14

1 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ ተረዳ፡፡ 2 ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ቴቁሔ ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጥቶ፣ “ሐዘንተኛ በመምሰል የሐዘን ልብስ ልበሺ፣ እባክሽን ዘይት አትቀቢ ነገር ግን ለብዙ ጊዜ እንዳዘነች መስለሽ ታዪ፡፡ 3 ከዚያም ወደ ንጉሡ ሄደሽ እኔ የምገልጽልሽን ንገሪው፡፡” ስለዚህ ኢዮአብ ለንጉሡ የምትናገረውን ነገር ነገራት፡፡ 4 ከቴቁሔ የመጣችውም ሴት ለንጉሡ ለመንገር በገባችበት ጊዜ በንጉሡ ፊት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት፣ “ንጉሥ ሆይ፣ እርዳኝ” አለች፡፡ 5 ንጉሡም፣ “ችግርሽ ምንድን ነው?” አላት፡፡ ሴቲቱም፣ “እኔ በእውነቱ ባሏ የሞተባት ባልቴት ነኝ፡፡ 6 እኔ ባሪያህ ሁለት ልጆች ነበሩኝ፣ እነርሱም ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፣ የሚገላግላቸውም ሰው አልነበረም፡፡ አንደኛውም ሌላኛውን መታውና ገደለው፡፡ 7 መላው ቤተሰብም አሁን በባሪያህ ላይ ተነሥቶ፣ ’ስለገደለው ስለ ወንድሙ ዋጋ እንዲከፍልና እኛም እንድንገድለው ወንድሙን የገደለውን ሰው አውጥተሸ ስጪን’ አሉኝ፤ ወራሽ የሆነውንም ያጠፉ ዘንድ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ዓይነት የቀረኝን አንድ የጋለ ፍም አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው፡፡” 8 ስለዚህ ንጉሡ ለሴቲቱ፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፣ አንድ ነገር እንዲደረግልሽ እኔ ትዕዛዝ እሰጣለሁ” አላት፡፡ 9 የቴቁሔዪቱም ሴት ለንጉሡ፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች፡፡ 10 ንጉሡም፣ “ማንም ሰው ቢናገርሽ ወደ እኔ ዘንድ አምጪው ከዚያ በኋላም አያስቸግርሽም” በማለት መለሰላት፡፡ 11 ከዚያ በኋላ ሴቲቱ፣ “ደም ተበቃዩ ሌላ ሰው እንዳያጠፋና ልጄንም እንዳያጠፉት፣ እባክህን ንጉሥ እግዚአብሔር አምላክህን አሳስብልኝ” አለችው፡፡ ንጉሡም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን ከልጅሽ ራስ አንዲት ፀጉር እንኳ አትወድቅም” ብሎ መለሰላት፡፡ 12 ከዚያ በኋላም ሴቲቱ፣ “ባሪያህ ለጌታዬ ለንጉሡ ተጨማሪ ቃል እንድናገር እባክህ ፍቀድልኝ” አለችው፡፡ ንጉሡም፣ “ተናገሪ” አላት፡፡ 13 ስለዚህ ሴቲቱ፣ “ታዲያ፣ እንዲሀ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህንን በመናገሩ ንጉሡ ራሱን በደለኛ እንደሚያደርግ ሰው ነው፣ የኮበለለውን ልጁን ንጉሡ ወደ ቤቱ አልመለሰውምና፡፡ 14 ሁላችንም እንሞት ዘንድ ይገባናልና፣ እንደገናም ሊሰበሰብ እንደማይችል እንደ ፈሰሰ ውሃ ነንና፡፡ እግዚአብሔር ግን የሰውን ሕይወት አይወስድም ይልቁንም ከፊቱ ራሱን ያስኮበለለውን ሰው ወደ ራሱ የሚመልስበት መንገድ ይፈልጋል እንጂ፡፡ 15 እንግዲህ አሁን ለጌታዬ ለንገሡ ይህንን ልናገር የመጣሁት ሕዝቡ እንድፈራ ስላደረጉኝ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ባሪያህ ለራሷ፣ ‘አሁን ለንጉሡ እናገራለሁ፣ ምናልባትም ንጉሡ የባሪያውን ጥያቄ ይቀበል ያደርግላት ይሆናል፡፡ 16 እኔንና ልጄን ከእግዚአብሔር ርስት ሊያጠፋን ካለው ሰው እጅ ያድን ዘንድ ባሪያውን ያወጣ ዘንድ ንጉሡ ይሰማኛልና፣’ አለች፡፡ 17 ከዚያ በኋላም ባሪያህ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፣ የጌታዬ የንጉሡ ቃል እፎይታን የሚሰጠኝ ይሁን፣ ምክንያቱም መልካሙን ከክፉው በመለየት ጌታዬ ንጉሡ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና’ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ይሁን፡፡” 18 ከዚያ በኋላም ንጉሡ ለሴቲቱ፣ “እኔ ለምጠይቅሽ ጥያቄ እባክሽ ምንም ነገር አትደብቂኝ” አላት፡፡ 19 ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር የለም?” ሴቲቱም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከተናገረው አንዳችም ነገር ማንም ሰው ወደ ቀኝም ወደ ግራም ማምለጥ አይችልም፡፡ ያዘዘኝና ባሪያህም የተናገረችውን እነዚህን ነገሮች እንድናገር የነገረኝ ባሪያህ ኢዮአብ ነው፡፡ 20 ባሪያህ ኢዮአብ ይህንን ያደረገው ነገሮች እየሄዱበት ያለውን አቅጣጫ ለመለወጥ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ጥበብ ጌታዬ ጠቢብ ነው፤ በምድሪቱም የሚሆነውን ማንኛውንም ነገር ያውቃል፡፡” 21 ስለዚህ ንጉሡ ለኢዮአብ፣ “እነሆ፣ እኔ አሁን ይህንን አደርጋለሁ፡፡ እንግዲህ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን አምጣው” አለው፡፡ 22 ስለዚህ ኢዮአብ ለንጉሡ አክብሮቱንና ምስጋናውን ለመግለጽ ጎንበስ ብሎ እጅ ነሳ፡፡ ኢዮአብም፣ “ዛሬ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ፊት ሞገስ እንዳገኘ አወቅሁ፣ ንጉሡ የባሪያውን ጥያቄ ፈጽሞለታልና” 23 ስለዚህ ኢዮአብ ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፣ አቤሴሎምንም ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡ 24 ንጉሡም፣ “ወደ ራሱ ቤት መመለስ ይችላል፣ ነገር ግን ፊቴን አያይም” ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ቤቱ ተመለሰ፣ የንጉሡን ፊት ግን አላየም፡፡ 25 በመላው እስራኤል ከአቤሴሎም ይልቅ በመልከ መልካምነቱ የተመሰገነ ማንም አልነበረም፡፡ ከእግር ተረከዙ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ ምንም እንከን አልነበረበትም፡፡ 26 ይከብደው ስለ ነበረ የራሱን ፀጉር በሚቆረጥበት ጊዜ ፀጉሩን ይመዝነው ነበር፣ በንጉሡም የመመዘኛ ልክ ሁለት መቶ ሰቅል ይመዝን ነበር፡፡ 27 አቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የምትባል አንድ ሴት ልጅ ነበሩት፡፡ ሴት ልጁም ውብ ነበረች፡፡ 28 አቤሴሎምም የንጉሡን ፊት ሳያይ ሁለት ሙሉ ዓመት በኢየሩሳሌም ኖረ፡፡ 29 ከዚህ በኋላ ወደ ንጉሡ ይወስደው ዘንድ አቤሴሎም ወደ ኢዮአብ መልእክት ላከ፣ ኢዮአብ ግን ሊመጣ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ አቤሴሎም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢዮአብ መልእክት ላከ፣ ኢዮአብ ግን አሁንም አልመጣም፡፡ 30 ስለዚህ አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ፣ “ኢዮአብ በእኔ እርሻ አጠገብ እርሻ አለው፣ በዚያም ገብስ አለው፤ ሂዱና በገብሱ ላይ እሳት ልቀቁበት” አላቸው፡፡ ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች በእርሻው ላይ እሳት ለቀቁበት፡፡ 31 ከዚያም ኢዮአብ ተነስቶ ወደ አቤሴሎም ቤት መጣና፣ “አገልጋዮችህ በእርሻዬ ላይ እሳት የለቀቁበት ለምንድን ነው?” አለው፡፡ 32 አቤሴሎምም ለኢዮአብ፣ “እነሆ፣ ወደ አንተ ዘንድ፣ ‘ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ዘንድ መጥተህ ለንጉሡ፣ ከጌሹር ለምን መጣሁ? እዚያው ብቆይ ይሻለኝ ነበር’ ብለህ እንድትነግርልኝ መልእክት ልኬብህ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን የንጉሡን ፊት ልይ፣ በደለኛ ከሆንኩም ይግደለኝ” አለው፡፡ 33 ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄዶ ነገረው፡፡ ንጉሡም አቤሴሎምን ባስጠራው ጊዜ አቤሴሎም በንጉሡ ፊት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፣ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው፡፡