ምዕራፍ 1

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ አቅርቦቶችዋን ሁሉ ለማቋረጥም ከበባት። 2 ጌታም ለናቡከደነፆር በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአቄም ላይ ድል ሰጠው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከሚገኙ የተቀድሱ ዕቃዎች ጥቂቱን ሰጠው። ናቡከደነፆርም ወደ ባቢሎን ምድር ወደ አምላኩ ቤት አመጣቸው፤ የተቀደሱትንም ዕቃዎች በአምላኩ ግምጃ ቤት ውስጥ አኖራቸው። 3 ንጉሡም ዋና አለቃው አስፋኔዝን፣ ከነገሥታቱ ቤተ ሰብና ከመሳፍንቱ ዘር ከሆኑት ከእስራኤል ሰዎች አንዳንዶችን 4 እነርሱም ነውር የሌለባቸውን ወጣት ወንዶች፣ መልከ መልካሞችን፣ ጥበበኞችን፣ በዕውቀትና በማስተዋል የተሞሉትንና በንጉሡ ቤት ለማገልገል ብቁ የሆኑትን እንዲያመጣ አዘዘው። የባቢሎናውያንን ሥነ ጽሑፍና ቋንቋ እንዲያስተምራቸው ነገረው። 5 ንጉሡም ከምግቡና ከሚጠጣው ወይን በየዕለቱ ድርሻ መደበላቸው። እነዚህ ወጣት ወንዶች ለሦስት ዓመት መሠልጠንና ከዚያም በኋላ ንጉሡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። 6 ከእነዚህም መካከል ከይሁዳ ሰዎች ጥቂቶቹ የሆኑት ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ። 7 ዋና አለቃውም ስም አወጣላቸው፦ ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያን ሲድራቅ፣ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያንም አብድናጎ ብሎ ጠራቸው። 8 ነገር ግን ዳንኤል በንጉሡ ምግብና በሚጠጣውም ወይን ራሱን እንዳያረክስ በውስጡ አሰበ። ስለዚህ እንዳያረክስም ከዋናው አለቃ ፈቃድ ጠየቀ። 9 ዋና አለቃው ለእርሱ ባለው አክብሮት አማካይነት እግዚአብሔር ለዳንኤል ሞገስንና መውደድን ሰጠው። 10 ዋና አለቃውም ዳንኤልን እንዲህ አለው፤ «እኔ ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ። ምን ዓይነት ምግብና መጠጥ ማግኘት እንዳለባችሁ አዞኛል። በእናንተ እድሜ ካሉ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁ ስለ ምን ይመለከታል? ንጉሡ ከእናንተ የተነሣ በሞት ይቀጣኝ ይሆናል።» 11 ዳንኤልም ዋናው አለቃ በዳንኤል፣ በአናንያ፣ በሚሳኤልና በአዛርያ ላይ ለሾመው መጋቢ ተናገረ። 12 እርሱም እንዲህ አለ፤ «እባክህ፣ እኛን አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያህል ፈትነን። የምንመገብው ጥቂት አትክልትና የምንጠጣው ውኃ ብቻ ስጠን። 13 ከዚያም የእኛን ፊት የንጉሡን ምግብ ከሚመገቡ ወጣቶች ጋር አስተያይ፤ ባየኸውም መሠረት በአገልጋዮችህ ላይ አድርግ።» 14 መጋቢውም ይህን ለማድረግ ከእርሱ ጋር ተስማማ፤ ለዐሥር ቀንም ፈተናቸው። 15 ከዐሥርም ቀን በኋላ የንጉሡን መብል ከተመገቡ ወጣቶች ይልቅ ፊታቸው ያማረና ሰውነታቸው የወፈረ ሆነው ታዩ። 16 ስለዚህ መጋቢው የተመደበላቸውን የተመረጠ ምግብና ወይን አስቀርቶ አትክልት ብቻ ሰጣቸው። 17 ለእነዚህ አራት ወጣቶች እግዚአብሔር በሁሉም ሥነ ጽሑፍና ትምህርት ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤልም ሁሉንም ዐይነት ራእይና ሕልም መረዳት ይችል ነበር። 18 ወደ እርሱ እንዲመጡ ንጉሡ የመደበው ጊዜ እንዳበቃ፣ ዋናው አለቃ በናቡከደነፆር ፊት አቀረባቸው። 19 ንጉሡም ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ፤ አብረዋቸው ከነበሩት ሁሉ መካከል ከዳንኤል፣ ከሐናንያ፣ ከሚሳኤልና አዛርያ ጋር የሚወዳድር ማንም አልነበረም። በንጉሡ ፊት ቆሙ፥ ሊያገለግሉት ዝግጁዎች ነበሩ። 20 ንጉሡ በጠየቃቸው የጥበብና የማስተዋል ጥያቄዎች ሁሉ፥በግዛቱ ሁሉ ከሚገኙ አስማተኞችና ሙታን ሳቢዎች አሥር እጥፍ በልጠው ተገኙ። 21 ዳንኤልም እስከ ንጉሥ ቂሮስ የመጀመሪያ ዓመት ድረስ እዚያው ነበረ።