1 ዳዊት ከተራራው ጫፍ ባሻገር ጥቂት እልፍ ብሎ እንደሄደ ሲባ የተባለው የሜምፊቦስቴ አገልጋይ፣ ሁለት መቶ እንጀራ አንድ ሙሉ ጥፍጥፍ ዘቢብ አንድ መቶ ጥፍጥፍ በለስና አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች ይዞ ተገናኘው፡፡ 2 ንጉሡም ሲባን፣ “ይህን ሁሉ ያመጣኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ሲባም፣ “አህዮቹን የንጉሡ ቤተ ሰቦች እንዲቀመጡባቸው፣ እንጀራውንና በለሱን ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እንዲበሉት፣ የወይን ጠጁ ደግሞ በምድረ-በዳ የደከመ ማንኛውም ሰው እንዲጠጣው ነው” አለው፡፡ 3 ንጉሡም፣ “የጌታህ የልጅ ልጅ የት ነው?” አለው፡፡ ሲባም ለንጉሡ፣ “’ዛሬ የእስራኤል ቤት የአባቴን መንግሥት ለእኔ ይመልስልኛል’ እያለ ስለነበረ፣ እነሆ፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል” ብሎ መለሰለት፡፡ 4 ከዚያም ንጉሡ ሲባን፣ “የሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ፣ እነሆ፣ የአንተ ሆኖአል” አለው፡፡ ሲባም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ በትሕትና በፊትህ እጅ እነሣለሁ፣ በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለው፡፡ 5 ንጉሥ ዳዊት ወደ ብራቂም ሲደርስ ከሳዖል ቤተሰብ ነገድ የሆነ የጌራ ልጅ ሳሚ ብቅ አለ፡ እርሱም እየመጣ ሳለ ይራገም ነበር፡፡ 6 የንጉሡ ወታደሮችና የክብር ዘቦቹ ሁሉ በዳዊትና ግራና ቀኝ ቢኖሩም እንኳን፣ በዳዊትና በሹማምንቱ ላይ ድንጋይ ይወረውርባቸው ነበር፡፡ 7 ሳሚም እንደዚህ ብሎ ተራገመ፣ “ውጣ፣ ከዚህ ውጣ፣ አንተ ወሮበላ፣ አንተ የደም ሰው፤ 8 በእርሱ ምትክ የነገሥህበትን የሳዖልን ቤተሰብ ደም ብድራት ሁሉ እግዚአብሔር እየከፈለህ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንግሥቱን በልጅህ በአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ አሁንም አንተ የደም ሰው ስለሆንክ ጥፋት ደርሶብሃል፡፡” 9 ከዚህ በኋላ የጽሩይ ልጅ አቢሳ፣ “ይህ የሞተ ውሻ ንጉሡ ጌታዬን ለምን ይራገማል? እባክህ፣ ተሻግሬ ልሂድና ራሱን ልቁረጠው” አለ፡፡ 10 ንጉሡ ግን፣ “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እርሱ የሚረግመኝ ምናልባት እግዚአብሔር፣ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት ይሆናል፡፡ ታዲያ እርሱን፣ ‘ንጉሡን ለምን ትረግማለህ?’ ሊለው የሚችለው ማን ነው?” 11 ስለዚህ ዳዊት ለአቢሳና ለአገልጋዮቹ ሁሉ፣ “ከአብራኬ የወጣው ልጄ ነፍሴን ሊያጠፋት ከፈለገ፣ ይህ ብንያማዊ ምን ያህል ጥፋቴን አይፈልግ? እግዚአብሔር እንዲራገም አዞት ይሆናልና፣ ተዉት፣ ይራገም፡፡ 12 ምናልባት የተሰነዘረብኝን ውርደት እግዚአብሔር ተመልክቶ ስለ ዛሬው እርግማኑ በጎ ያደርግልኝ ይሆናል፡፡” 13 ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ በመንገዱ ጉዟቸውን ቀጠሉ፣ ሳሚም በኮረብታው ጥግ ጥግ እየሄደ ድንጋይ ይወረውር አቧራም ይበትንበት ነበር፡፡ 14 ከዚህ በኋላ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ደከሙ፣ እነርሱም ለምሽቱ በሚቆሙበት ጊዜ እርሱ ዕረፍት አደረገ፡፡ 15 አቤሴሎምና ከእነርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ በበኩላቸው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፣ አኪጦፌልም ከእርሱ ጋር ነበረ፡፡ 16 የዳዊት ወዳጅ፣ አርካዊው ኩሲም ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ፣ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ንገሥ! ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ንገሥ!” አለው፡፡ 17 አቤሴሎምም ኩሲን፣ “ለወዳጅህ ያለህ ታማኝነት ይሄ ነው? ለምን ከእርሱ ጋር አልሄድህም?” አለው፡፡ 18 ኩሲም አቤሴሎምን፣ “አይሆንም፣ ይልቁኑ እግዚአብሔርና ይህ ሕዝብ እንዲሁም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ከመረጡት ከእርሱ ጋር ነው እኔ የምሆነው፣ ከእርሱም ጋር እቆያለሁ፡፡ 19 ላገለግለው የሚገባኝ ሰው ማን ነው? በልጁስ ፊት ላገለግል አይገባኝምን? በአባትህ ፊት እንዳገለገልሁ በአንተም ፊት አገለግላለሁ፡፡” 20 ከዚያ በኋላ አቤሴሎም ለአኪጦፌል፣ “ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክርህን ስጠን” አለው፡፡ 21 አኪጦፌልም ለአቤሴሎም፣ “ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ አባትህ ከተዋቸው ቁባቶቹ ጋር ግባና ተኛ፣ ከዚያም አንተ ለአባትህ መጥፎ ጠረን እንዳለው ሰው እንደሆንክበት እስራኤል ሁሉ ይሰማል፤ ከዚያም ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች ሁሉ እጅ ይበረታል፡፡” 22 ስለዚህ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ለአቤሴሎም ድንኳን ተከሉለት፤ አቤሴሎምም መላው እስራኤል እያየው ከአባቱ ቁባቶች ጋር ተኛ፡፡ 23 በዚያን ጊዜ አኪጦፌል ይሰጠው የነበረው ምክር ከእግዚአብሔር ከራሱ አፍ እንደ መስማት ያለ ነበር፡፡ ዳዊትም ሆነ አቤሴሎም ለአኪጦፌል ምክር የነበራቸው ግምት እንደዚህ ነበር፡፡