1

1 እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። 2 ምድርም ቅርፅ የሌላትና ባዶ ነበረች። ጥልቅ የሆነው ስፍራዋም በጨለማ ተውጦ ነበር። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃው ላይ ሰፍፎ ነበር። 3 እግዚአብሔርም፦ “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። 4 እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ ብርሃንኑም ከጨለማ ለየው። 5 እግዚአብሔርም ብርሃኑን ‘ቀን’ ጨለማውን ደግሞ ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው። ቀኑ መሸ ሌሊቱም ነጋ አንድ ቀን ሆነ። 6 እግዚአብሔርም፦ “በውሆች መካከል ጠፈር ይሁን፣ ውሆችንም ይለያዩ” አለ። 7 እግዚአብሔር ጠፈርን አደረገና ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያሉትን ውሆች ለየ። እንደዚያም ሆነ። 8 እግዚአብሔር ጠፈሩን ‘ሰማይ’ብሎ ጠራው። ቀኑ መሸ ሌሊቱም ነጋ ሁለተኛ ቀን። 9 እግዚአብሔር፦ “ከሰማይ በታች ያለው ውሃ ወደ አንድ ስፍራ ይሰብሰብ፣ ምድሩም ይገለጥ” አለ። እንደዚያም ሆነ። 10 እግዚአብሔርም ምድሩን ‘የብስ’፣ ወደአንድ ስፍራ የተሰበሰበውንም ውሃ ‘ባሕር’ ብሎ ጠራው። ይህም መልካም መሆኑን ተመለከተ። 11 እግዚአብሔር፦ እንደ ዓይነታቸው ዘርን የሚያፈሩ ተክሎችን፣ በውስጣቸው ዘርን ያዘሉ የፍራፍሬ ዛፎችን እንደዓይነታቸው የሚያፈሩ አዝርዕትን ታብቅል” አለ። እንደዚያም ሆነ። 12 ምድር እንደአይነታቸው የሚያፈሩ አዝርዕትን አበቀለች። ይህም መልካም እንደሆነ እግዚአብሔር ተመለከተ። 13 ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ ሶስተኛ ቀን ሆነ። 14 እግዚአብሔር፦ “ቀኑን ከሌሊቱ ይለዩ ዘንድ በሰማይ ብርሃናት ይሁኑ። እነዚህ ብርሃናት የዓመት ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን የሚለዩ ምልክቶች ይሁኑ። 15 ለምድርም ብርሃን ይሰጡ ዘንድ በሰማይ ላይ የሚገኙ ብርሃናት ይሁኑ” አለ። እንደዚያም ሆነ። 16 እግዚአብሔር ታላቁ ብርሃን በቀን፣ ታናሹ ብርሃን በሌሊት ይሠለጥኑ ዘንድ ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ። ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። 17 ለምድርም ብርሃን ይሰጡ ዘንድና 18 በቀንና በሌሊት ላይ እንዲሠለጥኑ እንደዚሁም ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ በሰማይ አኖራቸው። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደሆነ ተመለከተ። 19 ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ አራተኛ ቀን ሆነ። 20 እግዚአብሔር፦ “ውሆች በሕያዋን ፍጡራን የተሞሉ ይሁኑ፣ ወፎችም ከምድር በላይ ባለው በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ። 21 እግዚአብሔር ታላላቅ የባሕር ፍጥረታትን እንደዚሁም በምድር የሚንቀሳቀሱ፣ በውሆች ውስጥ የሚርመሰመሱና በክንፎቻቸው የሚበሩ ወፎችን እንደዓይነታቸው ፈጠረ። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደሆነ ተመለከተ። 22 እግዚአብሔርም፦ “ብዙ ተባዙ የባሕርን ውሆች ሙሉአቸው፣ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። 23 ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ አምስተኛ ቀን ሆነ። 24 እግዚአብሔርም፦ “ምድር እንደወገናቸው ሕያው ፍጥረታትን ማለትም ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡትንና የምድር አራዊትን ታስገኝ” አለ። እንደዚያም ሆነ። 25 እግዚአብሔር በየዓይነታቸው የምድር አራዊትን፣ በየዓይነታቸው ማናቸውንም በምድር የሚሳቡትን ፈጠረ። 26 እግዚአብሔርም፦ “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንፍጠር፣ ሰዎችም በባሕር ዓሣዎች፣ በሰማይ በሚበሩ ወፎችና በምድር ላይ በሚሳቡ ማናቸውም ተሳቢ ፍጥረቶች ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። 27 እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ፣ በራሱም አምሳል ፈጠረው። ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። 28 እግዚአብሔር ባረካቸው እንደዚህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት ግዟትም። በባሕር ውስጥ ባሉት ዓሣዎች፣ በሰማይ ላይ በሚበሩት ወፎችና በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱት ማናቸውም ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራችሁ” 29 እግዚአብሔርም፦ “እነሆ፣ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ በውስጣቸው ዘርን ያዘሉ ማናቸውንም ተክሎችና በውስጣቸው ፍሬ ያላቸውን ማናቸውንም የፍራፍሬ ዛፎች ሰጥቻችኋለሁ። 30 በምድር ላይ ለሚገኙ እንስሳት ሁሉ፣ በሰማይ ለሚበሩ ወፎች ሁሉ፣ እንዲሁም በምድር ላይ ለሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ማለትም የሕይወት እስትንፋስ ላለበት ማንኛውም ፍጡር ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ። እንደዚሁም ሆነ። 31 እግዚአብሔር የፈጠረውን ማንኛውንም ነገር ተመለከተ። እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበረ። ቀኑ መሸ፣ ሌሊቱም ነጋ ስድስተኛ ቀን ሆነ።