ምዕራፍ 1

1 እነዚህ ሕዝቡ <አስተማሪው> ብለው የሚጠሩት በኢየሩሳሌም ነግሦ የነበረው የንጉሥ ዳዊት ልጅ የተናገራቸው ቃሎችና ምሳሌዎች ናቸው። 2 አስተማሪው እንዲህ ይላል፡< ቋሚ የሆነ ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር እንደ ማለዳ ጤዛ ወይም እንደ ነፋስ ነው። ይመጣል፡ ይሄዳል፡ ነገር ግን ምክንያቱ ምን ይሆን? 3 ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ከሚያከናውኑት ሥራ ሁሉ የሚያገኙት ትርፍ ምንድን ነው?> 4 በየዓመቱ የሸመገሉ ሰዎች ሲሞቱ ሕፃናት ይወለዳሉ፡ ነገር ግን ምድር ፈጽሞ አትለወጥም። 5 በየማለዳው ፀሐይ ትወጣለች፡ምሽትም ላይ ትጠልቃለች፡ወደ ምትወጣበትም ለመመለስ ትጣደፋለች። 6 ነፋስ አንዴ ወደ ደቡብ ከዚያም ተመልሶ ወደ ሰሜን ይነፍሳል፡ መልሶ መላልሶም ይዞራል። 7 ወንዞች ሁሉ ወደ ባህር ይፈሳሉ፡ ባህሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም። ውሃው መሬት ውስጥ ይገባል፡እንደ ገና ወንዝ ሆኖ ይመጣል፡ ተመልሶም ወደ ባህሩ ይፈሳል። 8 ሰው በቃላት ከሚገልጸው በላይ ሁሉም ነገር እርካታ የማይሰጥ ነው። በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ነገር እናያለን፡ያም አሰልቺ ይሆንብናል። የምንሰማው አንድ ዓይነት ነገር ነው፡ ይሁን እንጂ በተጨማሪ መስማት እንፈልጋለን። 9 ሁል ጊዜ ሲደረግ እንደነበረው ሁሉም ነገር እንደዛው እየተደረገ ይቀጥላል። አሁን የሚሆኑ ነገሮች ቀደም ሲል የሆኑ ናቸው፡ወደፊትም ተመልሰው ይሆናሉ። ከዚህ በፊት የተደረገው ነገር እንደ ገና ይደረጋል። በርግጥ በዚህ ምድር ምንም አዲስ ነገር የለም። 10 አንዳንድ ሰዎች «ይህን ተመልከቱ፡ከዚህ በፊት ያልታየ አዲስ ነገር ነው» ይላሉ። ነገር ግን ቀደም ሲል የነበረ ነው፡ እኛ ከመወለዳችንም በፊት ነበር። 11 ከረጅም ዘመን በፊት የሆኑትን ነገሮች ሰዎች አያስታውሷቸውም፡አሁን እያደረግነው ያለው ነገርም ቢሆን ወደፊት በሰዎች ዘንድ አይታወስም 12 እኔ ሰባኪው በኢየሩሳሌም ሆኜ እየገዛሁ ለብዙ ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ነበርሁ። 13 ጥበቤን በመጠቀም በምድር ላይ እየተደረገ የነበረውን ማንኛውም ነገር መርምሬ ለመረዳት ራሴን አተጋሁ። የሚሞክረው ማንኛውንም ሰው እንደሚያደክም ሁሉ እኔንም ያደከመ ተግባር ነበር። 14 በምድር ላይ ከሚደረገው ነገር ማንኛውም ጠቃሚ የሆነ ነገር ለመሥራት የሚያስችለን ምንም ነገር የሌለ ይመስላል። ይህም ነፋስን ለመቆጣጠር እንደ መሞከር ነው። 15 የተጣመሙ ብዙ ነገሮች ቀጥ እንዲሉ ማድረገ አዳጋች ነው። የማናያቸውን ነገሮች መቁጠር አንችልም። 16 እኔም በልቤ'«ከእኔ በፊት በኢሩሳሌም ከነገሡት ከማናቸውም ይልቅ ጥበበኛ ነኝ፡ ከማናቸውም በላይ ጥበበኛና ዐዋቂ የሆንሁ ነኝ። 17 ጥበበኛ ስለመሆን ይበልጥ ለመረዳት እንዲሁም እርባናቢስና ከንቱ የሆኑ ነገሮችን ስለማድረግ ይበልጥ ለመማር ወሰንኩ። ነገር ግን እነዚያን ነገሮች ለመረዳት መሞክርም ከንቱ እንደሆነ ተረዳሁ ፡ነፋስንም ለመቆጣጠር እንደ መሞከር ነበር። 18 በጣም ጥበበኛ የሆነ ሰው ትካዜው ይበዛል። አንድ ሰው ይበልጥ ባወቀ ቁጥር ሐዘኑም እየጨመረ ይሄዳል።