15

1 ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ ሃምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ፡፡ 2 አቤሴሎም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማይቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆማል፡፡ ሙግት ያለበት ማንኛውም ሰው ዳኝነት ለማግኘት ወደ ንጉሡ ሲመጣ፣ በዚያን ጊዜ አቤሴሎም ወደ እርሱ ይጠራውና፣ “ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” ይለው ነበር፡፡ ሰውዬውም፣ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው?” ይለው ነበር፡፡ 3 ከዚህም የተነሣ አቤሴሎም፣ “ተመልከት፣ ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ጉዳይህን ለመመልከት ከንጉሡ ሥልጣን የተሰጠው ማንም ሰው የለም፡፡” ይለው ነበር፡፡ 4 ከዚህ ጋር በማያያዝ አቤሴሎም፣ “ሙግት ወይም ጉዳይ ያለው ማንኛውም ሰው ወደ እኔ እንዲመጣና እኔም ፍትሕ እንድሰጠው በምድሪቱ ዳኛ ሆኜ መሾም እመኛለሁ” ይል ነበር፡፡ 5 ስለዚህ ክብርን ሊሰጠው ማንኛውም ሰው ወደ አቤሴሎም በሚመጣበት ጊዜ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር፡፡ 6 ከንጉሡ ፍትሕ ለማግኘት በሚመጡ እስራኤላውያን ሁሉ አቤሴሎም እንደዚህ ያደርግ ነበር፡፡ በዚህም ሁኔታ አቤሴሎም የእስራኤላውያንን ልብ ሰረቀ፡፡ 7 በአራተኛው ዓመት ፍጻሜ አቤሴሎም ለንጉሡ፣ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ እባክህን ፍቀድልኝ፡፡ 8 ባሪያህ በአራም በጌሹር በነበርኩበት ጊዜ፣ ‘እግዚአብሔር በእርግጥ ወደ ኢየሩሳሌም ዳግመኛ የመለሰኝ እንደሆነ በኬብሮን እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስዬ ነበር፡፡” 9 ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ፡፡ 10 አቤሴሎም ግን ወደ መላው የእስራኤል ነገዶች፣ “የመለከትን ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ’ ማለት ይገባችኋል” የሚሉ ሰላዮችን ላከ፡፡ 11 ከአቤሴሎምም ጋር ሁለት መቶ የተጋበዙ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፡፡ አቤሴሎም ምን እንዳቀደ ምንም ነገር ሳያውቁ በየዋህነት ነበረ የሄዱት፡፡ 12 አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ ለሆነው ለአኪጦፌል ወደሚኖርበት ወደ ጊሎ መልእክት ላከበት፡፡ አቤሴሎምን ይከተለው የነበረው ሕዝብ እየጨመረ ስለነበረ የአቤሴሎም ሤራ ጠንካራ ነበር፡፡ 13 “የእስራኤል ሰዎች ልብ አቤሴሎምን እየተከተለ ነው፡፡” የሚል መልእክተኛ ወደ ዳዊት መጣ፡፡ 14 ስለዚህ ዳዊት በኢየሩሳሌም ለነበሩት አገልጋዮቹ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ለመውጣት ተዘጋጁ አለዚያ እርሱ መጥቶ ይይዘናል በእኛም ላይ ጥፋት ያደርስብናል፣ ከተማይቱንም በሰይፍ ይመታታል፡፡” አላቸው፡፡ 15 የንጉሡም አገልጋዮች፣ “እነሆ፣ ጌታችን የወሰነውን ማንኛውንም ለማድረግ አገልጋዮችሀ ዝግጁ ነን” በማለት ለንጉሡ ነገሩት፡፡ 16 ንጉሡ ከእርሱም ጋር መላው ቤተሰቡ ሄዱ፣ ነገር ግን ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁ ዘንድ ቁባቶች የነበሩ አሥር ሴቶችን እንዲቀሩ አደረገ፡፡ 17 ንጉሡና እርሱን ተከትሎ መላው ሕዝብ ከሄደ በኋላ ከመጨረሻው ቤተ ሲደርሱ ቆሙ፡፡ 18 ሠራዊቱ ሁሉ ከእርሱ ጋር ተጓዙ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡት ስድስት መቶ ጌታውያን በንጉሡ ፊት አለፉ፡፡ 19 ከዚያም ንጉሡ ጌታዊውን ኢታይን፣ “አንተ ደግሞ ከእኛ ጋር የመጣኸው ለምንድን ነው? እንግዳና ስደተኛ ነህና ተመልሰህ ሄደህ ከአቤሴሎም ጋር ቆይ፤ ወደ ራስህ አገር ሂድ፡፡ 20 የወጣኸው ገና ትላንት ስለሆነ፣ ከእኔ ጋር በየቦታው ለምን እንድትንከራተት ላድርግህ? ወዴት እንደምሄድ እንኳን አላውቅም፡፡ ስለዚህ ተመለስ የአገርህንም ሰዎች መልሳቸው፤ በጎነትና ታማኝነት ከአንተ ጋር ይሁን፡፡” አለው፡፡ 21 ኢታይ ግን ለንጉሡ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት ንጉሡ ወደሚሄድበት ወደየትኛውም ቦታ አገልጋይህም ይሄዳል፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡ 22 ስለዚህ ዳዊት ለኢታይ፣ “እንግዲያውስ፣ ከእኛ ጋር መሄድህን ቀጥል” አለው፡፡ ከእርሱ ጋር ከነበሩት ሰዎች ሁሉና አብረውት ከነበሩት ቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ጌታዊው ኢታይ ከንጉሡ ጋር ተጓዘ፡፡ 23 ሕዝቡ ሁሉ ንጉሡም ራሱ የቄድሮንን ወንዝ ሲሻገሩ የአገሩ ሕዝብ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ምድረ-በዳ በሚወስደው መንገድ ተጓዘ፡፡ 24 ሳዶቅም እንኳን የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ከተሸከሙት ሌዋውያን ጋር በዚያ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ታቦት አስቀመጡትና አብያታር ከእነርሱ ጋር ሆነ፤ እነርሱም ሕዝቡ ሁሉ ከከተማይቱ እስኪወጡ ድረስ ጠበቁ፡፡ 25 ንጉሡም ሳዶቅን፣ “ታቦቱን ወደ ከተማይቱ ይዘህ ተመለስ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ካገኘሁ ወደዚህ መልሶ ያመጣኛል፣ ታቦቱንና እርሱም የሚኖርበትን ስፍራ እንደገና ያሳየኛል፡፡ 26 ነገር ግን እርሱ፣ ‘በአንተ አልተደሰትሁም’ ካለኝ፣ እነሆ፣ በፊቱ አለሁ፣ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግብኝ፡፡” 27 ንጉሡ ለካህኑ ለሳዶቅ፣ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? አንተ ከሁለቱ ልጆችህ፣ ከልጅህ አኪማአስና ከአብያታር ልጅ ከዮናታን ጋር ሆናችሁ በሰላም ወደ ከተማይቱ ተመለሱ፡፡ 28 ከአንተ ዘንድ መልእክት እስካገኝ ድረስ፣ እነሆ፣ እኔ በአረባ በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቆያለሁ፡፡” 29 ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እዚያው ቆዩ፡፡ 30 ዳዊት ግን እያለቀሰ በባዶ እግሩ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፣ ራሱንም ተከናንቦ ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር የነበረውም እያንዳንዱ ሰው ራሱን ተከናንቦ ነበር፤ እየሄዱም ሳሉ ያለቅሱ ነበር፡፡ 31 አንድ ሰውም ለዳዊት፣ “በሤራው ውስጥ ከአቤሴሎም ጋር ካሉት አንደኛው አኪጦፌል ነው” ብሎ ነገረው፡፡ ስለዚህ ዳዊት፣ “እባክህ፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ የአኪጦፌልን ምክር ወደ ሞኝነት ለውጠው” ብሎ ጸለየ፡፡ 32 ዳዊት እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ወደ መንገዱ ጫፍ በደረሰ ጊዜ፣ አርካዊው ኩሲ መጎናጸፊያውን ቀድዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ፡፡ 33 ዳዊትም ለእርሱ፣ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትህንብኛለህ፤ 34 ነገር ግን ወደ ከተማይቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን ‘ንጉሥ ሆይ፣ አገልጋይህ እሆናለሁ፣ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ አሁን ደግሞ የአንተ አገልጋይ እሆናለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማደናገር ትረዳኛለህ፡፡ 35 ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተ ጋር አሉልህ አይደለምን? በንጉሡ ቤተ መንግሥት የምትሰማውን ማንኛውንም ነገር ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር መንገር አለብህ፡፡ 36 የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን ሁለቱ ወንዶች ልጆች በዚያ አብረዋቸው መሆናቸውን አረጋግጥ፡፡ የምትሰማውን ማንኛውንም ነገር በእነርሱ በኩል ላክልኝ፡፡” 37 ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ኩሲ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት በዚያው ወቅት ወደ ከተማይቱ መጣ፡፡