1 በሳዖል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ ጦርነት ነበረ፡፡ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ የሳዖል ቤት ግን እየደከመ ሄደ፡፡ 2 በኬብሮን ለዳዊት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፡፡ የበኩር ልጁ፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን ነበር፡፡ 3 ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ ነበር፡፡ ሦስተኛ የነበረው፣ አቤሴሎም የጌሹር ንጉሥ ከነበረው ከተልማይ ልጅ ከመዓካ የተወለደው ነበር፡፡ 4 አራተኛው፣ ልጁ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፣ አምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣ 5 ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትርኃም ነበር፤ እነዚህ ወንዶች ልጆች ለዳዊት በኬብሮን የተወለዱለት ነበሩ፡፡ 6 የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ አበኔር በሳዖል ቤት ራሱን ጠንካራ አድርጎ ነበር፡፡ 7 ሳኦል የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ የተባለች ቁባት ነበረችው፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፣ “ለምንድን ነው ከአባቴ ቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው፡፡ 8 አብኔርም በዚያን ጊዜ በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ስለተቆጣ እንዲህ አለ፣ “እኔ ለይሁዳ የተሰጠሁ የውሻ ራስ ነኝን? አንተን ለዳዊት አሳልፌ ባለመስጠቴ እኔ ዛሬ ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹና ለወዳጆቹ ታማኝነቴን አሳይቻለሁ፤ ይህም ሆኖ ሳለ አንተ ከዚህች ሴት ጋር በፈጸምሁት ነገር ትከሰኛለህን? 9 እግዚአብሔር ለዳዊት መንግሥትን ከሳዖል ቤት አውጥቶ 10 ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ዙፋኑን እንደሚያጸና በመሐላ የገባለት ተስፋ እንዲፈጸም ባለደርግ እግዚአብሔር በእኔ በአበኔር ላይ ክፉ ያድርግብኝ ከዚያ የባሰም ያምጣብኝ፡፡” 11 ኢያቡስቴም አበኔርን ፈርቶት ስለነበረ አንዲት ቃል ስንኳ ሊመልስለት አልቻለም፡፡ 12 ከዚያም አበኔር ለዳዊት፣ “ይህች ምድር የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፣ እነሆ፣ እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ እንዲመለሱ ለማድረግ እጄ ከአንተ ጋር እንደሆነ ትመለከታለህ” ብለው እንዲነግሩለት መልእክተኞችን ላከ፡፡ 13 ዳዊትም፣ “መልካም ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ነገር ግን ከአንተ የምሻው አንድ ነገር፤ ወደ እኔ በምትመጣበት ጊዜ የሳዖልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ ካልመጣህ ፊቴን ማየት እንደማትችል እንድታውቅ ነው፡፡” አለው፡፡ 14 ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልእክተኞች ላከበት፡፡ 15 ስለዚህም ኢያቡስቴ መልእክተኛ ልኮ፣ ሜልኮልን ከባሏ ከሌሳ ልጅ ከፍልጢኤል ወሰዳት፡፡ 16 ባሏም እስከ ብራቂም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፣ “አሁን፣ ወደ ቤትህ ተመለስ” አለው፡፡ ስለዚህም ተመለሰ፡፡ 17 አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር እንደዚህ በማለት ተመካከረ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊትን በላያችሁ ለማንገሥ ሞክራችሁ ነበር፤ 18 እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ስለተናገረው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት፡፡” 19 አበኔርም ራሱ ሄዶ ለብንያማውያን ይህንን ነገራቸው፤ ከዚያም በኋላ አበኔር እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለገውን ሁሉ በመግለጽ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ፡፡ 20 ከሃያ ሰዎች ጋር አበኔር በዳዊት ፊት ለመቅረብ ወደ ኬብሮን በመጡ ጊዜ ዳዊት ግብዣ አደረገላቸው፡፡ 21 አበኔርም ለዳዊት፣ “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉና በፈለግኸውም ሁሉ ላይ እንድትገዛ ተነሥቼ እስራኤልን ሁሉ ወደ አንተ እሰበስባለሁ” በማለት ገለጸለት፡፡ ዳዊትም አሰናበተው፤ አበኔርም በሰላም ሄደ፡፡ 22 ከዚያ በኋላ የዳዊትና የኢዮአብ ወታደሮች ከዘመቻ ሲመለሱ ብዙ ምርኮ ይዘው መጡ፡፡ ዳዊት አሰናብቶት ስለነበረና እርሱም በሰላም ስለሄደ አበኔር በኬብሮን ከዳዊት ጋር አልነበረም፡፡ 23 ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፣ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መጣ ንጉሡም አሰናበተው እርሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮአብ ነገሩት፡፡ 24 ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ ለምን ይሄድ ዘንድ አሰናበትኸው? 25 የኔር ልጅ አበኔር የመጣው አንተን ሊያታልልህ፣ ዕቅድህን ለማወቅና የምታደርገውን ማንኛውንም ነገር ለማጥናት እንደሆነ አታውቅምን?” 26 ኢዮአብ ከዳዊት ዘንድ በወጣ ጊዜ አበኔር ዘንድ መልእክተኞችን ላከ እነርሱም ከሴይር የውሃ ጉድጓድ አጠገብ መለሱት፡፡ ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር፡፡ 27 አበኔር ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮአብ በቆይታ ለማነጋገር ወደ ቅጥሩ ዞር አደረገው በዚያም ሆዱን ወግቶ ገደለው፤ በዚህም ዓይነት መንገድ የወንድሙን የአሣሄልን ደም ተበቀለ፡፡ 28 ዳዊት ይህንን በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፣ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአብኔር ደም በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ንጹሕ ነን፤ 29 ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም አሠቃቂ የቆዳ በሽታ ያለበት፣ በምርኩዝ የሚሄድ አንካሳ፣ ወይም በሰይፍ የሚገደል ወይም ምግብ አጥቶ የሚራብ ሰው ከኢዮአብ ቤት አይታጣ፡፡” 30 ስለዚህ ወንድማቸውን አሣሄልን በገባዖን በተደረገው ጦርነት ገድሎባቸው ነበርና፣ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ አበኔርን ገደሉት፡፡ 31 ዳዊት ለኢዮአብና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፣ “ልብሳችሁን ቀዳችሁ፣ ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር አስከሬን ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ንጉሥ ዳዊትም አስከሬኑን ከሚያጅበው ሕዝብ ጋር አብሮ ይሄድ ነበር፡፡ 32 አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ጮኾ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ፡፡ 33 ንጉሡም በሐዘን እንጉርጉሮ ለአበኔር አለቀሰ፣ “አበኔር እንደ ተራ ሰው ሊሞት ይገባው ነበር? 34 እጆችህ አልታሰሩም፤ እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤ ሰዎች በግፈኞች ፊት እንደሚወድቁ አንተም እንደዚሀ ወደቅህ፡፡” ሕዝቡም ሁሉ እንደገና አለቀሱለት፡፡ 35 ገና ቀን ሳለ ምግብ እንዲበላ ለማድረግ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ዳዊት መጡ፤ ዳዊት ግን፣ “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ማንኛውንም ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ፡፡ 36 ሕዝቡም ሁሉ የዳዊትን ሐዘን ተመለከቱ፤ ንጉሡ የሚያደርገው ሁሉ በእርግጥ ደስ ያሰኛቸው ስለነበረ፣ በዚህም ደስ አላቸው፡፡ 37 ስለዚህ የኔር ልጅ አበኔር ይገደል ዘንድ የንጉሡ ፍላጎት እንዳልነበረ ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ በዚያን ዕለት ዐወቁ፡፡ 38 ንጉሡ ለአገልጋዮቹ እንደዚህ አላቸው፣ “በዛሬይቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን? 39 ምንም እንኳን የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም እኔ ደካማ ነኝ፤ እነዚህ የጽሩይ ልጆች እጅግ ጨካኞች ሆነውብኛል፡፡ እንደ ክፋቱ በመቅጣት እግዚአብሔር ለክፉ አድራጊው እንደ እጁ ሥራ መጠን ይክፈለው፡፡”