1 እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳዖል እጅ በታደገው ጊዜ፣ ዳዊት በዚህ መዝሙር ያሉትን የቅኔ ቃላት ለእግዚአብሔር ዘመረ፡፡ 2 እንዲህም እያለ ጸለየ፣ “እግዚአብሔር ዐለቴ፣ አምባዬና ታዳጊዬ ነው፡፡ 3 እግዚአብሔር የምጠጋበት ዐለቴ፣ ጋሻዬና የድነቴ ቀንድ ነው፡፡ እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፣ መጠጊዬና ከግፍ የሚያድነኝ ነው፡፡ 4 ሊመሰገን የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ፡፡ 5 የሞት ማዕበል ከበበኝ፤ የከንቱነት ጎርፍም አጥለቀለቀኝ፡፡ 6 የሲዖል ገመድ ተጠመጠመብኝ፣ የሞትም ወጥመድ አጥምዶ ያዘኝ፡፡ 7 በጨነቀኝ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፣ አምላኬን ጠራሁት፣ ከመቅደሱ ድምፄን ሰማኝ፤ ለረድኤት ያደረግሁት ጥሪም ወደ ጆሮው ደረሰ፡፡ 8 በዚያን ጊዜ ምድር ተንቀጠቀጠች እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበረና የሰማይ መሠረቶች ተናወጡ ተንቀጠቀጡም፡፡ 9 ከአፍንጫው ጢስ፣ ከአፉም ፍሙን የሚያግል የሚንበለበል እሳት፡፡ 10 ሰማይን ከፍቶ ወረደ፣ ድቅድቅ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበር፡፡ 11 በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፣ በንፋስም ክንፍ ተቀምጦ ሲበር ታየ፡፡ 12 በሰማይ ላይ ያሉ ከባድ የዝናብ ደመናዎችን በማሰባሰብ ጨለማን እንደ ድንኳን እንዲከበው አደረገ፡፡ 13 በፊቱ ካለው ነጎድጓድ የእሳት ፍም ወረደ፡፡ 14 እግዚአብሔር ከሰማይ አንጎደጎደ፣ የልዑልም ድምፅ አስተጋባ፡፡ 15 ፍላፃውን ወረወረ ጠላቶቹንም በተነ - መብረቁ እንዲበርቅ አደረገ፣ በታተናቸውም፡፡ 16 በዚያን ጊዜ የውሃ መውረጃዎች ታዩ፣ እግዚአብሔር ባስተጋባው የክተት ድምፅ፣ ከአፍንጫው በሚወጣ የእስትንፋስ ግፊት የምድር መሠረቶች ተጋለጡ፡፡ 17 ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፣ እየተንዶለዶለ ካለውም ውሃ አወጣኝ፡፡ 18 ብርቱ ከሆነው ጠላቴ፣ ከሚጠሉኝም ታደገኝ፣ በእኔ ላይ እጅግ በርትተውብኝ ነበርና፡፡ 19 በጭንቀቴ ጊዜ መጡብኝ፣ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ፡፡ 20 እርሱም ሰፋ ወዳለ ስፍራ አወጣኝ፡፡ በእኔ ደስ ተሰኝቶ ነበርና አዳነኝ፡፡ 21 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን ብድራትን ከፍሎኛል፣ እንደ እጄም ንጽሕና መጠን ወደ ስፍራዬ መልሶኛል፡፡ 22 የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፣ ከአምላኬም ዞር በማለት ክፋትን አላደረግሁም፡፡ 23 የጽድቅ ሥርዓቱ በፊቴ ናቸውና፣ ከድንጋጌም ፈቀቅ አላልሁም፡፡ 24 ቅንነቴን በፊቱ ጠብቄ ነበርና፣ ራሴንም ከኃጢአት አርቄ ነበር፡፡ 25 ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ ጽድቅ ደረጃዬ፣ በፊቱ ካለኝ የንፅሕና አቋሜ መልሶኛል፡፡ 26 ታማኝ ለሆነው ታማኝነትህን ታሳያለህ፣ ነቀፋ ለሌለበትም ሰው ነቀፋ የሌለብህ መሆንህን ታሳያለህ፡፡ 27 ከንጹሖች ጋር ንጹሕ መሆንህን ስታሳይ ለተጣመሙት ግን ጠማማ ነህ፡፡ 28 የተጎሳቆሉትን ታድናለህ፣ ዐይኖችህ ግን በትዕቢተኞች ላይ ነው፣ ታዋርዳቸውማለህ፡፡ 29 እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ መብራቴ ነህና፣ እግዚአብሔር ጨለማዬን ያበራል፡፡ 30 በአንተ መሰናክሉን ጥሼ አልፋለሁ፣ በአምላኬ ቅጥሩን እዘላለሁ፡፡ 31 የእግዚአብሔር መንገድማ ፍጹም ነው፣ የእግዚአብሔር ቃል ንፁሕ ነው፡፡ ወደ እርሱ ለሚጠጋ ለማንኛውም ሰው ጋሻ ነው፡፡ 32 ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው? 33 እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነው፣ ነቀፋ የሌለበትንም ሰው በመንገዱ ይመራዋል፡፡ 34 እንደ ዋላ እግሮች እግሮቼን ፈጣን ያደርጋቸዋል፣ በተራራም ላይ ያቆመኛል፡፡ 35 እጆቼን ለውጊያ፣ ክንዴንም የናስ ቀስት ለመለጠጥ ያሠለጥናቸዋል፡፡ 36 የድነትን ጋሻ ሰጥተኸኛል፣ ሞገስህም ታላቅ አድርጎኛል፡፡ 37 በእግሮቼ ሥር ያለውን ስፍራ ሰፊ አድርገህልኛል፣ ስለዚህ እግሮቼ አልተንሸራተቱም፡፡ 38 ጠላቶቼን አሳደድኋቸው፣ አጠፋኋቸውም፡፡ እስካጠፋቸውም ድረስ አልተመለስሁም፡፡ 39 ፈጽሜ አጠፋኋቸው፣ አደቀቅኋቸውም፣ ተመልሰው መነሣት አይችሉም፡፡ በእግሬ ሥር ወድቀዋል፡፡ 40 እንደ ጦር መታጠቂያ ኃይልን በእኔ ላይ አደረግህ፣ በላዬ ላይ የተነሡትንም ከእኔ በታች አደረግኸቸው፡፡ 41 የጠላቶቼን ማጅራት ሰጠኸኝ፣ የሚጠሉኝንም አፈራረስኳቸው፡፡ 42 ዕርዳታ ለማግኘት ተጣሩ ነገር ግን ማንም አላዳነቸውም፣ ወደ እግዚአብሔር ተጣሩ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም፡፡ 43 እንደ አቧራ መሬት ላይ ፈጨኋቸው፣ በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃም ረገጥኋቸው፡፡ 44 ከራሴ ሕዝብ ክርክር አድነኸኛል፣ የሕዝቦችም ራስ አድርገህ አጽንተኸኛል፣ የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል፡፡ 45 ባዕድ ሕዝቦች ለእኔ ለመስገድ ተገደዱ፣ ስለ እኔ እንደሰሙ ወዲያውኑ ታዘዙኝ፡፡ 46 ባዕዳን ከምሽጋቸው እየተንቀጠቀጡ ወጡ፡፡ 47 እግዚአብሔር ሕያው ነው! ዐለቴ የተመሰገነ ይሁን፣ የድነቴ ዐለት እግዚአብሔር ከፍ ይበል፡፡ 48 በቀልን የሚበቀልልኝ፣ ሕዝብንም ከእኔ ሥር የሚያደርግልኝ አምላክ ይሄ ነው፡፡ 49 ከጠላቶቼ ነፃ ያወጣኛል፡፡ እንዲያውም በእኔ ላይ ከተነሡት በላይ አውጥተኸኛል፡፡ ከግፍኞች ታድገኸኛል፡፡ 50 ስለዚህ እግዚብሔር ሆይ፣ በሕዝቦች መካከል ለአንተ ምስጋና አቀርባለሁ፣ ለስምህም ምስጋና መዝሙር እዘምራለሁ፡፡ 51 እግዚአብሔር ለንጉሡ ታላቅ ድልን ይሰጠዋል፣ ኪዳናዊ ታማኝነቱን እርሱ ለቀባው፣ ለዳዊትና ለዘሮቹ ለዘላለም ያሳየዋል፡፡”