1 ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ሞተ፣ ልጁ ሐኖንም በእርሱ ምትክ ንጉሥ ሆነ፡፡ 2 ዳዊትም፣ “አባቱ ቸርነትን እንዳደረገልኝ ሁሉ እኔን ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነትን አደርግለታለሁ፡፡” አለ፡፡ ስለዚህ በአባቱ ምክንያት ከደረሰበት ኃዘን ያጽናኑት ዘንድ ዳዊት አገልጋዮቹን ላከ፡፡ አገልጋዮቹም ወደ አሞን ምድር ገቡ፡፡ 3 የአሞን ሕዝብ መሪዎች ግን ለጌታቸው ለሐኖን እንደዚህ አሉት፣ “አንተን እንዲያጽናኑ ሰዎቹን በመላኩ ዳዊት በእርግጥ አባትህን በማክበር ነው ብለህ ታስባለህን? ዳዊት ሰዎቹን የላከው ከተማይቱን እንዲመለከቱና ያጠፏትም ዘንድ እንዲሰልሏት አይደለምን?” 4 ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፤ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም እስከ ቂጣቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ሰደዳቸው፡፡ 5 ይህንን ለዳዊት በገለጹለት ጊዜ፣ ሰዎቹ እጅግ አፍረው ነበርና መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላከ፡፡ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪኮ ቆዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው፡፡ 6 የአሞን ሰዎች ለዳዊት መጥፎ ጠረን እንዳላቸው ሰዎች እንደሆኑበት ባወቁ ጊዜ የአሞን ሰዎች መልእክተኞችን ልከው ከቤትሮዖብና ከሱባ ሃያ ሺህ አራማውያን እግረኛ ወታደሮችን፣ ከንጉሥ መዓካ አንድ ሺህ ሰዎችን ደግሞም ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎችን ቀጠሩ፡፡ 7 ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን ከመላው ተዋጊ ሠራዊት ጋር ላከው፡፡ 8 አሞናውያን ወጥተው በከተማቸው መግቢያ በር ላይ ሲሰለፉ፤ የሱባና የረአብ አራማውያን ሰዎች ለብቻቸው ሜዳው ላይ ቆሙ፡፡ 9 ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፣ በእስራኤል በጀግንነታቸው ከታወቁት ጥቂቶቹን መርጦ በአራማውያን ግንባር አሰለፋቸው፡፡ 10 የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ ሥር መድቦ በአሞናውያን ሠራዊት ግንባር አሰለፋቸው፡፡ 11 ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ “አራማውያን የሚያይሉብኝ ከሆነ አንተ መጥተህ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን የሚያይሉብህ ከሆነ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ፡፡ 12 እንግዲህ በርታ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ጠንካሮች መሆናችንን እናስመስክር፤ እግዚአብሔርም ለዓላማው መልካም መስሎ የታየውን ያደርጋል፡፡” 13 ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ከእስራኤል ሠራዊት ፊት እንዲሸሹ ወደ ተገደዱት ወደ አራማውያን በመገሥገሥ ወደ ጦርነቱ ሄዱ፡፡ 14 አራማውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፣ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማይቱ ውስጥ ገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ከአሞናውያን ሕዝብ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ 15 አራማውያን በእስራኤላውያን እየተሸነፉ እንደሆኑ ባዩ ጊዜ እንደ ገና ተሰባሰቡ፡፡ 16 አድርአዛር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ወደነበሩት ወደ አራማውያን ሠራዊት መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም በአድርአዛር ሠራዊት አዛዥ በሶባክ መሪነት ወደ ዔላም መጡ፡፡ 17 ይሄ ነገር ለዳዊት በተነገረው ጊዜ መላውን እስራኤልን ሰበሰበ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ዔላም ሄደ፡፡ አራማውያን ለጦርነት ተሰልፈው ዳዊትን ገጠሙት ተዋጉትም፡፡ 18 አራማውያን ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ሰባት መቶ ሠረገለኞችንና አርባ ሺህ ፈረሰኞችን ገደለ፡፡ የሠራዊቱ አዛዥ ሶባክም ቆስሎ በዚያ ሞተ፡፡ 19 የአድርአዛር አገልጋዮች የነበሩት ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም መሠረቱ ተገዙላቸውም፡፡ ስለዚህም ሶርያውያን ከዚያ በኋላ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ፡፡