1 ከዚህ በኋላ የዳዊት ልጅ አምኖን የዳዊት ሌላ ልጅ የአቤሴሎም ሙሉ እኅት በነበረችው በውቧ ግማሽ እህቱ በትዕማር እጅግ ተማረከ፡፡ 2 በእኅቱ በትዕማር ምክንያት እስኪታመም ድረስ አምኖን እጅግ ተጨነቀ፡፡ ድንግል ስለነበረች በእርሷ ላይ ምንም ነገር ማድረግ ለአምኖን የማይቻል መሰለው፡፡ 3 አምኖን ግን የዳዊት ወንድም የሳምዕ ልጅ ኢዮናዳብ የተባለ ወዳጅ ነበረው፡፡ ኢዮናዳብ እጅግ ተንኮለኛ ሰው ነበር፡፡ 4 ኢዮናዳብም ለአምኖን፣ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፣ በየጥዋቱ ጭንቀት የሚሰማህ ለምንድን ነው? አትነግረኝምን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ አምኖንም፣ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እህት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” ብሎ መለሰለት፡፡ 5 በዚህን ጊዜ ኢዮናዳብ፣ “የታመምህ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ፣ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፣ ‘እህቴ ትዕማር የምበላውን ምግብ ታቀርብልኝ ዘንድ እባክህ ላክልኝ፤ ምግቡንም ዓይኔ እያየ ከእጇ እንድጎርስ እዚሁ መጥታ ታዘጋጅልኝ’ ብለህ ጠይቀው፡፡” 6 ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው በመጣ ጊዜ አምኖን ለንጉሡ፣ “ለሕመሜ የሚሆን ጥቂት ምግብ በፊቴ እንድታዘጋጅልኝና ከእጇም እንድበላ እባክህ እህቴን ትዕማርን ላክልኝ” ብሎ ጠየቀው፡፡ 7 ከዚያም ዳዊት፣ “አሁን ሂጂና ለወንድምሽ ለአምኖን ምግብ አዘጋጂለት” በማለት በቤተ መንግሥቱ ወደ ነበረችው ትዕማር መልእክት ላከባት፡፡ 8 ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካችው በኋላ ቂጣ አደረገችው፣ ጋገረችውም፡፡ 9 ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ ቂጣውን አቀረበችለት፣ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም፡፡ ስለዚህ አምኖን በዘያ ለነበሩት ለሌሎቹ፣ “ማንኛውንም ሰው ከዚህ ከእኔ ዘንድ አስወጡልኝ” አላቸው፤ ስለዚህ ሰው ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ፡፡ 10 ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “ምግቡን ከእጅሽ እበላ ዘንድ ወደዚህ ወደ ክፍሌ አምጭልኝ” አላት፡፡ 11 ምግቡን ባመጣችለት ጊዜ አምኖን እጇን ያዛትና፣ “እህቴ ሆይ፣ ነይ ከእኔ ጋር ተኚ” አላት፡፡ 12 እርሷም፣ “አይሆንም፣ ወንድሜ ሆይ፣ አታስገድደኝ፤ ይህን የመሰለ ነገር በእስራኤል ሊደረግ አይገባውምና፡፡ ይህን አሳፋሪ ነገር አታድርግ፡፡ 13 ይሄ ነገር ከሚያስከትልብኝ ዕፍረት ለማምለጥስ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ይህም ድርጊት አንተን በመላው እስራኤል ኀፍረተ-ቢስ ጅል አድርጎ ያስቆጥርሃል፡፡ እባክህ፣ ለንጉሡ እንድትነግረው እጠይቅህሃለሁ፤ እንድታገባኝ ይፈቅድልሃል፡፡” 14 ይሁን እንጂ አምኖን አልሰማትም፡፡ ከትዕማር ይልቅ ብርቱ ስለ ነበረ ይዟት ከእርሷ ጋር ተኛ፡፡ 15 ከዚያም አምኖን ትዕማርን ከመጠን በላይ ጠላት፤ አፍቅሯት ከነበረውም ይልቅ ጠላት፡፡ አምኖንም፣ “ተነሺ፣ ውጭልኝ” አላት፡፡ 16 እርሷ ግን፣ “አይሆንም፣ ምክንያቱም እኔን በማስወጣት የምታደርገው ይህ ክፉ ነገር ቀድመህ ካደረግኸው ይልቅ የከፋ ነው፡፡” አምኖን ግን እርሷን አልሰማትም፡፡ 17 ከዚያ ይልቅ የግል አገልጋዩን ጠርቶ፣ “ይህችን ሴት ከእኔ ዘንድ አስወጥተህ፣ በሩን ቀርቅረው” አለው፡፡ 18 ከዚህ በኋላ አገልጋዩ አስወጣትና በሩን ከበስተኋላዋ ቀረቀረባት፡፡ ድንግል የሆኑት የንጉሡ ሴት ልጆች እንደዚያ ይለብሱ ነበርና፣ ትዕማር በጣም ያጌጠ ቀሚስ ለብሳ ነበር፡፡ 19 ትዕማር በራሷ ላይ ማቅ ነሰነሰች፣ ቀሚሷንም ቀደደች፡፡ እጇንም በራሷ ላይ አድርጋ ሄደች፣ በምትሄድበትም ወቅት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አለቀሰች፡፡ 20 ወንድሟ አቤሴሎምም፣ “ወንድምሽ አምኖን ካንቺ ጋር ነበርን? ሆኖም፣ እህቴ ሆይ፣ አሁን ዝም በይ፡፡ ወንድምሽ ስለሆነ ነገሩን በልብሽ አትያዢው፡፡” ስለሆነም ትዕማር በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሆና ኖረች፡፡ 21 ነገር ግን ንጉሥ ዳዊት ይህንን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፤ 22 አቤሴሎም ለአምኖን ምንም አልተናገረውም፤ ስላደረገባት ነገር እህቱንም ትዕማርን ስላስነወራት ጠልቶት ነበርና፡፡ 23 ከሁለት ሙሉ ዓመት በኋላ አቤሴሎም በጎቹን በኤፍሬም አጠገብ በነበረው በቤላሶር ከተማ በጎችን የሚሸልቱ ሰዎች አስመጥቶ ነበር፤ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ወደዚያ ስፍራ ጋበዛቸው፡፡ 24 አቤሴሎም ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ “እነሆ፣ ባሪያህ በጎችን የሚሸልቱ አስመጥቷል፣ንጉሡና አገልጋዮቹ እባክህን ከባሪያህ ጋር ይምጡ” አለው፡፡ 25 ንጉሡም ለአቤሴሎም፣ “ልጄ ሆይ፣ ሁላችንም መሄድ የለብንም፤ ሸክም እንሆንብሃለን” ብሎ መለሰለት፡፡ አቤሴሎም ንጉሡን አደፋፈረው፣ እርሱ ግን መሄድ ባይፈልግም አቤሴሎምን ባረከው፡፡ 26 ከዚህ በኋላ አቤሴሎም፣ “ይሄ ካልሆነ፣ እባክህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር ይሂድ” አለው፡፡ ስለዚህ ንጉሡ አቤሴሎምን፣ “አምኖን አብሮአችሁ የሚሄደው ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ 27 አቤሴሎም አጥብቆ ስለለመነው፣ አምኖንና የንጉሡ ልጆች አብረውት እንዲሄዱ ፈቀደ፡፡ 28 አቤሴሎም አገልጋዮቹን፣ “ልብ ብላችሁ አድምጡ፣ አምኖን ወይን ጠጅ ጠጥቶ መስከር ሲጀምርና እኔ ‘አምኖንን ምቱት’ ስላችሁ፣ በዚያን ጊዜ ግደሉት፤ አትፍሩ፡፡ ያዘዝኋችሁ እኔ ነኝና በርቱ፣ ጠንክሩ፡፡” ብሎ አዘዛቸው፡፡ 29 ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት፡፡ ከዚያ በኋላም የንጉሡ ልጆች በየበቅሎአቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ፡፡ 30 እነርሱም እየሄዱ በመንገድ ላይ ሳሉ፣ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገደለ፣ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ዜና ለዳዊት ደረሰው፡፡ 31 ከዚያ በኋላ ንጉሡ ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፣ በወለሉም ላይ ተጋደመ፣ አገልጋዮቹም ልብሳቸውን ቀደው በአጠገቡ ቆሙ፡፡ 32 የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ ግን፣ “የሞተው አምኖን ብቻ ነውና የንጉሡ ልጆች የሆኑትን ጎልማሶች ሁሉ ገድለዋቸዋል ብሎ ጌታዬ አይመን፡፡ አምኖን እህቱን ትዕማርን ከደፈራት ቀን አንስቶ አቤሴሎም ይህንን ሲያቅድ ነበር፤ 33 ስለሆነም የሞተው አምኖን ብቻ ነውና፣ የንጉሡ ልጆች ሁሉ ሞተዋል ብሎ እስከሚያምን ድረስ ጌታዬ ንጉሡ የሚለውን ዜና ወደ ልቡ አያስገባው፡፡” 34 አቤሴሎም ሸሸ፡፡ ለጥበቃ የቆመውም አገልጋይ ቀና ብሎ ሲመለከት ከእርሱ በስተምዕራብ ካለው ኮረብታ ጥግ ባለው መንገድ ብዙ ሰዎች ሲመጡ አየ፡፡ 35 በዚያን ጊዜ ኢዮናዳብ ለንጉሡ፣ “እነሆ፣ የንጉሡ ልጆች እየመጡ ነው፤ ልክ ባሪያህ እንዳለው ነው፡፡” 36 ስለሆነም ተናግሮ እንደጨረሰ፣ የንጉሡ ልጆች ደረሱ፣ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፡፡ ንጉሡና አገልጋዮቹም ሁሉ አምርረው አለቀሱ፡፡ 37 አቤሴሎም ኮብልሎ የጌሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ፡፡ ዳዊትም ስለ ሞተው ልጁ ዘወትር ያለቅስ ነበር፡፡ 38 አቤሴሎም ለሶስት ዓመታት ወደ ቆየበት ወደ ጌሹር ሸሽቶ ሄደ፡፡ 39 በልጁ በአምኖን ሞት ከደረሰበት ሐዘን ተጽናንቶ ስለነበረ ንጉሥ ዳዊት በሃሳቡ ወደ አቤሴሎም የመሄድ ናፍቆት አደረበት፡፡