21

1 በዳዊት ዘመን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ራብ ሆነ፣ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ፈለገ፡፡ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “ሳዖልና ገዳይ ቤተሰቡ ገባዖናውያንን እንዲሞቱ ስላደረገ ይህ ረሃብ በአንተ ላይ ነው” አለ፡፡ 2 እንግዲህ ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ የእስራኤል ሕዝብ ወገን አልነበሩም፡፡ የእስራኤል ሕዝብ እንደማይገድሏቸው ምለውላቸው ነበር፣ ሳዖል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ ከነበረው ቅናት የተነሣ እንዲሁ ሁሉንም የመግደል ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ 3 ስለዚህ ዳዊት ገባዖናውያንን በአንድነት ጠራቸውና፣ “ምን ላደርግላችሁ? የእርሱን በጎነትና ተስፋ ቃሉን የሚወርሱትን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ትባርኩ ዘንድ ስርየትን እንዴት ማድረግ እችላለሁ?” አላቸው፡፡ 4 ገባዖናውያንም፣ “በእኛና በሳዖል ወይም በቤተሰቡ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ በእስራኤልም ውስጥ ማንም ሰው እንየዲገደል የምናደርግ እኛ አይደለንም፡፡” ብለው መለሱለት፡፡ ዳዊትም፣ “የምትጠይቁትን ማንኛውንም ነገር ቢሆን እኔ ያንን አደርግላችኋለሁ” አላቸው፡፡ 5 እነርሱም ለንጉሡ፣ “እንድንጠፋና በእስራኤል ክልል ውስጥ ምንም ስፍራ እንዳይኖረን ሁላችንንም ለመግደል ሙከራ ካደረገውና በእኛ ላይ ሤራ ካውጠነጠነው 6 ከእርሱ ዝርያዎች ሰባት ሰዎች ለእኛ ተላልፈው ይሰጡን እኛም በእግዚአብሔር በተመረጠው በሳዖል አገር በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንሰቅላቸዋለን” አሉት፡፡ ስለዚህ ንጉሡ፣ “እነርሱን እሰጣችኋለሁ” አላቸው፡፡ 7 ንጉሡ ግን በእርሱና በሳዖል ልጅ በዮናታን ስለነበረው የእግዚአብሔር መሐላ የሳዖልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነው፡፡ 8 ነገር ግን ንጉሡ የኢዩሄል ልጅ ሪጽፋ ለሳዖል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ወሰዳቸው፣ በተጨማሪም ዳዊት የሳዖል ልጅ ሜልኮል ለመሓላታዊው ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን አምስት ወንዶች ልጆች ወሰዳቸው፣ 9 በገባዖናውያንም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም በተራራው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ሰቀሏቸው፣ ሰባቱም አንድ ላይ ሞቱ፡፡ የተገደሉት በመከራ ወቅት፣ የገብስ መከር በሚሰበሰብባቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት ነበረ፡፡ 10 ከዚያ በኋላ የኢዩሄል ልጅ ሪጽፋ ከመከር መሰብሰብ ጊዜ ጀምሮ ዝናብ በእነርሱ ላይ እስኪወርድባቸው ድረስ በአስከሬኖቹ አጠገብ ባለው ተራራ ለራሷ ማቅ ወስዳ ዘረጋች፡፡ የሰማይ ወፎች በቀን፣ የዱር አራዊት በማታ እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፡፡ 11 የሳዖል ቁባት የኢዩሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችው ለዳዊት ተነገረው፡፡ 12 ስለዚህ የሳዖልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ሳዖልን በጊልቦዓ ከገደሉት በኋላ ሰቅለውት ከነበረበት ከቤትሻን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ዘንድ ዳዊት ሄዶ አመጣ፡፡ 13 ዳዊት ከዚያ ስፍራ የሳዖልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት እንዲሁም በዚያ የተሰቀሉትን የሰባት ሰዎች አጥንትም ሰብስቦ ወሰደ፡፡ 14 የሳዖልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩአቸው፡፡ ንጉሡም ያዘዘውን ነገር ሁሉ አከናወኑ፡፡ ከዚያ በኋላ ለምድሪቱ የተደረገውን ጸሎት እግዚአብሔር መለሰ፡፡ 15 ከዚያ በኋላ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር እንደገና ውጊያ ገጠሙ፡፡ ስለዚህ ዳዊት ከሠራዊቱ ጋር ወርዶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፡፡ ዳዊት በጦርነቱ የሰውነት መዛል አጋጠመው፡፡ 16 የኃላኑ ዝርያ የነበረውና የናስ ጦሩ ሦስት መቶ ሰቅል የሚመዝነው እንዲሁም አዲስ ሰይፍ የታጠቀው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ለመግደል አቀደ፡፡ 17 ነገር ግን የጽሩይ ልጅ አቢሳ ፍልስጥኤማዊውን ወግቶ በመግደል ዳዊትንም ታደገው፡፡ ከዚያ በኋላም የዳዊት ሰዎች፣ “የእስራኤል መብራት እንዳታጠፋ ከእንግዲህ አንተ ከእኛ ጋር መውጣት የለብህም” ብለው ማሉለት፡፡ 18 ከዚህ በኋላ ጎብ በተባለ ስፍራ የራፋይም ዝርያ የነበረው ኩስታዊው ሴቦካይ ሳፋንን የገደለበት ጦርነት ከፍልስጥኤማውያን ጋር እንደገና ተደረገ፡፡ 19 ጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገ ጦርነት የቤተልሔሙ የየዓሬዓርጊም ልጅ ኤልያናን የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለ፡፡ 20 ጋዛ ላይ በተደረገ ሌላ ጦርነት በእጆቹ ላይ ስድስት ስድስት ጣቶች በእግሮቹም ላይ ስድስት ጣቶች ባጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት ታላቅ ቁመት የነበረው ሰው ነበር፡፡ እርሱም የራፋይም ዝርያ ነበር፡፡ 21 እርሱም በእስራኤል ላይ ባፌዘ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው፡፡ 22 እነዚህ የጋዛዋ ራፋይም ዝርያዎች ነበሩ፣ እነርሱም በዳዊት እጅና በወታደሮቹ እጅ ተገደሉ፡፡