1 ዳዊት አብሮት የነበሩትን ወታደሮች ቆጠረ፤ በእነርሱም ላይ የሻለቆችንና የመቶ አለቆችን ሾመላቸው፡፡ 2 ከዚህ በኋላ ዳዊት ሠራዊቱን ሲሦውን በኢዮአብ፣ ሲሦውን በኢዮአብ ወንድም በጽሩይ ልጅ በአቢሳ፣ ሲሦውን ደግሞ በጌታዊው በኢታይ አዛዥነት ሥር ላካቸው፡፡ ንጉሡም ለሠራዊቱ፣ “እኔ ራሴም አብሬአችሁ በእርግጥ እወጣለሁ” አላቸው፡፡ 3 ሰዎቹ ግን፣ “አንተ መውጣት የለብህም፤ እንድንሸሽ ብንገደድ፣ ሰዎቹ ስለ እኛ ግድ አይኖራቸውም ወይም ከእኛ ግማሻችን እንኳን ብንሞት ደንታም የላቸውም፡፡ አንተ ግን ከእኛ ከአሥር ሺሁ ትበልጣለህ፤ ስለዚህ በከተማ ሆነህ ልትረዳን ዝግጁ ብትሆን የተሻለ ነው፡፡” አሉት፡፡ 4 ስለዚህ ንጉሡ፣ “መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህ ሠራዊቱ ሁሉ በመቶና በሺህ እየሆነ ተሰልፎ ሲወጣ ንጉሡ በከተማይቱ ቅጥር በር ቆሞ ነበር፡፡ 5 ንጉሡ ኢዮአብን፣ አቢሳንና ኢታይን፣ “ለእኔ ስትሉ ለወጣቱ ለአቤሴሎም ራሩለት” ብሎ አዘዛቸው፡፡ ሕዝቡ ሁሉ አቤሴሎምን በሚመለከት ንጉሡ ይህንን ትዕዛዝ ለአዛዦቹ ሲሰጣቸው ሰሙ፡፡ 6 ስለዚህ እስራኤልን ይወጋ ዘንድ ሠራዊቱ ከከተማ ወጣ፤ ውጊያውም እስከ ኤፍሬም ደን ተስፋፋ፡፡ 7 በዚያ የእስራኤል ሠራዊት በዳዊት ወታደሮች ድል ሆነ፤ በዚያ ሃያ ሺህ ሰው የሞተበት ታላቅ እልቂት በዚያ ቀን ነበረ፡፡ 8 ውጊያው በገጠሩ ሁሉ ተስፋፋ፣ በሰይፍ ካለቀውም ይልቅ ጫካ ውጦ ያስቀረው ሰው በለጠ፡፡ 9 አቤሴሎም ከዳዊት ሰዎች ከጥቂቶቹ ጋር ተገናኘ፡፡ አቤሴሎምም በበቅሎው እየጋለበ ነበር፤ በቅሎውም ጥቅጥቅ ያሉ ቅርንጫፎች በነበሩት የወርካ ዛፍ ሥር ያልፍ ነበርና ራሱ በዛፉ ቅርንጫፎች ተያዘ፡፡ የተቀመጠበት በቅሎ ከሥሩ አልፎ ሲሄድ እርሱ በሰማይና በምድር ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ 10 አንድ ሰው ይህንን ተመልክቶ፣ “እነሆ፣ አቤሴሎም በወርካ ዛፍ ላይ ተንጥልጥሎ አየሁት” ብሎ ለኢዮአብ ነገረው፡፡ 11 ኢዮአብም ስለ አቤሴሎም ለነገረው ሰው፣ “እነሆ፣ አንተ አየኸው፣ ታዲያ መትተህ ለምን ወደ መሬት አልጣልከውም? እኔ አሥር የብር ሰቅልና ቀበቶ በሸለምኩህ ነበር፡፡” 12 ሰውዬውም ለኢዮአብ፣ “አሥር ሺህ ሰቅል የምቀበል ብሆንም እንኳን እጄን ዘርግቼ የንጉሡን ልጅ ባልነካሁም ነበር፤ ምክንያቱም አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ንጉሡ፣ ‘አንድም ሰው ወጣቱን አቤሴሎምን እንዳይነካው’ ብሎ ሲያዛችሁ ሁላችንም ሰምተናል፡፡ 13 ውሸት በመናገር ሕይወቴን አደጋ ላይ ብጥል እንኳን (ከንጉሡ የሚደበቅ ምንም ነገር አይኖርምና) አንተ ታጋልጠኝ ነበር፡፡” አለው፡፡ 14 ከዚህ በኋላ ኢዮአብ፣ “እኔ አንተን አልጠብቅም” አለ፡፡ ስለዚህ ኢዮአብ ሦስት ጦር ወስዶ ገና በሕይወት እያለና በወርካው ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሳለ በአቤሴሎም ልብ ላይ ተከላቸው፡፡ 15 ከዚያ በኋላም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች አሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት፡፡ 16 ከዚያም ኢዮአብ ቀንደ-መለከቱን ነፋ፣ ኢዮአብም ከልክሏቸው ስለነበረ ሠራዊቱ እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ፡፡ 17 አቤሴሎምን ወስደው በጫካ ውስጥ ወደነበረ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ በሚሸሽበት ጊዜ በአስከሬኑ ላይ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፡፡ 18 አቤሴሎም፣ “የስሜን መታሰቢያ የሚያስጠራ ልጅ የለኝምና” በማለት ገና በሕይወቱ ሳለ ለራሱ አንድ ትልቅ የድንጋይ ሐውልት በንጉሡ ሸለቆ አቁሞ ነበር፡፡ ሐውልቱንም በስሙ ጠርቶት ስለነበረ፣ እስከዚህ ቀን ድረስ ‘የአቤሴሎም ሐውልት’ ተብሎ ይጠራል፡፡ 19 በዚህ ጊዜ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ እግዚአብሔር ከጠላቶቹ እንዳዳነው ሄጄ ለንጉሡ የምሥራች ልንገረው አለ፡፡ 20 ኢዮአብም፣ “ዛሬ የምሥራቹን የምታደርስለት አንተ አይደለህም፣ ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ፤ የንጉሡ ልጅ ስለሞተ ምንም የምሥራች አታደርስም፡፡” 21 ከዚያም ኢዮአብ ለአንድ ኩሻዊ፣ “ሂድና ለንጉሡ ያየኸውን ተናገር” አለው፡፡ ኩሻዊውም ኢዮአብን እጅ ነሥቶ እየሮጠ ሄደ፡፡ 22 የሳዶቅ ልጅ አኪማአስም እንደገና ለኢዮአብ፣ “ምንም ዓይነት ነገር ይሁን፣ እባክህ፣ ኩሻዊውን ተከትዬው ልሩጥ” አለው፡፡ ኢዮአብም፣ “ለየምሥራቹ ምንም ብድራት እንደማታገኝ እያወቅህ፣ ልጄ ሆይ፣ ለምን ትሮጣለህ?” ብሎ መለሰለት፡፡ 23 “የሆነው ይሁን፣ እሮጣለሁ” አለ፣ አኪማአስ፡፡ ስለዚህ ኢዮአብ ፣ “እንግዲያውስ፣ ሩጥ” ብሎ መለሰለት፡፡ ከዚያም አኪማአስ በሜዳው መንገድ በኩል ሮጠ፣ ኩሻዊውንም ቀደመው፡፡ 24 ዳዊት በውስጠኛውና በውጭኛው በሮች መካከል ተቀምጦ ነበር፡፡ ጠባቂው ቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ጣራ ወጥቶ ወደ ውጭ ዓይኑን አንስቶ ሲመለከት አንድ ብቻውን የሚሮጥ ሰው እየተቃረበ ነበር፡፡ 25 ጠባቂው ተጣራና ለንጉሡ ነገረው፤ ከዚያም ንጉሡ፣ “ብቻውን ከሆነ መልካም ዜና በአንደበቱ አለ” አለ፡፡ ሯጩ እየተጠጋ መጥቶ ወደ ከተማይቱ ቀረበ፡፡ 26 ከዚያም ጠባቂው ሌላ የሚሮጥ ሰው አስተዋለ፤ ጠባቂውም ዘበኛውን ጠራና፣ “እነሆ፣ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አለ” አለው፡፡ ንጉሡም፣ “እርሱም መልካም ዜና አለው” አለ፡፡ 27 ስለዚህ ጠባቂው፣ “ከፊት እየሮጠ ያለው ሰው አሯሯጥ የሳዶቅን ልጅ የአኪማአስን ሩጫ ይመስለኛል” አለ፡፡ ንጉሡም፣ “እርሱ ጥሩ ሰው ነው፣ እርሱም የሚመጣው የምሥራች ይዞ ነው” አለ፡፡ 28 ከዚያ በኋላ አኪማአስ ተጣርቶ ለንጉሡ፣ “ሁሉም ደኅና ነው” አለና በንጉሡ ፊት ለጥ ብሎ እጅ ነሥቶ፣ ወደ መሬት እያቀረቀረ፣ “በጌታዬ በንጉሡ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠህ እግዚአብሔር አምላክህ የተባረከ ይሁን” አለው፡፡ 29 ንጉሡም፣ “ወጣቱ አቤሴሎም ደህና ነውን? ሲል ጠየቀ፡፡ አኪማአስም፣ “ኢዮአብ እኔን የንጉሡን አገልጋይ በላከኝ ጊዜ ትልቅ ሁካታ ነበር፣ ምን እንደሆነ ግን እኔ አላወቅሁም” አለው፡፡ 30 ከዚያ በኋላ ንጉሡ፣ “እልፍ በልና ቁም” አለው፡፡ ስለዚህ አኪማአስ እልፍ ብሎ ዝም ብሎ ቆመ፡፡ 31 ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ኩሻዊው ደረሰና፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ የምሥራች አለኝ፣ እግዚአብሔር በንጉሡ ላይ የተነሡብህን ሁሉ ዛሬ ተበቅሎልሃልና” አለው፡፡ 32 ንጉሡም ኩሻዊውን፣ “ወጣቱ አቤሴሎም ደህና ነውን?” አለው፡፡ ኩሻዊውም፣ “የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች እንዲሁም በእርሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ በአንተ ላይ የሚነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ወጣት ይሁኑ” ብሎ መለሰለት፡፡ 33 በዚያን ጊዜ ንጉሡ ጥልቅ የሆነ ሐዘን አዘነ፤ በቅጥሩ በር ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ገብቶም አለቀሰ፡፡ እየሄደም ሳለ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም ልጄ፣ ልጄ!” እያለ ያለቅስ ነበር፡፡