1 “እነሆ፣ ንጉሡ ለልጁ ለአቤሴሎም እያለቀሰ ነው” ተብሎ ለኢዮአብ ተነገረው፡፡ 2 “ንጉሡ ለልጁ እያለቀሰ ነው” የሚለውን ሠራዊቱ በዚያን ቀን ሰምቶ ስለነበረ፣ የዚያን ቀኑ ድል ለሠራዊቱ ወደ ኃዘን ቀንነት ተለወጠ፡፡ 3 ከጦርነት ሸሽተው የሚመጡ በኀፍረት ሹልክ ብለው እንደሚገቡ በዚያን ቀን ወታደሮቹ ሹልክ ብለው ወደ ከተማ ይገቡ ነበር፡፡ 4 ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖና ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፣ አቤሴሎም፣ ልጄ፣ ልጄ!” እያለ አለቀሰ፡፡ 5 ከዚያም ኢዮአብ ወደ ቤት ወደ ንጉሡ ዘንድ ገብቶ፣ “የሚወዱህን ትጠላለህና የሚጠሉህንም ትወዳለህና ዛሬ ሕይወትህን፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሕይወት፣ የሚስቶችህን ሕይወት እንዲሁም የቁባቶችህን ሕይወት ያዳኑትን የወታደሮችህን ሁሉ ፊት አሳፍረሃል፡፡ 6 የሚጠሉህን ትወዳለህ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችና ወታደሮች ለአንተ ምንም እንዳይደሉ ዛሬ አሳይተሃልና፡፡ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት በኖረና እኛ ሁላችንም ብንሞት፣ ያ ደስ ያሰኝህ እንደነበረ አምናለሁ፡፡ 7 ስለዚህ አሁንም ተነሥተህ ውጣና ለወታደሮችህ በትሕትና ተናገራቸው፣ ባትሄድ ግን፣ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ በዛሬው ሌሊት አንድም ሰው ከአንተ ጋር አይቀርም፡፡ ይሄ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ከደረሰብህ መከራ ሁሉ የከፋ ይሆንብሃል፡፡” 8 ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በከተማይቱ በር አጠገብ ተቀመጠ፣ ለሰዎችም ሁሉ፣ “እነሆ፣ ንጉሡ በበሩ ተቀምጦአል” ተብሎ ተነገራቸው፡፡ ከዚያ በኋላም ሰዎች ሁሉ በንጉሡ ፊት መጡ፡፡ በዚህን ጊዜ በእስራኤል ሰው ሁሉ ወደየቤቱ ሸሽቶ ነበር፡፡ 9 በመላው እስራኤል በየነገዱ ያሉ ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው፣ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አስጥሎናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፤ አሁን ደግሞ ከአቤሴሎም ሸሽቶ ከአገር ወጥቷል፡፡ 10 በላያችን ላይ የቀባነውም አቤሴሎም በጦርነቱ ተገድሏል፡፡ ስለዚህ ንጉሡን መልሰን ስለማምጣት ለምን አንነጋገርም?” እያሉ ይነጋገሩ ነበር፡፡ 11 ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር ልኮ፣ “ለይሁዳ ሽማግሌዎች፣ ‘ወደ ቤተ መንግሥቱ ይመልሰው ዘንድ የመላው የእስራኤል ልብ ለንጉሡ ድጋፍ የሚሰጥ ነውና፣ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እናንተ የመጨረሻዎቹ የምትሆኑት ለምንድን ነው? 12 እናንተ የሥጋዬ ቁራጭ የአጥንቴ ፍላጭ ናችሁ፡፡ ታዲያ፣ ንጉሡን ለመመለስ እናንተ የመጨረሻዎቹ የሆናችሁት ለምንድን ነው?’ 13 ለአሜስያም፣ ‘አንተስ የሥጋዬ ቁራጭ የአጥንቴ ፍላጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ ባለደርግህ እግዚአብሔር ይህንን ያድርግብኝ፣ ከዚህም የባሰ ይጨምርብኝ’” በሉ ብሎ መልእክት ላከ፡፡ 14 “አንተና ሰዎችህ ሁሉ ተመለሱ” ብለው ወደ ንጉሡ መልእከት እስኪልኩ ድረስ የአንድ ሰው ልብ እንደነበራቸው ያህል የይሁዳን ሁሉ ልብ ማረከ፡፡ 15 ስለዚህ ንጉሡ ተመልሶ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ የይሁዳም ሰዎች ዮርዳኖስን ሲሻገር ለማጀብ፣ ንጉሡን ለመገናኘት ወደ ጌልጌላ መጡ፡፡” 16 ከብራቂም የሆነው የጌራ ልጅ ሳሚ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ከይሁዳ ሰዎች ጋር ፈጥኖ ወረደ፡፡ 17 ከእርሱ ጋር ከብንያም አንድ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ ደግሞም ከሲባ ከሳዖል አገልጋይ ጋር አሥራ አምስት ልጆቹና ሃያ አገልጋዮቹ ነበሩ፡፡ በንጉሡ ፊት ዮርዳኖስን አቋረጠው ተሻገሩ፡፡ 18 የተሻገሩት የንጉሡን ቤተሰብ ለማምጣትና እርሱ መልካም ነው ያለውን ለማድረግ ነበር፡፡ 19 ሳሚ ለንጉሡ፣ “ጌታዬ እኔን በደለኛ አድርጎ አይቁጠረኝ ወይም ጌታዬ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም በወጣበት ቀን ባሪያህ በግትረኛነት ያደረገውን ትኩረት አይስጠው፡፡ ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ ይህንን በልብህ አታኑረው፡፡ 20 ባሪያህ ኃጢአት ማድረጌን አውቃለሁ፡፡ ከመላው የዮሴፍ ቤት ጌታዬ ንጉሡን ለመቀበል የመጀመሪያ ሆኜ ዛሬ የመጣሁት እነሆ፣ ለዚህ ነው፡፡” አለ፡፡ 21 ነገር ግን የጽሩይ ልጅ አቢሳ፣ “እግዚአብሔር የቀባውን ተራግሟልና ስለዚህ ጉዳይ ሳሚ ሊገደል አይገባውምን?” 22 ከዚያ በኋላ ዳዊት፣ “ዛሬ ለእኔ ጠላቶች ትሆኑኝ ዘንድ እናንተ የጽሩያ ልጆች ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ በእስራኤል አንድ ሰው ሊገደል ይገባዋል? በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁት በዛሬው ቀን አይደለምን?” 23 ስለዚህ ንጉሡ ለሳሚ፣ “አትሞትም” አለው፡፡ ስለዚህ ንጉሡ በመሐላ ቃል ገባለት፡፡ 24 ከዚያ በኋላ የሳዖል ልጅ ሜምፊቦስቴ ንጉሡን ለመቀበል መጣ፡፡ ንጉሡ ከሄደበት ቀን ጀምሮ በሰላም ወደ ቤቱ እስከተመለሰበት ቀን ድረስ በእግሩ ሱሪ አላስገባም፣ ጢሙን አልተላጨም ወይም ልብሱን አላጠበም፡፡ 25 ስለዚህም ንጉሡን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ንጉሡ፣ “ሜምፊቦስቴ ከእኔ ጋር ለምን አልሄድክም?” አለው፡፡ 26 እርሱም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አገልጋዬ አታለለኝ፣ ምክንያቱም፣ ‘እኔ ባሪያህ ሽባ ስለሆንኩኝ እንድቀመጥበትና ከንጉሡ ጋር እንድሄድ አህያዬን እጭናለሁ’ ብዬ ነበርና፡፡ 27 አገልጋዬ ሲባ እኔን ባሪያህን ለጌታዬ ለንጉሡ አማ፤ ጌታዬ ንጉሡ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡ ስለዚህ በዓይንህ ፊት መልካም መስሎ የታየህን አድርግብኝ፡፡ 28 የአባቴ ቤት ሰዎች ሁሉ በጌታዬ በንጉሡ ዘንድ የሞት ሰዎች ነበሩና፤ ነገር ግን ባሪያህን በገበታህ ከሚበሉት አንዱ አድርገህ አስቀመጥኸኝ፡፡ ስለዚህ አሁንም በንጉሡ ፊት ልቅሶዬን ለመቀጠል እኔ ምን መብት አለኝ?” 29 ከዚያ በኋላም ንጉሡ፣ “ከዚህ በላይ መግለጫ መስጠት ምን ያስፈልጋል? እርሻውን አንተና ሲባ እንድትካፈሉት ወስኛለሁ፡፡” 30 ስለዚህ ሜምፊቦስቴ ለንጉሡ፣ “ጌታዬ ንጉሡ ወደ ራሱ ቤት በሰላም ስለመጣ፣ ግድ የለም፣ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው፡፡ 31 ከዚያም ገለዓዳዊው ቤርዜሊ ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን ለመሻገር ከሮግሊም መጣ፣ ንጉሡም ዮርዳኖስን ሲሻገር አጀበው፡፡ 32 ቤርዜሊ ሰማንያ ዓመት የሆነው ሽማግሌ ሰው ነበር፡፡ እጅግ ባለጠጋ ሰው ስለነበረ፣ ንጉሡ በመሃናይም በቆየበት ጊዜ ስንቅ አምጥቶለት ነበር፡፡ 33 ንጉሡም ለቤርዜሊ፣ “ከእኔ ጋር ና፣ እኔ በኢየሩሳሌም የምትመገበውን አቀርብልሃለሁ” አለው፡፡ 34 ቤርዜሊም ለንጉሡ፣ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ዘንድ ከሕይወት ዘመኔ ምን ያህል ቢቀር ነው? 35 እኔ ሰማንያ ዓመቴ ነው፤ መልካሙንና ክፉውን መለየት እችላለሁን? ባሪያህ የሚበላውንስ ሆነ የሚጠጣውን ጣዕም መለየት ይችላልን? የሚዘፍኑ ወንዶችንና የሚዘፍኑ ሴቶችን ከእንግዲህ መስማት እችላለሁን? ስለዚህ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ለምን ሸክም ይሆናል? 36 ባሪያህ የሚፈልገው ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን መሻገር ብቻ ነው፡፡ ንጉሡ ለባሪያው ይህንን ያህል ብድራት ለምን ይከፍለኛል? 37 በአገሬ እሞት ዘንድ፣ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እቀበር ዘንድ፣ እባክህ ወደ አገሬ እንድመለስ ፍቀድልኝ፡፡ ነገር ግን አገልጋይህ ከመዓም ከዚህ አለ፣ እርሱ ከአንተ ጋር ይሻገር፣ የመሰለህን መልካም ነገር አድርግለት፡፡” 38 ንጉሡም፣ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገራል፣ ለአንተም መልካም መስሎ የታየህን አደርግለታለሁ፤ ከእኔም የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር እኔ አደርግልሃለሁ፡፡” 39 ከዚያም ሰዎቹ ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ከዚያም ንጉሡ ተሻገረ፣ ንጉሡም ቤርዜሊን ሳመው ባረከውም፡፡ ከዚህ በኋላ ቤርዜሊ ወደ ራሱ አገር ተመለሰ፡፡ 40 ስለዚህ ንጉሡ ወደ ጌልጌላ ተሻገረ፣ ከመዓምም ከእርሱ ጋር ተሻገረ፡፡ የይሁዳ ሠራዊት ንጉሡንና የእስራኤልን ግማሽ ሠራዊት ይዞ ተመለሰ፡፡ 41 ወዲያውም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጥተው ለንጉሡ፣ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች አንተን ዳዊትንና ቤተሰቡን እንዲሁም የዳዊትን ሰዎች ሰርቀው ዮርዳኖስን አሻግረው ለምን አመጧቸው?” 42 ስለዚህ የይሁዳ ሰዎች ለእስራኤል ሰዎች፣ “ይህንን ያደረግነው ንጉሡ የቅርብ ዘመዳችን ስለሆነ ነው፡፡ ታዲያ እናንተ በዚህ ለምን ትቆጣላችሁ? እኛ የበላነውና ንጉሡ መክፈል ያለበት አንዳች ነገር አለ? ለእኛስ አንዳች ስጦታ ሰጥቶናል?” 43 የእስራኤል ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች፣ “እኛ ከዳዊት ጋር የሚዛመዱ አሥር ነገዶች አሉን፣ ስለዚህ እኛ ከእናንተ ይልቅ በዳዊት ዘንድ መብት አለን፡፡ ታዲያ እናንተ እኛን ለምን ትንቁናላችሁ? ንጉሡን ለማምጣት ያቀረብነው ሃሳብ በመጀመሪያ ሊሰማ የሚገባው አልነበረምን? ነገር ግን የይሁዳ ሰዎች የሰጡት መልስ የእስራኤል ሰዎች ከሰጡት መልስ ይልቅ እጅግ የከረረ ነበር፡፡”