11

1 ነገሥታት ወደ ጦርነት መውጣታቸው የተለመደ በነበረበት በፀደይ ወራት ዳዊት ኢዮአብን፣ አገልጋዮቹንና መላውን የእስራኤል ሠራዊት ወደ ዘመቻ ላካቸው፤ እነርሱም አሞናውያንን አጠፉ፤ ረባትንም ከበቡአት፡፡ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀረ፡፡ 2 ከዚህም የተነሣ በአንድ የምሽት ወቅት ዳዊት ከዐልጋው ተነስቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ በዚያም ስፍራ ሆኖ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ በጣም ውብ ነበረች፡፡ 3 ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ የሚያውቁ ሰዎችን አጠያየቀ፡፡ አንድ ሰውም፣ “ይህች ቤርሳቤህ የኤልያብ ልጅ፣ የኬጢያዊው የኦርዮን ሚስት አይደለችምን?” 4 ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፣ (ከወር አበባ ጊዜዋ የነጻችበት ወቅት ነበርና) አብሮአት ተኛ፡፡ ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች፡፡ 5 ሴቲቱ ፀነሰች፣ “አርግዣለሁ” ብላም ወደ ዳዊት መልእክት ላከችበት፡፡ 6 ከዚያ በኋላም ዳዊት ለኢዮአብ፣ “ኬጢያዊውን ኦርዮንን ወደ እኔ ላክልኝ” ብሎ መልእክት ላከበት፡፡ ስለዚህም ኢዮአብ ኦርዮንን ወደ ዳዊት ላከው፡፡ 7 ኦርዮን በደረሰ ጊዜ ኢዮአብና ሠራዊቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው፡፡ 8 ዳዊትም ለኦርዮን፣ “ወደ ቤትህ ሄደህ እግርህን ተታጠብ” አለው፡፡ ኦርዮንም ከቤተ መንግሥቱ ወጣ፣ ንጉሡም ኦርዮን ከወጣ በኋላ ስጦታ አስከትሎ ላከለት፡፡ 9 ኦርዮን ግን ከጌታው አገልጋዮች ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጥር በር ተኛ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር፡፡ 10 ለዳዊት “ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም” ብለው በነገሩት ጊዜ፣ ዳዊት ኦርዮንን፣ “ከመንገድ መግባትህ አይደለምን? ለምን ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡ 11 ኦርዮም ዳዊትን፣ “ታቦቱ፣ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፣ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም አገልጋዮች ገላጣ ሜዳ ላይ ሰፍረው፤ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? እንዲህ ያለውን ነገር እንደማላደርገው በነፍስህ እምላለሁ፡፡” አለው፡፡ 12 ከዚህም የተነሣ ዳዊት ለኦርዮ፣ “ዛሬ ደግሞ በዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው፡፡ ስለዚህ ኦርዮ በዚያ ዕለትና በማግሥቱ እዚያው ኢየሩሳሌም ቆየ፡፡ 13 ዳዊትም ባስጠራው ጊዜ በእርሱ ፊት በላ ደግሞም ጠጣ፣ ዳዊትም እንዲሰክር አደረገው፤ ሲመሽም ኦርዮን በአልጋው ላይ ለመተኛት የጌታው አገልጋዮች ወዳሉበት ሄደ፣ ወደ ቤቱ ግን አልሄደም፡፡ 14 ስለዚህ በማግስቱ ሲነጋ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮን እጅ ላከለት፡፡ 15 በደብዳቤውም ውስጥ ዳዊት፣ “ኦርዮንን ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም እንዲመታና እንዲሞት ከኋላው አፈግፍጉ” ብሎ ጻፈ፡፡ 16 ስለዚህ ኢዮአብ የከተማይቱን መከበብ እየተመለከተ ሳለ ጠንካሮቹ የጠላት ሠራዊት እየተዋጉ እንዳሉ በሚያውቅበት ግንባር ኦርዮንን መደበው፡፡ 17 የከተማይቱ ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት በገጠሙበት ጊዜ ከዳዊት ወታደሮች ጥቂቶቹ ሞቱ፣ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮንም በዚያ ሞተ፡፡ 18 ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት በላከበት ጊዜ፣ 19 መልእክተኛውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፣ “ጦርነቱን በሚመለከት ሁሉንም ነገር ለንጉሡ ከጨረስክ በኋላ፣ 20 ምናልባት ንጉሡ ይቆጣና፣ ‘ለመዋጋት ስትሉ ወደ ከተማይቱ ይህን ያህል የተጠጋችሁት ስለምንድን ነው? በግንቡ ቅጥር ላይ ሆነው ፍላፃ እንደሚወርውሩባችሁ አታውቁም ኖሮአል? 21 የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ እንዲሞት ያደረገችው አንዲት ሴት ከግንቡ ላይ የወፍጮ መጅ ስለለቀቀችበት አይደለምን? ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ይልህ ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቶአል’ ብለህ ንገረው፡፡” 22 ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ወደ ዳዊት ዘንድ ሄደ፣ ኢዮአብ እንዲናገር የላከውን ማንኛውንም ነገር ነገረው፡፡ 23 መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፣ “እኛ በመጀመሪያ ከነበረው ይልቅ ጠላት በርትቶ ነበር ወደ ሜዳው ወደ እኛ ዘንድ መጡ፤ እኛም እስከ ቅጥሩ መግቢያ በር ድረስ አሳድደን መለስናቸው፡፡ 24 የእነርሱም ባለ ፍላጻዎች ከግንቡ ላይ ሆነው በወታደሮችህ ላይ ቀስት ወረወሩ፣ ከንጉሡ አገልጋዮችም ጥቂቶችን ገደሉ፤ አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ፡፡” 25 ከዚያ በኋላ ዳዊት ለመልእክተኛው፣ “ለኢዮአብ፣ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፣ ሌላ ጊዜም ሌላውን ይበላልና ይህ አያሳዝንህ፡፡ በከተማይቱ ላይ ውጊያህን አጠናክረህ አፍርሳት፡፡’ በለው፣ ኢዮአብን አበረታታው፡፡” 26 ስለዚህ የኦርዮ ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ አምርራ አለቀሰችለት፡፡ 27 የሐዘኗም ጊዜ ካበቃ በኋላ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ ወሰዳት፣ ሚስቱም ሆነች፣ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር እግዚአብሔርን አሳዘነው፡፡