1 እነዚህ ተወዳጁ የእስራኤል ዘማሪ፣ በያዕቆብ አምላክ የተቀባው፣ እጅግ የተከበረው፣ የእሴይ ልጅ የዳዊት የመጨረሻ ቃሎች ናቸው፡፡ 2 የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፣ ቃሉም በምላሴ ላይ ነበረ፡፡ 3 የእስራኤል አምላክ ተናገረ፣ የእስራኤልም ዐለት እንደዚህ አለኝ፣ “ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፣ በፈሪሀ-እግዚአብሔር የሚያስተዳድር፣ 4 እርሱ ከዝናብ በኋላ ብሩሕ በሆነው የፀሐይ ብርሃን ከምድር እንደሚበቅል ለምለም ሣር፣ ደመና የሌለባት ፀሐይ ጥዋት ስትወጣ እንደሚፈነጠቅ የማለዳ ብርሃን ነው፡፡ 5 በእርግጥ የእኔ ቤተሰብ በእግዚአብሔር ፊት እንደዚህ አይደለምን? ከእኔስ ጋር ሥርዓት ያለውና በሁሉም መንገድ እርግጠኛ የሆነ የዘላለም ቃል ኪዳን አልገባምን? ድነቴን ከፍ ከፍ አድርጎ፣ ማንኛውንም ፍላጎቴን አይፈጽምልኝምን? 6 ነገር ግን በእጅ ሊሰበሰቡ ስለማይችሉ ሁላቸውም እንደሚጣሉ እሾሆች ከንቱዎች ናቸው፡፡ 7 እነርሱን የሚነካ የብረት መሣሪያ መጠቀም ወይም የጦር ዘንግ መያዝ ስላለበት ባሉበት መቃጠል ይገባቸዋል፡፡” 8 የዳዊት ምርጥ ወታደሮች ስም የሚከተለው ነው፡- የታህክሞን ሰው ዮሴብ የሦስቱ አለቆች አለቃና በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰዎችን የገደለ ነው፡፡ 9 ከእርሱ ቀጥሎ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፣ እርሱም ከሦስቱ ኃያላን ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ እርሱም ጦርነት ለመግጠም የተሰባሰቡ ፍልስጥኤማውያን በተገዳደሩ ጊዜና የእስራኤልም ሰዎች ባፈገፈጉ ጊዜ በዚያ ነበር፡፡ 10 ኤልኤዘር እስኪዝልና እጁ ከሰይፉ ጋር ተጣብቆ እስኪቀር ድረስ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ቆሞ ተዋጋ፡፡ የዚያን ቀን እግዚአብሔር ታላቅ ድል አስገኘ፡፡ ከኤልኤዘር በኋላ ሠራዊቱ የተመለሰው አስከሬኖቹን ለመግፈፍ ብቻ ነበር፡፡ 11 ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፡፡ ፍልስጥኤማውያኑ የምስር እርሻ በነበረበት ተሰብስበው ሳሉ ሠራዊቱ ከ እነርሱ ሸሸ፡፡ 12 ሣማ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ተቋቋማቸው ፍልስጥኤማዊውንም ገደለው እግዚአብሔርም ታላቅ ድል ሰጣቸው፡፡ 13 ከሰላሳዎቹ ወታደሮች ሶስቱ በመከር ጊዜ ወደ አዶላም ዋሻ ወደ ዳዊት ዘንድ ሄዱ፡፡ የፍልስጥኤም ሠራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍረው ነበር፡፡ 14 በዚያን ጊዜ ዳዊት በአንድ ዋሻ በምሽጉ ውስጥ ሲሆን ፍልስጥኤማውያን ግን በቤተልሔም ተደራጅተው ነበር፡፡ 15 ዳዊትም ውሃ ተጠምቶ፣ “በበሩ አጠገብ ካለችው ጉድጓድ የምጠጣውን ውሃ ምነው አንድ ሰው በሰጠኝ!” አለ፡፡ 16 ስለዚህ እነዚህ ሶስቱ ኃያላን ፍልስጥኤማውያንን ጥሰው አልፈው በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ቀዱ፡፡ ውሃውንም ይዘው ለዳዊት አመጡለት፣ እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈቀደ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው፡፡ 17 ከዚያ በኋላም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህንን እጠጣው ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉ ሰዎችን ደም ልጠጣ ይገባኛልን?” ከዚህም የተነሣ ሊጠጣው አልፈቀደም፡፡ ሶስቱ ኃያላን ያደረጓቸው ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡ 18 የኢዮአብ ወንድምና የጽሩያ ልጅ አቢሳ የሶስቱ አለቃ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከሶስት መቶዎቹ ጋር በጦሩ ተዋግቶ ገደላቸው፡፡ ከሶስቱ ወታደሮች ጋር በተያያዘ ብዙውን ጊዜ ስሙ ይጠቀሳል፡፡ 19 እርሱ ከእነርሱም ይልቅ ዝነኛ አልነበረምን? እርሱ የሶስቱ አለቃ ሆኖ ተሾመ፡፡ ይሁን እንጂ የእርሱም ዝና ከሶስቱ እጅግ ዝነኛ ከነበሩት ወታደሮች ጋር የሚስተካከል አልነበረም፡፡ 20 የቀብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ታላቅ ጀብዱ የሠራ ጠንካራ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም ሁለቱን የአርኤል ልጆች ገደለ፡፡ በረዶ በጣለበትም ወቅት በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሎአል፡፡ 21 ደግሞም አንድ ግዙፍ ግብፃዊም ገድሎአል፡፡ ግብፃዊው በእጁ ጦር የያዘ ቢሆንም በናያስ በትር ብቻ ይዞ ገጠመው፡፡ ጦሩን ከግብፃዊው እጅ ቀምቶ በራሱ ጦር ገደለው፡፡ 22 በናያስ እነዚህን ጀብዱዎች ፈጸመ ከሶስቱም ኃያላን ጋርም ስሙ የተጠራ ሆነ፡፡ 23 በአጠቃላይ ከነበሩት ሰላሳ ወታደሮች ይልቅ ከፍ ያለ ግምት የተሰጠው ነበረ፣ ሆኖም የሶስቱ እጅግ ምርጥ ወታደሮችን ያህል ታላቅ ግምት የተሰጠው አልነበረም፡፡ ሆኖም ዳዊት የክቡር ዘበኞቹ አለቃ አደረገው፡፡ 24 ሰላሳዎቹ የሚከተሉትን ያካተተ ነበር፣ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣ የቤተልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣ 25 አሮዳዊው ሣማ፣ አሮዳዊው ኤሊቃ፣ 26 ፈሊጣዊው ሴሌስ፣ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ፣ 27 ዓኖቶታዊው አቢዔዜር፣ ኩስታዊው ምቡናይ ፣ 28 አሆሃዊው ጸልሞን፣ ነጦፋዊው ማህራይ፣ 29 የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፣ ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፣ 30 ጲርዓቶናዊው በናያስ፣ የገዓስ ሸለቆ ሰው ሂዳይ፣ 31 ዓረባዊው አቢዔልቦን፣ በርሑማዊው ዓዝሞት፣ 32 ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣ የአሳን ልጆች፤ ዮናታን የተባለው፣ 33 የአሮዳዊው የሣማ ልጅ፣ የአሮዳዊው የሻራር ልጅ አሒአም፣ 34 የማዕካታዊው የአሐሰባይ ልጅ ኤልፋላት፣ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊኦም፣ 35 ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፣ አርባዊው ፈዓራይ፣ 36 የሱባ ሰው የሆነው የናታን ልጅ ይግዓል፣ 37 አሞናዊው ጻሌቅ፣ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጦር መሣሪያ ያዥ የነበረው ብኤሮታዊው ነሃራይ፣ 38 ይትራዊው ዔራስ ፣ ይትራዊው ጋሬብ፣ 39 እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮ፤ በጠቅላላው ሠላሳ ሰባት ነበሩ፡፡