ምዕራፍ 1

1 እኔ የባቱኤል ልጅ ኢዮኤል ነኝ፤ እግዚአብሔር ለእኔ የሰጠኝ መልእት ይህ ነው፡፡ 2 እናንተ የእስራኤል መሪዎችና በዚች አገር የምትኖሩ ማንኛችሁም ሰዎች ይህንን መልእክት አድምጡ! እኛ ወይም አባቶቻችን በኖሩበት ዘመን እንዲህ ያለ ነገር ከቶ ሆኖ ዐያውቅም፡፡ 3 እናንተ ለልጆቻችሁ ንገሩ፣ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው እንዲነግሯቸው ንገሯቸው፤ የልጅ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው እንዲነግሩ ንገሯቸው፡፡ 4 ሰብሎቻችንን ስለበሉ አንበጣዎች እየተናገርሁ ነው፤ የመጀመሪያው የአንበጣ መንጋ መጣና ከሰብሉ ቡቃያ አብዛኛውን በላ፤ ከዚያ በኋላ ሌላ መንጋ መጥቶ ከቡቃያው የቀረውን በላ፤ ከዚያ ቀጥሎ ሌላ መንጋ እያኰበኰበ መጣ፤ በመጨረሻም ሌላ መንጋ መጣና ማንኛውንም ነገር ደመሰሰ፡፡ 5 እናንተ የሰከራችሁ ንቁ! ዘለላው ሁሉ ስለጠፉ፣ ዐዲስ ወይን ጠጅም ስለማይኖር ነቅታችሁ በከፍተኛ ድምፅ አልቅሱ! 6 ግዙፍ የአንበጣ መንጋ ወደ አገራችን ገብቷል፤ ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ወታደሮች እንዳሉት ብርቱ ሠራዊት ናቸው፤ አንበጦቹ እንደ አንበሳ ጥርሶች የተሳሉ ጥርሶች አሏቸው! 7 ቅርንጫፎቹ ተራቁተው ነጭ እስኪሆኑ በመላጥና ቅርፊቱን ሁሉ በመብላት የወይን ተክሎቻችንና የበለስ ዛፎቻችንን ደምስሰዋል፡፡ 8 የታጨችለት ወጣት ሲሞትባት ልጃገረድ እንደምታለቅስና ዋይ እንደምትል አልቅሱ፡፡ 9 መሥዋዕት እንዲሆን በቤተ መቅደስ የምናቀርበው ዱቄት ወይም ወይን ጠጅ ስለሌለን እግዚአብሔርን በሚያገለግሉ ካህናት እያለቀሱ ነው፡፡ 10 በማሳ ላይ ያለው ስላጠፉ መሬቱ ራሱ እንደሚያለቅስ ሆኗል፤ እህሉ ጠፍቷል፤ ወይን ጠጅ የሚጠመቅበትም ወይን የለም፤ ከእንግዲህም የወይራ ዘይት የለም፡፡ 11 እናንተ ገበሬዎች እዘኑ! እህሉ ስላጠፋ፣ ስንዴ ወይም ገብስ እየበቀለ ባለመሆኑ የወይን ዘለላን የምትንከባከቡ አልቅሱ፡፡ 12 የወይኑ ተክልና የበለሱ ዛፍ ጠውልገዋልና፣ የሮማኑ ቴምሩና የእንኮይ ዛፎች ሁሉ ደርቀዋልና ሕዝቡ ከእንግዲህ ሐሤት አያደርጉም፡፡ 13 እናንተ ካህናት ማው ልበሱና አልቅሱ፤ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቶችን በማቅረብ እግዚአብሔርን የምታገለግሉ በአምላካችሁ ቤተ መቅደስ የሚቀርብ እህል ወይም ወይን ጠጅ ባለመኖሩ እያለቀሳችሁ መሆናችሁን ለማሳየት እነዚያን የማቅ ልብሶች ሌሊቱን ሁሉ ልበሱ፤ 14 ሕዝቡ ምግብ የማይበላባቸውን ቀናት ለዩ፤ መሪዎቹና ሌሎቹ ሰዎች በቤተ መቅደስ ተሰብስበው በዚያ ወደ እግዚአብሔር እንዲጮኹ ንገሯቸው፡፡ 15 አስፈሪ ነገሮች እየሆነብን ነው! ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እግዚአብሔር ተጨማሪ ጥፋቶች እንዲደርሱብን በሚያደርግበት ጊዜ እኛን የሚቀጣበት ወቅት ፈጥኖ ይደርሳል፡፡ 16 ሰብሎቻችን ቀደም ብለው ጠፍተዋል፤ በአምላካችን ቤተ መቅደስም አንድም ሰው ጨርሶ ሐሤት አያደርግም፡፡ 17 ዘርን ስንዘራ አይበቅልም፤ በመሬት ውስጥ ይደርቃል፤ ስለዚህ የምንሰበስበው ሰብል የለንም፤ ጐተራዎቻችን ባዶ ናቸው፤ በእነርሱ ውስጥ የምናከማቸው እህል የለንም፡፡ 18 ጥቂት የሚበላ ሣር ያለበትን መሰማሪያ በመፈለግ ከብቶቻችን ያቃስታሉ፤ እየተሠቃዩ በመሆናቸው በጎቹም ይጮኻሉ፡፡ 19 ማሰማሪያዎቻችንና ደኖቻችን ደርቀዋልና እግዚአብሔር ወደ አንተ እጮኻለሁ፡፡ 20 ወንዞቹ ሁሉ ደርቀዋልና የዱር እንስሳቱ እንኳ ወደ አንተ እንደሚጮኹ ናቸው፤ ድርቀቱ የምድረ በዳውን ማሰማሪያዎች እንደሚያቃጥል የሚነድ እሳት ነው፡፡