ምዕራፍ 2

1 በእግዚአብሔር የተቀደሰ ተራራ በኢየሩሳሌም ባለው የጽዮን ተራራ መለከትን ንፉ! እግዚአብሔር እኛን በተጨማሪ የሚቀጣበት ጊዜ ፈጥኖ ስለሚደርስ መፍራትና መንቀጥቀጥ እንዳለባቸው ለይሁዳ ሕዝብ ተናገር፡፡ 2 ያ ቀን እጅግ ጨለማና ጭጋጋማ ቀን ነው፤ ጥቁር ደመና ስለሚኖር እጅግ ጨለማ ነው፤ ግዙፍ የአንበጣ መንጋ ተራራውን ስለሸፈነው እንደ ጥቁር ደመና ይሆናል፤ እንደዚህ ያለ ነገር ከዚህ ቀደም በፍጹም አልሆነም፤ እንደዚህ ያለ ነገር በፍጹም ዳግመኛ አይሆንም፡፡ 3 ማንም ሊያመልጠው የማይችል የእሳት ነበልባል ያመጡ ያህል ነው፤ በፊታቸው ምድሪቱ እንደ ዔደን ገነት የተዋበች ነች፤ በስተኋላቸው ግን ምድሪቱ እንደ በረሐ ነች፤ ምንም ነገር በሕይወት አይኖርም፡፡ 4 አንበጦቹ ፈረሶችን ይመሳስላሉ፤ በፈረሶች ላይ እንደተቀመጡ ወታደሮችም ይጋልባሉ፡፡ 5 ለጦርነት እንደሚዘጋጅ ኃያል ሠራዊት ወይም በሜዳ ላይ ገለባን የሚያቃጥል እሳት እንደሚያሰማው ፉጨት በተራሮች ጫፍ ላይ ሲዘሉ የሰረገሎችን የማንኳኳት ድምፅ የመሰለ ድምፅ ያሰማሉ፡፡ 6 ሰዎች መምጣታቸውን ሲመለከቱ እጅግ ይገረጣሉ ይፈሩማል፡፡ 7 ወታደሮች እንደሚያደርጉት አንበጦቹ በግድግዳዎች ላይ ይዘላሉ፤ ረድፋቸውንም ጠብቀው ይጓዛሉ እንጂ በፍጹም ከመስመራቸው ዝንፍ አይሉም (አይወጡም)፡፡ 8 እርስ በርሳቸው ሳይጋፉ ወደፊት ይገሠግሣሉ፤ ሰዎች ጦርና አንካሴ ቢወረውሩባቸውም ያ እንዲቆሙ አያደርጋቸውም፡፡ 9 በከተማ ቅጥሮች ላይ ይርመሰመሳሉ ወደ ቤቶቻችንም ይገባሉ፤ ሌቦች እንደሚያደርጉት በመስኮቶቻችን በኩል ይገባሉ፡፡ 10 መሬት እንድትንገዳገድ ሰማይም እንዲንቀጠቀጥ እንደሚያደርጉ ያህል ነው፡፡ በሰማዩ ላይ እጅግ ብዙ አንበጦች ስለሚኖሩ ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ ክዋክብትም አያንፀባርቁም፡፡ 11 ሊቈጠር የማይችለውን ይህንን የአንበጣ ሠራዊት እግዚአብሔር ይመራዋል፤ እነርሱም የእርሱን ትእዛዝ ያከብራሉ፤ ማንም በሕይወት ሊተርፍ የሚችል እስከማይመስል ድረስ ይህ አሁን በእኛ ላይ የሚፈርድበትና እኛን የሚቀጣበት ጊዜ እጅግ አስፈሪ ነው፡፡ 12 እግዚአብሔር ግን እንደዚህ ይላል፡- ‹‹እንደደረሱባችሁ እንደነዚህ ጥፋቶች ሳይሆን በመላ ውስጣዊ ማንነታችሁ እናንተ ወደ እኔ መመለስ ትችላላችሁ፤ እኔን በመተዋችሁ እንዳዘናችሁ ለማሳየት አልቅሱ፣ ዋይ በሉ ደግሞም ጹሙ፡፡ 13 ማዘናችሁን ለመግለጽ ልብሶቻችሁን ብቻ አትቅደዱ፤ ከዚያ ይልቅ በውስጣዊ ማንነታችሁ ማዘናችሁን ግለጹ፡፡›› እግዚአብሔር መሐሪና ደግ ነው ፈጥኖ አይቈጣም፤ በታማኝነት ሕዝቡን ይወዳል፡፡ ፈጥኖ አይቆጣም፣ ከዚያ ይልቅ እጅግ አብዝቶና በታማኝነት ይወዳችኋል፤ እኛንም መቅጣት አይወድም፡፡ 14 እናንተን ለመቅጣት የወሰነውን ውሳኔ ለውጦ በዚያ ፋንታ በምሕረቱ ያደርግላችሁ እንደሆነ ማንም አያውቅም፤ እንደዚያ የሚያደርግ ከሆነ ከሚሰጣችሁ ነገሮች ጥቂቱን ለእርሱ መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ እህልና ወይን አትረፍርፎ በመስጠት ይባርካችኋል፡፡ 15 በጽዮን ተራራ መለከትን ንፉ፤ ሕዝቡንም ሰብስቡ! ስለ ኃጢአታችሁ ማዘናችሁን ለመግለጽ የተለየ የጾም ወቅት ቅጠሩ፡፡ 16 በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንድታገኙ የሚያደርጓችሁን ሥርዓቶች ፈጽሙ፤ አዛውንቶቹና ልጆቹ ሕፃናቱም ሳይቀሩ፣ ሙሽሪርንና ሙሽራውን ለእልፍኞቻቸው (ከጫጉላ ቤታቸው) ጠርታችሁ ለየት ብላችሁ ለዓላማ እንደተሰለፈ ወገን በአንድት ተያያዙ፡፡ 17 እግዚአብሔርን የሚያገለግሉንም ካህናት በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እንዲያለቅሱና እንደዚህም ብለው እንዲጸልዩ ንገሯቸው፡- ‹‹እግዚአብሔር ሆይ፣ እኛን ሕዝብህን አድነን፤ የባዕድ ሕዝቦች እንዲንቁን አትፍቀድላቸው፤ እንዲያፌዙብንና ‹‹አምላካቸው ለምን ተዋቸው?›› እንዲሉን አትፍቀድላቸው፡፡›› 18 እግዚአብሔር ግን ስለ ሕዝቡ ግድ እንደሚለውና ለእነርሱም በምሕረቱ እንደሚያደርግላቸው ዐሳየ፡፡ 19 ሕዝቡ ሲጸልይ እግዚአብሔር መለሰ እንዲህም አለ፡- ‹‹እኔ እህልና ወይን ጠጅ እንዲሁም የወይራ ዘይት አትረፍርፌ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም ትረካላችሁ፤ ባዕድን ሕዝቦችም እንዲሰድቧችሁ ከእንግዲህ አልፈቅድላቸውም፡፡ 20 ሌላ የአንበጣ ሠራዊት እናንተን ለማጥቃት ከሰሜን ይመጣል፤ ነገር ግን ኢየሩሳሌምን አልፈው ወደ በረሐው ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ አደርጋቸዋለሁ፤ አንዳንዶቹ በስተምሥራቅ በኩል ወደ ሙት ባሕር ይሄዳሉ፤ አንዳንዶቹ በስተምዕራብ በኩል ወደ ታለቁ ባሕር ይሄዳሉ፤ በዚያ ሁሉም ይሞታሉ፣ አካላቸውም ይከረፋል (ይገማል)፤ ለእናንተ ድንቅ ነገሮችን አደርግላችኋለሁ፡፡›› 21 በእርግጥም እግዚአብሔር ድንቅ ነገሮችን ያደርጋል፤ ስለዚህ ምድሪቱ እንኳን ደስ ሊላት ይገባል! 22 መስኩ ፈጥኖ ይለመልማልና የዱር እንስሳቱ ሊፈሩ አይገባቸውም፤ በለሱና ሌሎቹ ዛፎች በፍሬ የተሞሉ ይሆናሉ፤ የወይን ተክሉም በዘለላዎች ይሸፈናል፡፡ 23 እናንተ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ ስለሚያደርግላችሁ ነገር ደስ ይበላችሁ፤ እርሱ ከዚህ ቀደም ሲያደርግላችሁ እንደነበረው በወቅቱ በፀደይና በበልግ ወራት የተትረፈረፈን ዝናብ ይልክላችኋል፡፡ 24 እህላችሁን የምትወቁበት አውድማ በእህል የተሸፈነ ይሆናል፤ ዐዲስ የወይን ጭማቂንና የወይራ ዘይትን የምታጠራቅሙባቸው ጋኖችም ሞልተው ይፈሳሉ፡፡ 25 እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል፡- ‹‹እንዲያጠቃችሁ የላክሁባችሁ ያ ግዙፍ ሠራዊት፣ ታላቁ የአንበጣ መንጋ የደመሰሰባችሁን ማንኛውንም ነገር መልሼ እሰጣችኋለሁ፡፡ 26 እናንተም የእኔ ሕዝብ ሆዳችሁ እስኪሞላ ድረስ ትበላላችሁ፤ ከዚያ በኋላም ስላደረግሁላችሁ ድንቅ ነገሮች እኔን አምላካችሁን ታመሰግናላችሁ፤ ከእንግደዲህ ሌሎች ዳግመኛ እንዲያሳፍሯችሁ በፍጹም አላደርግም፡፡ 27 ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ ምንጊዜም በመካከላችሁ እንዳለሁ፣ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እደሆንሁና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ዳግመኛ ሌሎች እንዲያሳፍራችሁ በፍጹም አልፈቅድም፡ 28 በኋለኛው ዘመን ለብዙ ሰዎች ከመንፈሴ እሰጣለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ በቀጥታ ከእኔ የሚመጡ መልእክቶችን ያስተላልፋሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁ ከእኔ የሆኑ ሕልሞች ያልማሉ፤ ጐበዞቻችሁም ከእኔ የሆኑ ራእዮችን ያያሉ፡፡ 29 በዚያን ጊዜ ለወንድ ለሴት ባሪያዎች እንኳን መንፈሴን እሰጣለሁ፡፡ 30 በምድርና በሰማይ ያልተለመዱ ነገሮችን አደርጋለሁ፤ በምድር ላይ ብዙ ደም መፍሰስ ይኖራል፤ ግዙፍ ደመናዎች የሚመስል ጭስ የሚወጣውም እጅግ ታላቅ እሳት ይኖራል፡፡ 31 በሰማይ ፀሐይ ትጨልማለች፣ ጨረቃም እንደ ደም ትቀላለች፤ እኔ እግዚአብሔር በሰዎች ሁሉ ላይ ከምፈርድበት ከታላቁና ከሚያስፈራው ቀን በፊት እነዚያ ነገሮች ይሆናሉ፡፡ 32 ነገር ግን በዚያን ጊዜ እኔን የሚያመልከኝን ማንኛውንም ሰው አድናለሁ፤ በኢየሩሳሌም ያሉ አንዳንድ ሰዎች ከዚያ ጥፋት እንደሚያመልጡ ቃል እገባለሁ፤ የመረጥኋቸው እነርሱ በሕይወት ይኖራሉ፡፡››