1 ዳርዮስ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ እንዲገዙ አንድ መቶ ሃያ መሳፍንትን መሾም ፈለገ፤ 2 በእነዚህም ላይ ሦስት የበላይ አስተዳዳሪዎችን አደረገ፣ ከእነርሱም አንዱ ዳንኤል ነበረ። ንጉሡ ጉዳት እንዳይደርስበት መሳፍንቱ ተጠሪነታቸው ለሦስቱ የበላይ አስተዳዳሪዎች እንዲሆን ተደረገ። 3 ከመሳፍንቱና ከበላይ አስተዳዳሪዎቹ ሁሉ ይልቅ ዳንኤል ልዩ የጥበብ መንፈስ የሞላበት ሆኖ በመገኘቱ፣ ንጉሡ በመላው ግዛቱ ላይ ሊሾመው አሰበ። 4 በዚህ ምክንያት የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ ዳንኤል በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ እንከን ለማግኘት ፈለጉ፤ ነገር ግን ዳንኤል ታማኝ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት ስለነበር በእርሱ ላይ ስህተት ሊያገኙ አልቻሉም። 5 እነዚህም ሰዎች፣ “ከአምላኩ ሕግ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ ይህን ሰው የምንከስበት ምንም ሰበብ አናገኝበትም” አሉ። 6 ከዚያም የበላይ አስተዳዳሪዎቹና አሳፍንቱ ዕቅድ ካወጡ በኋላ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! 7 ንጉሥ ሆይ፤ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያወጣ ትእዛዙም እንዲፈጸም፤ ይህንም የተላለፈ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል፣ የመንግሥት የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማካሪዎችና አገረ-ገዦች ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል፤ 8 ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዐዋጅ አውጣ፤ እንደማይሻረውና እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንዲሆን ትእዛዙን በጽሑፍ አድርገው።” 9 ስለዚህ ንጉሡ ዳርዮስ ዐዋጁ ተጽፎ እንዲወጣ አደረገ። 10 ዳንኤልም ዐዋጁ እንደወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹን በኢየሩሳሌም አንፃር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ አምላኩንም አመሰገነ። 11 ሰዎቹም በአንድ ላይ ሄደው ዳንኤልን ሲጸልይና አምላኩን ሲማጸን አገኙት። 12 ወደ ንጉሡም ሄደው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ በሚቀጥሉት ሠላሳ ቀናት ማንም ሰው ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደ ሰውም ሆነ ወደ ማንኛውም አምላክ ቢጸልይ በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ አልነበረምን?” ሲሉ እርሱ ስላወጣው ዐዋጅ ጠየቁት። ንጉሡም፤ “ዐዋጁ እንደማይሻረው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጸና ነው” ሲል መለሰ። 13 እርሱም ንጉሡን፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት። 14 ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልንም ከዚህ ትእዛዝ የሚያድንበትን መንገድ አሰላሰለ፤ ፀሐይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ። 17 ድንጋይ አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተፈጸመው እንዳይለወጥ በራሱ የቀለበት ማሕተምና በመሳፍንቱ ቀለበቶች አተመበት። 18 ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ በዚያም ሌሊት ምግብ ሳይበላ፣ የሚያዝናናውም ነገር ሳይቀርብለት ዐደረ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ። 19 በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፣ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ እየተጣደፈ ሄደ። 20 ወደ ጉድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ጠየቀው። 21 ዳንኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ 22 ንጉሥ ሆይ፤ በፊቱ ቅን ሆኜ ስለተገኘሁ፣ በአንተም ፊት በደል ስላልተገኘብኝ አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልጎዱኝም።” 24 በንጉሡ ትእዛእ ዳንኤልን የከሰሱት ሰዎች ተይዘው እንዲመጡ ተደረገ፤ እነርሱም ተይዘው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በአንበሶቹ ጉድጓድ ውስጥ ተጣሉ። ወደ ጉድጓዱም መጨረሻ ገና ሳይደርሱ አንበሶቹ ቦጫጩቋቸው፤ ዐጥንቶቻቸውንም ሁሉ ሰባበሩ። 25 ከዚያ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ እንዲህ የሚል መልእክት ጻፈ፤ “ሰላም ይብዛላችሁ! 26 በማንኛውም የመንግሥቴ ግዛት ሰው ሁሉ፣ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር ይህን ዐዋጅ አውጥቻለሁ። “እርሱ ለዘላለም የሚኖር ሕያው አምላክ ነውና መንግሥቱም አይጠፋም፤ ለግዛቱም መጨረሻ የለውም 27 እርሱ ይታደጋል፣ ያድናልም በሰማይና በምድር ምልክቶችንና ድንቆችን ያደርጋል ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ አድኖታል። 28 ስለዚህ ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ ዘመነ መንግሥት ሁሉ ኑሮው ተሳካለት።