8

1 እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሳት ሁሉ አሰበ። በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ ውሃውም ጎደለ። 2 የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ መስኮቶች ተዘጉ፣ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ። 3 ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ ሃምሳ ቀን በኋላም የውሃው ከፍታ እጅግ ቀነሰ። 4 በሰባተኛው ወር፤ በአሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ አረፈች። 5 ውሃው እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየጎደለ ሄደ። በአሥረኛው ወር መጀመሪያው ቀን የተራሮች ጫፎች ታዩ። 6 ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣ 7 ቁራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቁራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። 8 ከዚያም በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ ገጽ ጎድሎ እንደሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤ 9 ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ መርከቡ ውስጥ አስገባት። 10 ሰባት ቀን ከቆየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደገና ላካት። 11 እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን አወቀ። 12 ደግሞም ሰባት ቀን ከቆየ በኋላ ኖኅ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቢቱ ወደ እርሱ አልተመለሰችም። 13 ኖኅ በተወለደ 601ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፣ ምድሪቱም እንደደረቀች አየ። 14 በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች። 15 ከዚያም እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው። 16 “አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ። 17 እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ ከአንተ ጋር ያሉትን ወፎች፣ እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።” 18 ስለዚህ ኖኅ ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ። 19 እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር የሚሳቡት፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ። 20 ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። ንፁሕ ከሆኑት እንስሳትና ንፁሕ ከሆኑት ወፎች አንዳንዶቹን ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። 21 እግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን መዓዛ አሸተተ፣ በልቡም እንዲህ አለ፦ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በእርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጡራንን ዳግመኛ አላጠፋም። 22 ምድር እስካለች ድረስ የዘር ወቅትና መከር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ፣ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም።”