1 ከዚህ በኋላ አኪጦፌል ለአቤሴሎም፣ “አሥራ ሁለት ሺህ ሰው መርጬ በዛሬይቱ ሌሊት አባትህን አሳድደዋለሁ፤ 2 በደከመውና ዐቅም ባነሰው ጊዜ ድንገት ደርሼ በማስፈራት አስደንቀዋለሁ፤ አብሮት ያለው ሕዝብም ይሸሻል፣ በንጉሡ ላይ ብቻ ጥቃት አደርስበታለሁ፡፡ 3 ሙሽራ ወደ ባሏ እንደምትመጣ ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንተ ሥር በሰላም ይሆናል፡፡” 4 አኪጦፌል የተናገረውም አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኛቸው፡፡ 5 ከዚያ በኋላ አቤሴሎም፣ “አርካዊውን ኩሲን አሁን ጥሩትና እስቲ፣ እርሱ ደግሞ የሚለውን እንስማ” አለ፡፡ 6 ኩሲ ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ፣ አኪጦፌል ያለውን ከገለጸለት በኋላ፣ ኩሲን፣ “አኪጦፌል ያለውን እናድርግ? ካልሆነም የምትመክረንን አንተ ንገረን፡፡” 7 ስለዚህ ኩሱ ለአቤሴሎም፣ “አኪጠፌል በዚህን ጊዜ የሰጠው ምክር መልካም አይደለም፡፡” ካለ በኋላ፣ 8 ኩሲ በመቀጠል፣ “አባትህና ሰዎቹ ብርቱ ተዋጊዎችና ግልገሎቿ በሜዳ እንደተነጠቁባት ድብ መራሮች እንደሆኑ አንተ ታውቃለህ፡፡ አባትህ የጦር ሰው ነው፣ በዛሬው ሌሊት ከሠራዊቱ ጋር አይተኛም፡፡ 9 እነሆ፣ አሁን እንኳ በአንዱ ዋሻ ወይም በሌላ ቦታ ተደብቆ ይሆናል፡፡ በውጊያው መጀመሪያ ላይ ከአንተ ሰዎች ጥቂቶቹ ቢሞቱ፣ ያንን የሰማ ማንኛውም ሰው፣ ‘አቤሴሎምን ይከተሉ በነበሩት ላይ እልቂት ተፈጽሟል’ ይላል፡፡ 10 ከዚያ በኋላ አባትህ ኃያል ሰው ስለሆነና ከእርሱም ጋር ያሉት በጣም ብርቱዎች መሆናቸውን መላው እስራኤል ስለሚያውቅ ልባቸው እንደ አንበሳ ልብ የሆነው እጅግ ጀግና የሆኑት እንኳን ይፈራሉ፡፡ 11 ስለዚህ እኔ የምመክርህ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ የሆነው ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው መላው የእስራኤል ሕዝብ ወደ አንተ ይሰብሰብ፣ አንተም በግልህ ወደ ጦርነቱ ግባ፡፡ 12 ከዚያ በኋላ እርሱ በየትኛውም ቦታ ቢሆን እንመጣበታለን፣ ጤዛም ምድርን እንደሚሸፍን በላዩ ላይ እንወድቅበታለን፡፡ ከእርሱ ማንኛውንም ሰው ወይም እርሱን ራሱንም እንኳን ቢሆን በሕይወት አንተውም፡፡ 13 ወደ አንዲት ከተማ የሚያፈገፍግ እንኳ ቢሆን፣ እስራኤል ሁሉ ገመድ አምጥቶ አንድ እንኳ እስከማይቀር ድረስ ከተማይቱን ወደ ወንዝ ውስጥ ስበን እንከታታለን፡፡” 14 ከዚያም አቤሴሎምና የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ፣ “የአርካዊው ኩሲ ምክር ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የተሻለች ነች” አሉ፡፡ በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ይመጣ ዘንድ እግዚአብሔር የአኪጦፌል መልካም ምክር ተቀባይነት እንዳያገኝ አደረገ፡፡ 15 ከዚያም ኩሲ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር፣ “አኪጦፌል አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው መክሮአቸው ነበር፣ እኔ ግን የተለየ ምክር ሰጠኋቸው፡፡ 16 እንግዲህ እናንተ ፈጥናችሁ ወደ ዳዊት ዘንድ ሂዱና ፣ ‘በአረባ ባለው የወንዙ መሻገሪያ እንዳታድር፣ ነገር ግን እንደ ምንም ብለህ ተሻገር፤ አለበለዚያ ንጉሡና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ትዋጣላችሁ’ በሉት፡፡” 17 በዚህ ጊዜ፣ ዮናታንና አኪማአስ በዓይንሮጌል ባለችው ምንጭ ይጠብቁ ነበር፣ ወደ ከተማ ሲገቡ እንዳይታዩ አንዲት ሴት አገልጋይ ወደ እነርሱ እየሄደች መልእከቶችን ታቀብላቸው ነበር፤ እነርሱም በዚያን ጊዜ ለዳዊት ሄደው ይነግሩት ነበር፡፡ 18 በዚህን ጊዜ ግን አንድ ወጣት አያቸውና ለአቤሴሎም ሄዶ ነገረ፡፡ ስለዚህ ዮናታንና አኪማአስ ፈጥነው በግቢው ውስጥ የውሃ ጉድጓድ ወደነበረው በብራቂም ወደ ነበረ ሰው ቤት መጡ፡፡ 19 የሰውዬው ሚስት የውሃ ጉድጓዱን መሸፈኛ ወስዳ በጉድጓዱ አፍ ላይ ዘረጋችው ከዚያ በኋላም ዮናታንና አኪማአስ በውሃ ጉድጓድ ዘንድ እንዳሉ ማንም እንዳያውቅ በላዩ ላይ እህል አሰጣችበት፡፡ 20 የአቤሴሎም ሰዎች በቤት ወደነበረችው ሴትዮ መጡና፣ “አኪማአስና ዮናታን ወዴት አሉ?” አሏት፤ እርሷም፣ “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል” አለቻቸው፡፡ ስለዚህ ፈልገው ሊያገኟቸው ስላልቻሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ 21 እነርሱ ከሄዱ በኋላ አኪማአስና ዮናታን ከጉድጓዱ ወጡ፤ ወደ ዳዊትም ዘንድ ሄደው፣ “ተነሣና ፈጥነህ ወንዙን ተሻገር፣ ምክንያቱም አኪጦፌል አንተን በሚመለከት እንደዚህና እንደዚያ ብሎ ምክር ሰጥቶአል፡፡” 22 ከዚያ በኋላ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበረው ሕዝብ ተነሡ፣ የዮርዳኖስንም ወንዝ ተሻግረው ሄዱ፤ ሲነጋም ዮርዳኖስን መሻገር አቅቶት የቀረ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ 23 አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተቀበሉት ባየ ጊዜ አህያውን ጭኖ ቤቱ ወዳለበት ወደ መኖሪያ ከተማው ሄደ፣ ጉዳዩንም መልክ ካስያዘ በኋላ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ፡፡ በዚህ አኳኋን ሞተና በአባቱ መቃብር ተቀበረ፡፡ 24 ከዚያ በኋላ ዳዊት ወደ መሃናይም መጣ፤ አቤሴሎምም ከእርሱ ጋር ከነበሩት ከመላው የእስራኤል ሰዎች ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ፡፡ 25 ከዚህ በኋላም አቤሴሎም በኢዮአብ ምትክ አሜሳይን በሠራዊቱ ላይ ሾመ፤ አሜሳይ የእስራኤላዊው የዮቴር ልጅ ነበር፡፡ ዮቴር ከኢዮአብ እናት ከጽሩያ እህት ከናዖስ ልጅ ከአቢግያ ጋር ተኝቶ የነበረ ነው፡፡ 26 ከዚህ በኋላ እስራኤላውያንና አቤሴሎም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ፡፡ 27 ዳዊት ወደ መሃናይም በመጣ ጊዜ ከአሞናውያን ከተማ ከራባ የመጣው፣ የናዖስ ልጅ ሾቢ፣ ከሎዶባር የመጣው የዓሚኤል ልጅ ማኪርና ከሮግሊም የመጣው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ፣ 28 መተኛ ምንጣፎችና ብርድ ልብሶች፣ ጎድጓዳ ሳህኖችና ድስቶች እንዲሁም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ይበሉ ዘንድ ስንዴ፣ የገብስ ዱቄት፣ የተጠበሰ እሸት፣ ባቄላ፣ ምስር፣ 29 ማር፣ ቅቤ፣ በግና እርጎ አመጡ፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ “ሕዝቡ በምድረ-በዳ ተርቦአል፣ ደክሞአል ደግሞም ተጠምቶአል” ብለው ነበር፡፡