1 እግዚአብሔር ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፣ “በአንድ ከተማ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ድኻ ነበረ፡፡ 2 ባለጠጋው እጅግ ብዙ መንጋዎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ 3 ድኻው ግን ከገዛትን ካሳደጋት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም፡፡ ይህች በግ ከእርሱ ጋር ኖረች ከልጆቹም ጋር አደገች፡፡ በጊቱ እንዲያውም ከእርሱ ጋር ትበላ፣ ከጽዋውም ትጠጣ ነበር፤ በእቅፉም ትተኛ ነበር፣ ለእርሱም እንደ ሴት ልጁ ነበረች፡፡ 4 አንድ ቀን አንድ እንግዳ ወደ ባለጠጋው ቤት መጣ፤ ባለጠጋው ግን ለእንግዳው ምግብ ለማቅረብ ከራሱ መንጋ ወይም ከቀንድ ከብቶቹ አንድ እንሰሳ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ የድኻውን ጠቦት በግ ወስዶ ለእንግዳው ምግብ አድርጎ አዘጋጀለት፡፡” 5 ዳዊትም በባለጠጋው ላይ ቁጣው ነደደ፣ በንዴትም ለናታን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! 6 እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ለደኻውም ባለመራራቱ ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት፡፡” 7 ከዚያ በኋላም ናታን ለዳዊት፣ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል፣ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ 8 የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ብዙ ሌሎች ነገሮችንም ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር፡፡ 9 ስለዚህ በእርሱ ፊት ክፉ የሆነውን ታደርግ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕግ ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮንን በሰይፍ ገደለህ፣ ሚስቱንም ወስደህ የራስህ ሚስት አደረግኸት፡፡ ኦርዮንን በአሞናውያን ሠራዊት ሰይፍ ገደልኸው፡፡ 10 እኔን አቃለኸኛልና የኬጢያዊውንም የኦርዮንን ሚስት ሚስትህ አድርገህ ወስደሃልና ሰይፍ ከቤትህ በፍጹም አይርቅም፡፡’ 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘ከራስህ ቤት ጥፋት አስነሳብሃለሁ፤ ዓይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለጎረቤትህ እሰጠዋለሁ፣ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል፡፡ 12 አንተ ኃጢአትህን በስውር አደረግህ፤ እኔ ግን ይህንን ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ፡፡’” 13 ከዚያም ዳዊት ለናታን፣ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” አለው፡፡ ናታንም ለዳዊት መለሰለት፣ “እግዚአብሔር ኃጢአትህን አስወግዶልሃል፡፡ አንተ አትሞትም፤ 14 ይሁን እንጂ በዚህ ድርጊትህ እግዚአብሔርን ስላቃለልህ የተወለደልህ ልጅ በእርግጥ ይሞታል፡፡” 15 ከዚያ በኋላ ናታን ወጥቶ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ እግዚአብሔርም የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ እግዚአብሔር አስጨነቀው እጅግም ታመመ፡፡ 16 ዳዊት ስለ ልጁ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም ከዚያም ወደ ክፍሉ ገብቶ ሌሊቱን ወለሉ ላይ ተኝቶ አደረ፡፡ 17 የቤተሰቡ ሽማግሌዎችም ከወለሉ ላይ ያነሱት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፣ እርሱ ግን አልተነሳም፣ ከእነርሱም ጋር አልበላም፡፡ 18 በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ፡፡ “እነሆ፣ ሕፃኑ ገና በሕይወት ሳለ ስናነጋግረው ድምፃችንን አልሰማንም፣ ታዲያ፣ ሕፃኑ ሞቶአል ብንለው በራሱ ላይ ምን ያደርግ ይሆን?!” ብለው ስለነበረ፣ የዳዊት አገልጋዮች ሕፃኑ እንደ ሞተ ለመንገር ፈርተው ነበር፡፡ 19 ነገር ግን እርስ በርሳቸው ሲንሾካሾኩ ዳዊት በተመለከተ ጊዜ፣ ሕፃኑ እንደ ሞተ ዳዊት ተገነዘበ፤ ለአገልጋዮቹም፣ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም፣ “ሞቶአል” ብለው መለሱለት፡፡ 20 ከዚያም ዳዊት ከወለሉ ላይ ተነስቶ ታጠበ፣ ቅባት ተቀባ ደግሞም ልብሱን ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤትም ሄዶ አምልኮ አቀረበ፣ ከዚያ በኋላም ወደ ራሱ ቤተ መንግሥት ተመለሰ፡፡ ምግብ እንዲያቀርቡለት በጠየቀ ጊዜ አቀረቡለት፣ እርሱም በላ፡፡ 21 ከዚያ በኋላ አገልጋዮቹ፣ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ አለቀስህም፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” አሉት፡፡ 22 ዳዊትም፣ “ሕፃኑ ገና በሕይወት ሳለ ጾምሁ አለቀስሁም፤ ‘ሕፃኑ በሕይወት ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር ቸርነት ያደርግልኝ እንደሆነ ማን ያውቃል’ ብዬ ነበር፡፡ 23 አሁን ግን፣ እርሱ ሞቶአልና ለምን እጾማለሁ? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም፡፡” 24 ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሮአት ተኛ፡፡ ከዚህም የተነሣ ወንድ ልጅ ወለደች፣ ልጁም ሰሎሞን የሚል ስም ተሰጠው፤ እግዚአብሔርም ወደደው፡፡ 25 ስለሆነም እግዚአብሔር ስለወደደው ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ፡፡ 26 በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያን የንጉሥ ከተማ የነበረችውን ረባትን ወግቶ ምሽጉን ያዘ፡፡ 27 ስለሆነም ኢዮአብ ወደ ዳዊት መልእክተኞችን በመላክ እንዲህ አለው፣ “ረባትን ወግቼ የከተማይቱን የውሃ ማከፋፈያ ይዤአለሁ፡፡ 28 እንግዲህ አሁን፣ የቀረውን ሠራዊት አሰባስበህ በከተማይቱ ዙሪያ ሠፍረህ ያዛት፤ ምክንያቱም እኔ ከተማይቱን ከያዝኳት በስሜ መጠራቷ ነው፡፡” 29 ስለዚህ ዳዊት መላውን ሠራዊት አሰባስቦ ወደ ረባት ሄዶ ከተማይቱን ወግቶ ያዛት፡፡ 30 ዳዊት ከሞሎክ ራስ ላይ ዘውዱን ወሰደ፤ የዘውዱም ክብደት አንድ መክሊት ወርቅ ሲሆን የከበረ ዕንቁም በላዩ ላይ ነበረበት፡፡ ዘውዱም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ፡፡ ከዚያም እጅግ ብዙ የከተማይቱን ምርኮ አመጣ፡፡ 31 በከተማይቱ የነበሩትንም ሰዎች አውጥቶ በመጋዝ፣ በብረት መቆፈሪያና በመጥረቢያ እንዲሠሩ አስገደዳቸው፤ የሸክላ ጡብም እንዲሠሩ አደረጋቸው፡፡ ዳዊት የአሞን ሕዝብ ከተሞች ሁሉ ይህንኑ ተግባር እንዲፈጽሙ አደረጋቸው፡፡ ከዚያም ዳዊትና ሠራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡