ምዕራፍ 2

1 እኔም በልቤ «ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ሁሉ ለማድረግ እሞክራለሁ፡ ደስ ያለኝን ነገር ማድረግ በርግጥ ደስታ ሊሰጠኝ ይችል እንደሆነ መርምሬ ለማወቅ እጥራለሁ» አልሁ። ነገር ግን ያንንም ማድረግ ከንቱ እንደሆነ ተረዳሁ። 2 እኔም በልቤ «ሁልጊዜ መሳቅ ከንቱ ነው፡አዘውትሬም ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ማድረግ ዘላቂ የሆነ ጥቅም የሚያስገኝ አይደለም» አልሁ። 3 እንግዲህ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ካሰብኩ በኋላ ብዙ የወይን ጠጅ በመጠጣት ራሴን ደስ ለማሰኘት ወሰንኩ። አሁንም ጥበበኛ ለመሆን እየሞከርሁ እያለሁ የጅልነት ሥራ እየሠራሁ ነበር። ሰዎች በምድር ላይ በሚኖሩበት አጭር ጊዜ ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያደርጉ ለማወቅ ሞከርሁ። 4 ታላላቅ ነገሮችን አከናወንሁ። ለራሴ ቤቶች እንዲሠሩና የወይን ተክል እንዲተከል አደረግሁ። 5 የአትክልትና የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጀሁ። በአትክልቱ ስፍራዎችም ላይ የተለያዩ ዓይነት የፍሬ ዛፎች ተከልሁ። 6 የፍሬ ዛፎችንም ለማጠጣት የውሃ ግድቦችን ሠራሁ። 7 ወንድና ሴት ባሪያዎችን ገዛሁ። ወደፊትም በባርነት ሊያገለግሉኝ የሚችሉ ልጆች በቤተ መንግሥቴ ተወለዱ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ብዙ የከብት የበግና የፍየል መንጋዎች ነበሩኝ። 8 ከተለያዩ የአውራጃ ንጉሦችና ገዦች ሀብት የተገኘ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ብርና ወርቅ አከማቸሁ። እኔን የሚያሞጋግሱ ወንድና ሴት አዝማሪዎች አዘጋጀሁ። እንዲሁም በመላው ዓለም ያሉ ወንዶች ተድላ ደስታ ለማግኘት ብለው ብዙ ሴቶች እንደሚሰበስቡ ሁሉ እኔም ብዙ ሚስቶችና ቅምጦች ነበሩኝ። 9 ከዚህም የተነሳ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ይገዛ ከነበረ ከማንኛውም ንጉሥ ይልቅ ከፍተኛ ክብርና ሀብት አገኘሁ። በጥበቤም እየተመራሁ ቀጠልሁ። 10 ያየሁትንና የፈልግሁትን ሁሉ አገኘሁ። ደስታ ይሰጠኛል ብዬ ያሰብሁትን ማንኛውንም ነገር አደረግሁ። ደስ የምሰኝባቸው ነገሮች ሁሉ ለትጋቴና ለድካሜ እንደ ሽልማት ነበሩ። 11 ይሁን እንጂ እነዚያን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ምን ያህል ከባድ ሥራ እንዳከናወንሁ አሰብሁ፡ ካከናወንሁት ተግባር ሁሉ አንዱም ዘለቄታ ያለው ጥቅም እንዳላስገኘልኝ ተረዳሁ። ሁሉም ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነበር። 12 ከዚያም ጥበበኛ እንዲሁም ጅል ስለመሆን ማሰብ ጀመርሁ። እኔም በልቤ «ማንም ሰው እኔ ማድረግ ከምችለው በላይ የተሻለ ነገር ማድረግ ይችላል ብዬ አላስብም» አልሁ። 13 ከዚያም አሰብሁ፡እንዲህም አልሁ፡«በርግጥ ብርሃን ከጨለማ እንደሚሻል ሁሉ ጥበብም ከጅልነት ይሻላል። 14 ምክንያቱም ጥበበኛ ሰዎች በቀን ብርሃን ይሄዳሉ፡ወዴት እንደሚሄዱም ማየት ይችላሉ። ነገር ግን ጅል ሰዎች በጨለማ ይሄዳሉ፡ወዴት እየሄዱም እንደሆነ ማየት አይችሉም።» ነገር ግን ጥበበኞቹም ሆኑ ጅሎቹ ሰዎች በመጨረሻ እንደሚሞቱ አስተዋልሁ። 15 ስለዚህ እኔም በልቤ እንዲህ ብዬ አሰብሁ፡« እኔ በጣም ጠቢብ ነኝ፡ ይሁን እንጂ በሕይወቴ መጨረሻ ጅል ሰዎች እንደሚሞቱ እሞታለሁ፡ ታዲያ በጣም ጠቢብ መሆኔ የጠቀመኝ ምኑ ላይ ነው? ሰዎች ጠቢብ መሆን ጠቃሚ ነው ብለው ለምን እንደሚያስቡ አይገባኝም። 16 ጠቢቡም ሆነ ጅሉ ሁለቱም ይሞታሉ፡ከሞትን በኋላ ሁላችንም የተረሳን ሆነን እንቀራለን።» 17 ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ የምንሠራው ሥራ ሁሉ ለሐዘን የሚዳርግ ሆኖ ስላገኘሁት በሕይወት መኖር ጠላሁ። ሁሉም ከንቱና ነፋስንም ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው። 18 ቀደም ሲል በዚህ ምድር ላይ ያከናወንሁትን አድካሚ ሥራ ሁሉ መጥላት ጀመርሁ። ምክንያቱም እኔ ስሞት ላለኝ ነገር ሁሉ ባለቤት የሚሆነው ከእኔ በኋላ የሚወርሰው ሰው ነው። 19 ያ ሰው ጠቢብ ወይም ጅል ይሁን ማን ያውቃል? ነገር ግን ጅል ቢሆንም እንኳ ሳልታክት በመሥራትና ጥበብ በመጠቀም ያገኘሁትን ነገር ሁሉ ይወርሳል። 20 በዚህ ምድር ስላከናወንሁት ከባድ ሥራ አሰብሁ። ከንቱ ልፋት ስለሆነም አዘንኩ። 21 አንዳንድ ሰዎች የተማሩትን ነገር በመጠቀም በጥበብና በብልሃት ይሠራሉ። ነገር ግን በሚሞቱበት ጊዜ ሁሉንም ነገር ጥለው ይሄዳሉ፡እነዚያን ነገሮች ለማግኘት ምንም ያልደከመው ሌላው ሰው በውርስ ያገኛቸዋል። ያም እውነታ ደግሞ ከንቱና ተስፋ አስቆራጭ ሆነብኝ። 22 ስለዚህ ሰዎች መሥራት የሚችሉትን ነገር ሁሉ ማከናወናቸው ከንቱ ነው። 23 ሁልጊዜ በሚሠሩት ሥራ የሚያተርፉት ሥቃይና ጭንቀት ነው። በሌሊትም አእምሮአቸው ማረፍ አይችልም። ያም ደግሞ ሁሉም ነገር እንዴት ጊዜያዊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። 24 እንግዲህ ማድረግ የምንችለው ከሁሉ የተሻለው ነገር በመብላት በመጠጣት መደሰት በሥራችንም መርካት ነው ብዬ አሰብሁ። እነዚያም እግዚአብሔር ለእኛ ባለው ዕቅድ መሠረት የሚሰጡን ነገሮች እንደሆኑ አስተዋልሁ። 25 ከእግዚአብሔር የተሰጡት ካልሆነ በቀር በእነዚያ ነገሮች መደሰት የሚችል አንድም ሰው የለም። 26 እግዚአብሔር ደስ ለሚያሰኙት ጥበብን ዕውቀትንና ደስታን ይሰጣቸዋል። ነገር ግን ኀጢአተኛ ሰዎች ተግተው በመሥራት ሀብታም ቢሆኑ እግዚአብሔር ገንዘባቸውን ከእነርሱ ወስዶ እርሱን ደስ ለሚያሰኙ ሰዎች መስጠት ይችላል። የሆነ ሆኖ ለዚያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ መረዳት ለእኔ አስቸጋሪ ነበር። እነርሱም ተግተው መሥራታቸው ከንቱና ነፋስንም ለመጨበጥ እንደመሞከር ነበር።