1 ንጉሡ ናቡከደነፆር ርዝመቱ ስድሳ ክንድ ስፋቱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ። በባቢሎንም ክፍለ አገር በዱራ ሜዳ አቆመው። 2 ከዚያም ናቡከደነፆር አማካሪዎችን፥ የግምጃ ቤት ኃላፊዎችን፥ ዳኞችን፥ የአጥቢያ ፈራጆችንና የክፍላተ አገር ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትን ሁሉ ጨምሮ የክፍለ አገር አስተዳዳሪዎች፥ የክልል አስተዳዳሪዎችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ላቆመው ምስል ምረቃ እንዲመጡ፥ በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡ መልእክት ላከ። 3 በዚያን ጊዜም አማካሪዎችን፥ የግምጃ ቤት ኋላፊዎችን፥ ዳኞችን፥ የአጥቢያ ፈራጆችንና የክፍላተ አገር ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትን ጨምሮ የክፍለ አገር አስተዳዳሪዎች፥ የክልል አስተዳዳሪዎችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ በአንድነት ተሰበሰቡ። በፊቱም ቆሙ። 4 ከዚያም አዋጅ ነጋሪ እየጮኽ እንዲህ አለ፡- «አሕዛብ፥ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሁሉ፥ 5 የመለከትና የእንቢልታ፥ የመስንቆና የክራር፥ የበገናና የዋሽንት፥ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ወድቃችሁ እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል። 6 ማንም የማይወድቅና የማይሰግድ፥ በዚያው ጊዜ በሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።» 7 ስለዚህም አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመስንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን፥ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ አሕዛብ ሁሉ፥ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ወድቀው ሰገዱ። 8 በዚህ ጊዜም አንዳንድ ከለዳውያን መጥተው አይሁድን ከሰሱ። 9 ለንጉሡ ናቡከደነፆርም እንዲህ አሉ፦ «ንጉሥ ሆይ ለዘላለም ኑር! 10 ንጉሥ ሆይ፥አንተ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመስንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን፥ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ የሰማ ማንኛውም ሰው ለወርቁ ምስል እንዲውድቅና እንዲሰግድ ትዕዛዝ አውጥተህ ነበር። 11 ማንም ያልወደቀና ያላመለከ በሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ውስጥ ሊጣል ይገባዋል። 12 አሁን ግን በባቢሎን ክፍለ አገር ጉዳይ ላይ የሾምካቸው፥ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ የሚባሉ አንዳንድ አይሁድ አሉ። ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች አንተን ከምንም አይቆጥሩም። አማልክትህን አያመልኩም፥ አያገለግሉምም ወይም ላቆምከው የወርቁ ምስል አይሰግዱም።» 13 በዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በቁጣና በብስጭት ተሞላ፤ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብድናጎን ወደ እርሱ እንዲያመጡአቸው አዘዘ። ስለዚም እነዚህን ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። 14 ናቡከደነፆርም አላቸው፦«ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ አማልክቴን አለማምለካችሁ ወይም ላቆምኩት የወርቅ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? 15 አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን፥የመስንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን፥ የዘፈኑንም ድምፅ ሁሉ በሰማችሁ ጊዜ ለመውደቅ እና ላሠራሁት ምስል ለመስግድ ዝግጅዎች ከሆናችሁ ሁሉም መልካም ይሆናል። ካላመለካችሁ ግን ወዲያው ወደ ሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ትጣላላችሁ። ከእጄስ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማነው?» 16 ሲድራቅ፥ሚሳቅና አብድናጎም ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦« ናቡከደነፆር ሆይ በዚህ ጉዳይ መልስ ልንሰጥህ አያስፈልገንም። 17 መልስ መስጠት የሚገባን ከሆነ፥ የምናገለግለው አምላካችን ከሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ሊያድነን ይችላል፥ ንጉሥ ሆይ፥ ከእጅህም ያድነናል። 18 ነገር ግን ንጉሥ ሆይ ባያድነን እንኳን፥አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምከውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ በአንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን። 19 በዚያን ጊዜ ናቡከደነፆር በቁጣ ተሞላ፤ በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብድናጎ ላይ ፊቱ ተለወጠባቸው። የእቶኑ እሳት ብዙውን ጊዜ ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ እንዲነድድ አዘዘ። 20 ከዚያም ከሠራዊቱ ጥቂት በጣም ብርቱ ሰዎችን፥ ሲድራቅን፥ሚሳቅንና አብድናጎን አሥረው ወደ ሚንቦገቦገው የእቶኑ እሳት እንዲጥሉአችው አዘዘ። 21 እነርሱም መጎናጸፊያቸውን፥ ቀሚሳቸውን፥ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው ወደ ሚንቦገቦገው የእቶን እሳት ተጣሉ። 22 የንጉሡ ትእዛዝ ጥብቅ ስለነበረና የእቶኑ እሳት እጅግ ነዶ ስለነበረ፥ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብድናጎን የወሰዱአቸውን ሰዎች ነበልባሉ ገደላቸው። 23 እነዚህ ሦሥት ሰዎች እንደ ታሰሩ በሚንቦገቦገው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ። 24 ከዚያም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ፥ ፈጥኖም ተነሣ። አማካሪዎቹንም፦ «ሦሥት ሰዎችን አስረን እሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?» ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ለንጉሡ፦ «ንጉሥ ሆይ እርግጥ ነው» ብለው መለሱ። 25 እርሱም፦ «እኔ ግን ያልታሰሩ አራት ሰዎች በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ አያልሁ፥ጉዳትም አላገኛቸውም። የአራተኛው ማንጸባረቅ የአማልክትን ልጅ ይመስላል።» አለ። 26 ከዚያም ናቡከደነፆር ወደ እሳቱ እቶን በር ቀረቦ፦ «የልዑል አምላክ ባሪያዎች ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ ኑ ውጡ! ወደዚህ ኑ!» ብሎ ተጣራ። በዚያን ጊዜም ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ውስጥ ወጡ። 27 በአንድነት የተሰበሰቡት የክፍላተ አገር አስተዳዳሪዎች፥ የክልል አስተዳዳሪዎች፥ ሌሎች አስተዳዳሪዎችና የንጉሡ አማካሪዎች እነዚህን ሰዎች ተመለከቱ። እሳቱ ሰውነታቸውን አልጎዳውም፥ የራሳችው ጸጉር አልተቃጠለም፥ መጎናጸፊያቸው አልተጎዳም፥ የእሳቱም ሽታ በላያቸው አልነበረም። 28 ናቡከደነፆርም እንዲህ አለ፦«መልአኩን የላከውንና ለአገልጋዮቹ መልእክቱን የሰጠውን የሲድራቅን፥የሚሳቅንና የአብድናጎን አምላክ እናመስግን። በእርሱ በመታመን ትእዛዜን ችላ ብለዋል፥ ከአምላካቸውም ሌላ ማንኛውንም ሌላ አምላክ ከማምለክ ወይም ለእርሱ ከመስገድ ይልቅ ሰውነ ታቸውን አሳልፈው መስጠትን መርጠዋል። 29 ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና፥በሲድራቅ፥ሚሳቅና አብድናጎ አምላክ ላይ ክፉ የሚናገር ማንኛውም ሕዝብ፥አገር ወይም ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ይቆራረጣሉ፥ቤቶቻቸውም የቆሻሻ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዤአለሁ። 30 ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብድናጎን በባቢሎን አውራጃ ሾማቸው።