰማ ጊዜ እጆቹ ዛሉ፣ መላው እስራኤልም ተጨነቀ፡፡ 2 በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ የወታደር ጭፍራ መሪዎች የነበሩ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ የአንደኛው ስም በዓና ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሬካብ ይባሉ ነበር፡፡ እነርሱም ከብንያም ነገድ የብኤሮት ተወላጅ የሆነው የሬሞን ልጆች ነበሩ (ብኤሮት ከብንያም ክፍል እንደ አንዱ ትቆጠር ነበር፤ 3 የብኤሮት ሕዝብ ወደ ጌቴም በመሸሽ እስከ ዛሬ በዚያ ይኖራሉ)፡፡ 4 የሳኦል ልጅ ዮናታን ሁለት እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው፡፡ እርሱም የሳዖልና የዮናታን ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ሞግዚቱ ይዛው ለመሸሽ አነሣችው፣ ነገር ግን ይዛው በምትሮጥበት ጊዜ የዮናታን ልጅ ወደቀና ሽባ ሆነ፡፡ ስሙም ሜምፊቦስቴ ይባል ነበር፡፡ 5 በዚህ ጊዜ የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ሞቃት በነበረበት በቀትሩ ሰዓት እርሱ ዕረፍት እያደረገ ሳለ ወደ ኢያቡስቴ ቤት ሄዱ፡፡ 6 ትጠብቅ የነበረችው ሴት ስንዴ በምታበጥርበት ጊዜ እንቅልፍ ወስዷት ነበርና ሬካብና በዓና በቀስታ አልፈዋት ገቡ፡፡ 7 ስለዚህ ወደ ቤት ከገቡ በኋላ በክፍሉ ተኝቶ ሳለ አጠቁት ገደሉትም፡፡ ከዚያ በኋላ ራሱን ቆርጠው በመውሰድ ሌሊቱን ሁሉ በዓረባ መንገድ ተጓዙ፡፡ 8 የኢያቡስቴንም ራስ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት ዘንድ አምጥተው፣ “አንተን ሊገድል ይፈልግ የነበረው የጠላትህ የሳዖል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ፤ እነሆ እግዚአብሔር በዛሬው ቀን ስለ ጌታዬ ስለ ንጉሡ ሳዖልንና ዘሩን ተበቅሎአል፡፡” አሉት፡፡ 9 ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞን ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና ምላሽ በመስጠት እንዲህ አላቸው፣ “ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን፣ 10 የምሥራች ያመጣልኝ መስሎት ‘እነሆ ሳኦል ሞተ’ ብሎ የነገረኝን ሰው ይዤ ጺቅላግ ላይ ገደልሁት፤ እንግዲህ ወሬውን ላመጣው ለዚያ ሰው የሸለምሁት ይህንን ነበር፡፡ 11 ታዲያ በገዛ ዐልጋው ላይ ዐርፎ የተኛውን ንጹሕ ሰው ክፉ ሰዎች የገደሉት ከሆነ እንዴት ይልቅ ደሙን ከእጃችሁ አልፈልግ፣ ከዚህ ምድርስ አልደመስሳችሁ?” 12 ስለዚህም ዳዊት ጎልማሶቹን አዘዘ፤ እነርሱም ገደሏቸው፤ እጅና እግራቸውንም ቆርጠው በኬብሮን ካለው ኩሬ አጠገብ ሰቀሏቸው፡፡ ነገር ግን የኢያቡስቴን ራስ ወስደው ኬብሮን በሚገኘው በአብኔር መቃብር ውስጥ ቀበሩት፡፡