20

1 በዚህ ጊዜ በዚሁ ስፍራ የቢክሪ ልጅ ስሙ ሳቤዔ የተባለ አንድ ችግር ፈጣሪ ብንያማዊ ነበር፡፡ እርሱም መለከት ነፍቶ፣ “እኛ ከዳዊት ጋር ድርሻ የለንም፣ ከእሴይ ልጅም ጋር ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፣ እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ ይመለስ” አለ፡፡ 2 ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዳዊትን ከድተው የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ተከተሉ፡፡ የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ አንስተው እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ንጉሣቸውን አጥብቀው ተከተሉ፡፡ 3 ዳዊት በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መንግሥቱ በመጣ ጊዜ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ትቶአቸው የነበሩትን ዐሥሩን ቁባቶች በአንድ ቤት ውስጥ አስገብቷቸው በአንድ ዘበኛ እንዲጠበቁ አደረገ፡፡ የሚያስፈልጋቸውን አቀረበላቸው፣ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ጋር አልተኛም፡፡ 4 እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ተዘግቶባቸው እንደ መበለት ይኖሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ንጉሡ ለአሜሳይ፣ “በሦስት ቀን ውስጥ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እንዲሰባሰቡ ጥራቸው፣ አንተም እዚህ መገኘት አለብህ” አለው፡፡ 5 ስለዚህ አሜሳይ የይሁዳ ሰዎች እንዲሰባሰቡ ለመጥራት ሄደ፣ ነገር ግን ንጉሡ ካዘዘው ቀነ-ገደብ በላይ ቆየ፡፡ 6 ስለዚህ ዳዊት ለአቢሳ፣ “አሁን የቤክሪ ልጅ ሳቤዔ አቤሴሎም ካደረሰው ይልቅ የባሰ ጉዳት ያደርስብናል፡፡ የጌታህን አገልጋዮች ወታደሮቼን ያዝና አሳደው፣ አለበለዚያ የተመሸጉ ከተሞችን ያገኝና ከዓይናችን ይሰወራል፡፡” አለው፡፡ 7 በዚያን ጊዜ የኢዮአብ ሰዎች ከከሊታውያን ከፈሊታውያን እንዲሁም ከሌሎች ኃያላን ጦረኞች ጋር ተከትለውት ወጡ፡፡ የቤክሪን ልጅ ሳቤዔን ያሳድዱ ዘንድ ከኢየሩሳሌም ወጡ፡፡ 8 ገባዖን ከሚገኘው ታላቅ ዐለት በደረሱ ጊዜ አሜሳይ ሊገናኛቸው መጣ፣ ኢዮአብ በሰገባው ውስጥ የገባ ሰይፍ በወገቡ የታጠቀበትን ቀበቶ የሚያካትት የጦር ሜዳ ልብሱን ለብሶ ነበር፡፡ ወደፊት እየተራመደ ሳለም ሰይፉ ወደቀ፡፡ 9 ኢዮአብም አሜሳይን፣ “ወንድሜ ሆይ፣ ደህና ነህን?” አለው፡፡ ኢዮአብም አሜሳይን እንደሚያፈቅረው አድርጎ ለመሳም ጢሙን ይዞ ሳበው፡፡ 10 አሜሳይ ኢዮአብ በግራ እጁ ይዞት የነበረውን ጩቤ አላስተዋለም፡፡ ኢዮአብ አሜሳይን ሆዱን ወጋው፣ ሆድ-ዕቃውም በምድር ላይ ተዘረገፈ፡፡ ኢዮአብ እንደገና አልወጋውም፣ አሜሳይም ሞተ፡፡ ስለዚህ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ የቤክሪን ልጅ ሳቤዔን አሳደዱ፡፡ 11 ከዚያ በኋላ ከኢዮአብ ሰዎች አንዱ በአሜሳይ አጠገብ ቆመና፣ “ኢዮአብን የሚደግፍና የዳዊት የሆነ ኢዮአብን ይከተል” አለ፡፡ 12 በዚህን ጊዜ አሜሳይ በደም ተጨማልቆ በመንገዱ መካከል ወድቆ ነበር፡፡ ሰዎች ሁሉ ቆመው እንደቀሩ ሰውዬው ተመልክቶ የአሜሳይን ሬሳ ከመንገድ ጎትቶ ወደ እርሻ ውስጥ አስገባው፡፡ ወደ አጠገቡ የደረሰ ማንኛውም ሰው ቆሞ ይቀር እንደነበረ ተመልክቶ ልብስ በላዩ ጣል አደረገበት፡፡ 13 አሜሳይ ከመንገድ ዞር ከተደረገ በኋላ የቤክሪ ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ሰዎች ሁሉ ኢዮአብን ተከተሉ፡፡ 14 ሳቤዔአም በእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል አልፎ ወደ አቤል ቤትማዓካና ተሰባስበው ሳቤዔን ያሳድዱ ወደነበሩት ወደ መላው የቤክሪያውያን ግዛት መጣ፡፡ 15 ደረሱበትና አቤል ቤትመዓካ ላይ ከበቡት፡፡ በከተማይቱም ላይ ግድግዳውን አስጠግተው የአፈር ድልድል ሠሩበት፡፡ ከኢዮአብ ጋር የነበረውም ሠራዊት ግንቡን ለመናድ ደበደበው፡፡ 16 ከዚያ በኋላ አንድ ብልህ ሴት ከከተማ ውስጥ ተጣራችና፣ “ስማኝ፣ እባክህን ስማኝ ኢዮአብ፤ እንዳነጋግርህ ወደዚህ ጠጋ በል” አለችው፡፡ 17 ስለዚህ ኢዮአብ ጠጋ አለ፣ ሴቲቱም፣ “አንተ ኢዮአብ ነህን?” አለችው፡፡ እርሱም፣ “አዎን፣ ነኝ” አለ፡፡ እርሷም ከዚያ በኋላ ለእርሱ፣ “የባሪያህን ቃል ስማ” አለችው፡፡ እርሱም፣ “እየሰማሁ ነው” ብሎ መለሰላት፡፡ 18 ከዚያ በኋላም እርሷ፣ “በቀደሙት ጊዜያት ‘በእርግጥ ምክርን ከአቤል ጠይቅ ምክሩም ችግሮችን ይፈታል’ ይሉ ነበር፡፡ 19 እኛ በእስራኤል ውስጥ እጅግ ሰላማዊና ታማኝ ከሆኑት ከተሞች አንዱ ነን፡፡ በእስራኤል ውስጥ እናት የሆነችውን ከተማ ለማጥፋት እየሞከርክ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ርስት ለምን ለመዋጥ ትፈልጋለህ?” 20 ስለዚህ ኢዮአብ፣ “መዋጥ ወይም ማጥፋት ከእኔ የራቀ ይሁን፣ 21 ያ እውነት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከኮረብታማው ከኤፍሬም አገር የሆነ ሳቤዔ የተባለ የቤክሪ ልጅ እጁን በንጉሡ ላይ ፣ በዳዊት ላይ አንስቷል፤ እርሱን ብቻ አሳልፋችሁ ስጡኝ፣ ከተማውን ለቅቄ እወጣለሁ” ብሎ መለሰላት፡፡ ሴቲቱም ለኢዮአብ፣ “ራሱ በቅጥሩ ላይ ይወረወርልሃል” አለችው፡፡ 22 ከዚያም ሴቲቱ በጥበብዋ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ሄደች፡፡ የቤክሪን ልጅ የሳቤዔን ራስ ቆርጠው በቅጥሩ ላይ ለኢዮአብ ወረወሩለት፡፡ እርሱም ቀንደ-መለከቱን ነፋ፣ የኢዮአብም ሰዎች ከተማይቱን ለቀው እያንዳንዱ ሰው ወደየቤቱ ሄደ፡፡ 23 በዚህን ጊዜ ኢዮአብ በሠራዊቱ ሁሉ ላይ የበላይ ነበር፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ደግሞ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ አለቃ ሆነ፡፡ 24 አዶኒራም በግዳጅ ሥራ ላይ ለተሰማሩት አለቃ ሆነ፣ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ደግሞ ታሪክ ጸሐፊ ሆነ፤ 25 ሱሳ ጸሐፊ፣ ሳዶቅና አብያታር ካህናት ነበሩ፤ 26 እንዲሁም የኢያዕር ሰው ዒራስ የዳዊት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነ፡፡