ምዕራፍ 2

1 ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አለመ፤ አእምሮው ታወከ፥ ሊተኛም አልቻለም። 2 ከዚያም አስማተኞችና ሙታን ሳቢዎች እንዲመጡ አዘዘ፤ ጠንቋዮችንና ጠቢባንን ደግሞ ጠራ፤ ስለ ሕልሙ እንዲነግሩት ፈለጋቸው፤ ስለዚህ ገቡና በንጉሡ ፊት ቆሙ። 3 ንጉሡ አላቸው፥«ሕልም አልሜአልሁ፥ሕልሙም ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ አእምሮዬ ተጨንቋል።» 4 ከዚያም ጠቢባኑ በአረማይክ፥ « ንጉሥ ሆይ ለዘላለም ንገሥ! ሕልሙን ለእኛ ለባሪያዎችህ ተናገር፥ እኛም ፍቺውን እናስታውቅሃለን» ብለው ለንጉሡ ተናገሩ። 5 ንጉሡም ለጠቢባኑ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፥« ሕልሙን ካልገለጣችሁልኝና ካልተረጎማችሁት፥ ሰውነታችሁ እንዲቆራረጥና ቤታችሁም የቆሻሻ ክምር እንዲሆን ወስኜአለሁ። 6 ነገር ግን ሕልሙንና ትርጉሙን ከነገራችሁኝ፥ ከእኔ ዘንድ ሥጦታ፥ ሽልማትና ታላቅ ክብር ትቀበላላችሁ። ስለዚህ ሕልሙንና ትርጉሙን ንገሩኝ።» 7 እነርሱም እንደገና እንዲህ ሲሉ መለሱ፥ «ንጉሡ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገር፥ እኛም ትርጉሙን እንነግርሃለን።» 8 ንጉሡም መለሰላቸው፥ «ይህን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔዬ ምን ያህል ጽኑ እንደሆነ ስላወቃችሁ ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንደምትፈልጉ በእርግጥ አውቃለሁ። 9 ነገር ግን ሕልሙን ባትነግሩኝ፥ ሁላችሁን አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል። ሐሰት የሆኑ አሳች አሳቦችን ለማዘጋጅት ወስናችኋል፥ አሳቤንም እስክለውጥ ድረስ ልትነግሩኝ በአንድነት ተስማምታችኋል። ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፥ ያን ጊዜም ልትተረጉሙልኝ እንደምትችሉ አውቃለሁ።» 10 ጠቢባኑም ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፥«የንጉሡን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰው በምድር አይገኝም። አስማተኞችን፥ ሙታን ሳቢዎችን ወይም ጠቢባንን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የጠየቀ ታላቅና ኃያል ንጉሥ የለም። 11 ንጉሡ የሚጠይቀው ነገር አስቸጋሪ ነው፥ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት አማልክት በስተቀር ይህንን ለንጉሡ መንገር የሚችል ማንም የለም። 12 ይህም ንጉሡን አስቆጣው እጅግም አበሳጨው፥ በባቢሎንም በጥበባቸው የሚታወቁትን ሁሉ እንዲያጠፉአቸው አዘዘ። 13 ስለዚህም አዋጁ ወጣ፤ በጥበባቸው የሚታወቁት ሁሉ ሊገድሉ ሆነ፥ ዳንኤልንና ጓደኞቹንም ሊገድሉአቸው ፈለጉአቸው። 14 በዚያን ጊዜ ዳንኤል በባቢሎን በጥበባቸው የሚታወቁትን ሁሉ ሊገድል ለመጣው ለንጉሡ የዘበኞች አዛዥ ለአርዮክ በጥንቃቄና በማስተዋል መለሰለት። 15 ዳንኤልም « የንጉሡ አዋጅ ለምን አስቸኳይ ሆነ?» ሲል የንጉሡን አዛዥ ጠየቀው፤ አርዮክም የሆነውን ለዳንኤል ነገረው። 16 በዚያን ጊዜ ዳንኤል ገባና ትርጉሙን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ቀጠሮ ከንጉሥ እንዲሰጠው ጠየቀ። 17 በዚያን ጊዜ ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደና የሆነውን ለአናንያ፥ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ነገራቸው። 18 እርሱም እነርሱም በጥበባቸው ከሚታወቁት ከተቀሩት የባቢሎን ሰዎች ጋር አብረው እንዳይገደሉ፥ ስለዚህ ምሥጢር ከሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲለምኑ አጥብቆ ነገራቸው። 19 20 በዚያች ሌሊት ምሥጢሩ ለዳንኤል በራዕይ ተገለጠለት። በዚያን ጊዜ ዳንኤል የሰማይን አምላክ አመሰገነ፥ አለም፦ «ጥበብና ኃይል የእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን።» 21 ጊዜዎችንና ወቅቶችን ይለውጣል፤ነገሥታትን ይሽራል በዙፋናቸውም ነገሥታትን ያስቀምጣል። ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። 22 እርሱ በጨለማ ያለውን ያውቃልና ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነውና የጠለቁትንና የተሰወሩትን ነገሮች ይገልጣል። 23 የአባቶቼ አምላክ ስለ ሰጠኽኝ ጥበብና ኃይል አመሰግንሃለሁ፥እባርክሃለሁም። የለመንህን ነገር አስታውቀኽኛል፥ንጉሡን ያሳሰበውን ነገር አስታውቀኽናል። 24 ከዚህም በኋላ ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ሁሉ እንዲገድል ንጉሡ ኃላፊነት ወደ ሰጠው ወደ አርዮክ ሄደ። ሄዶም አለው፦« በባቢሎን የሚገኙትን ጠቢባን አትግድል። ወደ ንጉሡ ይዘኽኝ ግባ እኔም የሕልሙን ትርጉም ለንጉሥ እናገራለሁ።» 25 ከዚያም አርዮክ በፍጥነት ዳንኤልን ወደ ንጉሡ አስገባና አለ፦«የንጉሡን ሕልም ትርጉም የሚገልጥ ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አግኝቼአለሁ። 26 ንጉሡም (ብልጣሶር ተብሎ የሚጠራውን) ዳንኤልን አለው፦«ያየሁትን ሕልምና ትርጉሙን ልትነግረኝ ትችላለህን?» 27 ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፦«ንጉሡ የጠየቀው ምሥጢር ጥበብ ባላቸው፥ በሙታን ሳቢዎች፥ በአስማተኞችና በኮከብ ቆጣሪዎችም ሊገለጥ አይችልም። 28 ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማያት ውስጥ አለ፤ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ! እርሱም በሚመጡት ዘመናት ሊሆን ያለውን አስታውቆሃል። በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለህ ያየኽው ሕልምህና የአእምሮህ ራዕዮች እነዚህ ናቸው፦ 29 ንጉሥ ሆይ! በአልጋህ ላይ ሆነህ ሊሆኑ ስላሉ ነገሮች ታስብ ነበር፤ ምሥጢርንም የሚገልጠው ሊሆን ያለውን አስታውቆሃል። 30 እኔ ከሌሎች ሰዎች የሚበልጥ ጥበብ ስላለኝ ይህ ምሥጢር አልተገለጠልኝም። ንጉሥ ሆይ! ይህ ምሥጢር ለእኔ የተገለጠው አንተ ትርጉሙን ትረዳ ዘንድና የውስጥ አሳብህንም ታውቅ ዘንድ ነው። 31 ንጉሥ ሆይ! ትልቅ ምስል አየህ ተመለከትህም። ምስሉም እጅግ ታላቅና አንጸባራቂ ነበር፥ በፊትህም ቆሞ ነበር። ማንጸባረቁም አስፈሪ ነበር። 32 የምስሉ ራስ ከወርቅ የተሠራ ነበር። ደረቱና ክንዶቹ ከብር የተሠሩ ነበሩ። ወገቡና ጭኖቹ ከናስ፥ 33 እግሮቹም ከብረት የተሠሩ ነበሩ። መርገጫ እግሮቹ ከፊሉ ከብረት ከፊሉ ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። 34 የሰው እጆች ሳይነኩት ድንጋይ ሲፈነቀል፥ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትንም የምስሉን መርገጫ እግሮች ሲመታቸውና ሲያደቃቸው ተመለከትህ። 35 ከዚያም ብረቱ፥ሸክላው፥ ናሱ፥ ብሩና ወርቁ ወዲያው እንክትክታቸው ወጣ፤ በመከርም ወቅት በአውድማ ላይ እንዳል እብቅ ሆኑ። ነፋሱም ጠርጎ ወሰዳችው ምልክታቸውም አልቀረም። ነገር ግን ምስሉን የመታው ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ሞላ። 36 ሕልምህ ይህ ነበር። አሁን ትርጉሙን ለንጉሥ እንናግራለን። 37 አንተ ንጉሥ ሆይ! የሰማይ አምላክ መንግስትን፥ ኃይልን፥ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ ነህ። 38 የሰው ልጆች የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ በእጅህ ሰጠህ። የምድር እንሰሳትንና የሰማያት ወፎችን በእጅህ ሰጠህ፤ በእነርሱ ሁሉ ላይም ግዢ አደረገህ። አንተ የምስሉ የወርቅ ራስ ነህ። 39 ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሳል፤ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሦሥተኛ የናስ መንግሥት ይነሳል። 40 ብረት ሌሎች ነገሮችን እንደሚሰባብርና ሁሉን ነገር እንደሚያደቅቅ፥እንዲሁ እንደ ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሳል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደቅቃቸዋል ይፈጫቸዋልም። 41 እግሮቹና ጣቶቹ በከፊል ከሸክላ በከፊል ከብረት ተሠርተው እንዳየህ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ለስላሳ ሸክላ ከብረት ጋር ተደባልቆ እንዳየህ እንዲሁ የተወሰነ የብረት ብርታት ይኖረዋል። 42 የእግሮቹ ጣቶች በከፊል ከብረት በከፊል ከሸክላ ተሠርተው እንዳየህ መንግሥቱ በከፊል ብርቱ በከፊል ደካማ ይሆናል። 43 ብረትና ለስላሳ ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ እንዲሁ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ብረትና ሸክላ እ ንደማይዋሓድ እነርሱም አብረው አይዘልቁም። 44 በእነዚያ ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋና በሌላ ሕዝብ የማይሸንፍ መንግሥት ያቆማል። ሌሎቹን መንግሥታት ይፈጫቸዋል ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። 45 የሰው እጆች ሳይነኩት ድንጋይ ከተራራ ሲፈነቀል እንዳየህ እንዲሁ ነው። እርሱም ብረቱን፥ ናሱን፥ ሸክላውን፥ ብሩንና ወርቁን አደቀቃቸው። ንጉሥ ሆይ! ከዚህ በኋላ ሊሆን ያለውን ታላቁ አምላክ አስታውቆሃል። ሕልሙ እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው። 46 ንጉሥ ናቡከደነፆርም በዳንኤል ፊት በግንባሩ ተደፋ አከበረውም፤ መሥዋዕትና ዕጣን እንዲይቀርቡለት አዘዘ። 47 ንጉሡ ዳንኤልን እንዲህ አለው፦« ይህን ምሥጢር መግለጥ ችለሃልና፥ ምሥጢርን ሁሉ የሚገልጠው አምላክህ በእውነት የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታት ጌታ ነው።» 48 ከዚያም በኋላ ንጉሡ ዳንኤልን እጅግ አከበረው፥ብዙ አስደናቂ ሥጦታዎችንም ሰጠው። በባቢሎን ክፍለ አገር ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው። በባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አስተዳዳሪ ሆነ። 49 ዳንኤልም ለንጉሡ ጥያቄ አቀረበ፥ ንጉሡም ሲድራቅን፥ሚሳቅንና አብድናጎን በባቢሎን ክፍለ አገር ላይ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ሾማቸው። ዳንኤል ግን በንጉሡ ቤተ መንግሥት ተቀመጠ።