1 ከዚህ በኋላ ዳዊት፤ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፣ እግዚአብሔርም፣"አዎን ውጣ" ብሎ መለሰለት ዳዊትም፣ "ወደ የትኛይቱ ከተማ ልውጣ?" ብሎ ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ "ወደ ኬብሮን" ብሎ መለሰለት፡፡ 2 ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ሄደ፡፡ 3 ዳዊት ቤተ ሰቦቻቸውን ይዘው የመጡትን ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን ከተሞች ይዟቸው መጣ፡፡ 4 ከዚያ በኋላም የይሁዳ ሰዎች ወደ ኬብሮን መጥተው ዳዊትን በይሁዳ ቤት ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት። ሳኦልንም የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች እንደቀረቡት ለዳዊት ነገሩት። 5 ስለዚህ ዳዊት ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞች ልኮ እንደዚህ አላቸው፣ “ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር ይህንን በጎነት ስላሳያችሁ በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ናችሁ፡፡ 6 አሁንም እግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፡፡ 7 እንግዲህ እጆቻችሁ ይጠንክሩ፣ በርቱ፤ ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና፣ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል፡፡” 8 የሳኦል ሠራዊት አዛዥ፣ የኔር ልጅ አበኔር ግን የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፤ 9 ኢያቡስቴንም በገለዓድ፣ በአሴር፣ በኢይዝራኤል፣ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው፡፡ 10 የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፣ ሁለት ዓመትም ገዛ፡፡ የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ፡፡ 11 ዳዊት በኬብሮን በይሁዳ ቤት ላይ ንጉሥ የሆነበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበር፡፡ 12 የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ አገልጋዮች ከመሃናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ፡፡ 13 እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች በገባዖን ኩሬ አጠገብ ተገናኟቸው፤ በዚያም አንዱ ወገን በኩሬው ወዲህ ማዶ፣ ሌላው ወገን ደግሞ በኩሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ፡፡ 14 አበኔርም ለኢዮአብ፣ “ጎልማሶች ይነሡና እርስ በርሳቸው ይጋጠሙ” አለው፡፡ ኢዮአብም፣ “እሺ፣ ይነሡ” አለ፡፡ 15 ከዚያ በኋላም ከብንያምና ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ ወገን አሥራ ሁለት፣ የዳዊት አገልጋዮች ከሆኑት ደግሞ አሥራ ሁለት ጎልማሶች ተነሥተው በአንድነት ተሰባሰቡ፡፡ 16 እያንዳንዱም ሰው የባላጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጎኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ፡፡ ስለዚህ በገባዖን ያለው ያ ስፍራ በዕብራይስጥ ‘ሐልቃት አዙሪም’ ወይም ‘የሰይፍ ምድር’ ተባለ፡፡ 17 በዚያን ዕለት ጦርነቱ እጅግ ከባድ ነበር፣ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት አገልጋዮች ድል ሆኑ፡፡ 18 ሦስቱ የጽሩያ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ፡፡ አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበር፤ 19 አሣሄል በየትኛውም አቅጣጫ ዞር ሳይል አበኔርን በቅርበት ተከታተለው፡፡ 20 አበኔርም ወደ ኋላው ዞር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል አንተ ነህን?” አለው፡፡ እርሱም፣ “እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት፡፡ 21 አበኔርም፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጎልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው፤ አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር። 22 እንደገናም አበኔር “እኔን መከታተል ብትተው ይሻልሃል፤ እኔስ ለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት ቀና ብዬ እንዴት አያለሁ?” አለው። 23 አሣሄል ግን ዘወር ለማለት እምቢ አለ፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ አካላቱን ወጋው፤ ጦሩም በአካሉ በሌላው ወገን ዘልቆ ወጣ፤ አሣሄልም ወደቀ፣ በዚያ ስፍራም ሞተ፡፡ ስለሆነም አሣሄል ወደ ወደቀበት ይመጣ የነበረ እያንዳንዱ ሰው በዚያ ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር፡፡ 24 ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን አሳደዱት፤ ፀሐይም በምትጠልቅበት ጊዜ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጋይ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደረሱ፡፡ 25 የብንያም ሰዎችም ከአበኔር በስተኋላ ተሰብስበው በተራራው ጫፍ ላይ ቆሙ፡፡ 26 ከዚያ በኋላም አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፣ “ሰይፍ ለዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ በመጨረሻ መራራ መሆኑን አንተ አታውቅምን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደድ እንዲያቆሙ የማትነግራቸውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” አለው፡፡ 27 ኢዮአብም ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ ይህን ባትናገር ኖሮ፣ ወታደሮቼ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ባሳደዱ ነበር” ብሎ መለሰ፡፡ 28 ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ሰዎቹም ሁሉ ቆሙ፤ ከዚያ በኋላም እስራኤልን አላሳደዱም፣ መዋጋታቸውንም አልቀጠሉም፡፡ 29 አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ በዓረባ በኩል አለፉ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረው በማግሥቱ ጥዋት ሲጓዙ ቆይተው ከዚያ በኋላ ወደ መሃናይም ደረሱ፡፡ 30 ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ። እርሱም አሣሄልንና ከዳዊት ወታደሮች አሥራ ዘጠኙ የጎደሉባቸውን ሰዎቹን ሁሉ ሰበሰበ፡፡ 31 የዳዊት ሰዎች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ሥልሳ ብንያማውያንን ገድለዋል፡፡ 32 ከዚያ በኋላም አሣሄልን ከወደቀበት አንሥተው ቤተ ልሔም በነበረው በአባቱ መቃብር ቀበሩት፡፡ ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሠው ኬብሮን ሲደርሱ ሌሊቱ ነጋላቸው፡፡