2

1 የምድር በውስጣቸው ያሉትም ሕያዋን ፍጡራን አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተከናወነ። 2 እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጽሞ በዚሁ ቀን ከሥራው ሁሉ አረፈ። 3 እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ ያረፈው በዚህ ቀን ስለሆነ ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም። 4 እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን በፈጠረበት ወቅት የሰማይና የምድር የአፈጣጠራቸው ታሪክ እንደዚህ ነበር። 5 እግዚአብሔር አምላክ በምድር ላይ ዝናብ እንዲዘንብ ስላደረገና ምድርንም የሚያለማ ሰው ባለመኖሩ በምድር ላይ ምንም ቡቃያ አልነበረም፣ በምድር ላይ የሚበቅል ተክልም ገና አልበቀለም። 6 ነገር ግን ውሃ ከመሬት እየመነጨ የምድርን ገጽ ያረሰርስ ነበር። 7 እግዚአብሔር አምላክም ከምድር አፈር ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። 8 እግዚአብሔር አምላክም በስተምሥራቅ በኩል በዔደን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፣ የአበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። 9 ከምድር ውስጥም እግዚአብሔር አምላክ ለዓይን የሚያስደስቱና ለምግብነት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ዛፎች እንዲበቅሉ አደረገ። በአትክልት ስፍራው መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበር፣ መልካሙንና ክፉውን የሚያሳውቀውም ዛፍ በዚያ ነበር። 10 የአትክልት ስፍራውንም የሚያጠጣ ወንዝ ከኤደን ይፈስ ነበር። ወንዙም ከኤደን ከወጣ በኋላ አራት ወንዞች ሆኖ ይከፋፈል ነበር። 11 የመጀመሪያው ፊሶን የተባለው ወንዝ ነበር፣ ይህም ወርቅ ይገኝበት የነበረውን መላውን የሐዊላ ምድር አቋርጦ የሚፈስው ወንዝ ነበር። 12 የዚያ አገር ወርቅ የጠራ ወርቅ ነበር፤ በተጨማሪም በዚያ አገር ሽቶና የከበሩ ድንጋዮች ነበሩ። 13 የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ይባል ነበር፣ እርሱም መላውን የኢትዮጵያ ምድር አቋርጦ ይፈስ ነበር። 14 የሶስተኛው ወንዝ ስም ጤግሮስ ይባል ነበር፣ እርሱም በአሦር በስተምሥራቅ ይፈሳል። አራተኛው ወንዝ ኤፍራጥስ ነበር። 15 እግዚአብሔር አምላክም የኤደንን የአትክልት ስፍራ ያለማና ይንከባከብ ዘንድ ሰውን ወስዶ በዚያ አኖረው። 16 እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ በማለት አዘዘው፣ “በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም የፍሬ ዛፍ መብላት ትችላልህ። 17 ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፣ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” 18 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ፦ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም። ስለዚህ የምትመቸውን ረዳት እፈጥርለታለሁ” አለ። 19 እግዚአብሔር አምላክም ከምድር አፈር የምድር እንስሶችንና የሰማይ ወፎችን አበጀ። ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ይመለከት ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው። ለእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር አዳም ያወጣለት ስም ያ ስሙ ሆነ። 20 አዳም ለሁሉም ከብቶች፣ ለሁሉም የሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው። ነገር ግን ለአዳም ለራሱ የምትመች ረዳት አልተገኘለትም። 21 እግዚአብሔር አምላክ በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ፣ ስለሆነም አዳም አንቀላፋ። እግዚአብሔር አምላክ አዳም አንቀላፍቶ ሳለ ከጎድን አጥንቶቹ አንዱን ወስዶ አጥንቱን የወሰደበትን ስፍራ በሥጋ ዘጋው። 22 እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም ከወሰደው የጎድን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት። ወደ አዳምም አመጣት። 23 አዳምም፦ “አሁን ይህቺ ከአጥንቴ የተገኘች አጥንት ከሥጋዬ የተገኘች ሥጋ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” አለ። 24 ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። 25 አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ራቁታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር።