7

1 እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ። 2 ከንፁህ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት ወንድና ሴት፣ ንፁሕ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ወንድና ሴት ከአንተ ጋር አስገባ። 3 እንዲሁም ከሰማይ ወፎች ወገን ሰባት ወንዶችና ሰባት ሴቶች በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ ከአንተ ጋር ታስገባለህ። 4 ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ላይ አጠፋለሁ።” 5 ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 6 የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የ600 ዓመት ሰው ነበር። 7 ኖኅና ወንዶች ልጆቹ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ። 8 ንፁሕ ከሆኑትና ንፁሕ ካልሆኑት እንስሳት ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ 9 ጥንድ ጥንድ ወንድና ሴት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሄር ኖኅን ባዘዘው መሠረትም ወደ መርከቧ ገቡ። 10 ከሰባት ቀንም በኋላ የጠፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ። 11 ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ። 12 ዝናቡም መዝነብ ጀመረ፣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ባለማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ። 13 ዝናቡ መዝነብ በጀመረበት ቀን ኖኅና ሚስቱ ከልጆቻቸው ጋር ከሴም ከካም ከያፌትና ከሶስቱም ልጆቻቸው ሚስቶች ጋር ወደ መርከቡ ገቡ። 14 ከአራዊት ከእንስሳት በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዓይነት አብረዋቸው ገቡ። 15 የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጡራን በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ። 16 ከሕያዋንም ፍጡራን ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ወንድና ሴት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር የመርከቡን በር ከውጭ ዘጋ። 17 የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለመቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ ውሃው እየጨመረ በሄድ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሳት። 18 ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃ ላይ ተንሳፈፈች። 19 ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው። 20 ውሃው ከተራሮች ጫፍ በላይ 7ሜትር ያህል ከፍ አለ። 21 በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንስሳት፣ አራዊት፣ በምድር የሚርመሰመሱ ፍጡራን ሰዎችም በሙሉ ጠፉ። 22 የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በምድር የነበሩ ፍጡራን ሁሉ ሞቱ። 23 ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከሰዎች ጀምሮ እንስሳት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንና የሰማይ ወፎች ሁሉም ከምድር ገጽ ጠፉ። ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ። 24 ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ አምሳ ቀን ቆየ።