46

1 እስራኤልም ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም ሲደርስ፣ ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ መሥዋዕት ሠዋ። 2 እግዚአብሔርም ሌሊት በራእይ ለእስራኤል ተገልጦ፣ “ያዕቆብ፣ ያዕቆብ” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “እነሆ፣ አለሁ” አለ። 3 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ የአባትህ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ ወደ ግብፅ ለመውረድ አትፍራ፤ በዚያ ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና፤ 4 አብሬህ ወደ ግብፅ እወርዳለሁ፣ ከዚያም መልሼ አወጣሃለሁ፣ የዮሴፍ የራሱ እጆች በምትሞትበት ጊዜ ዓይኖችህን ይከድናል። 5 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን ለያዕቆብ በላከላቸው ሠረገላ ላይ አወጧቸው። 6 ከብቶቻቸውንና በከነዓን ምድር ያፈሩትን ሀብት ንብረታቸውን ይዘው፣ ያዕቆብና ዘሮቹ በሙሉ ወደ ግብፅ ወረዱ። 7 ወደ ግብፅም የወረደው፤ ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን፣ ሴቶች ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ማለት ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ነው። 8 ወድ ግብፅ የወረዱት የእስራኤል ልጆች፣ የያዕቆብ ዘሮቹ እነዚህ ናቸው፦ የያዕቆብ የበኩል ልጆ ሮቤል። 9 የሮቤል ልጆች፦ ሄኖኅ፣ ፈሉሶ፣ አስሮን እና ከርሚ ናቸው። 10 የስሞዖን ልጆች፦ ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጸሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሳኡል ናቸው። 11 ልጆች፦ ጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ናቸው። 12 የይሁዳ ልጆች፦ ዔር አውናን፣ ሴሎም፣ ፋሬስ እና ዛራ ናቸው። ነገር ግን ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ። 13 የይሳኮር ልጆች፦ ቶላ፣ ፉዋ፣ ዮብና ሺምሮን ናቸው፤ 14 የዛብሎን ልጆች፦ ሴሬድ፣ ኤሎንና ያሕልኤል ናቸው፤ 15 እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መሰጴጦምያ ሳለ፣ ልያ የወለደችለት ናቸው። ሴቷን ዲናን ጨምሮ፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ቁጥር ሠላሳ ሦስት ነው። 16 የጋድ ልጆች፦ ጽፎን፣ ሐጊ፣ ሹኒ፣ ኤስቦን፣ ዔሪ፣ አሮዲና አርኤሊ ናቸው፤ 17 የአሴር ልጆች፦ ዩምና፣ የሱዋ፣ የሱዊና በሪዓ ናቸው፤ እኅታቸውም ሤራሕ ናት፤ የበሪዓ ልጆች፦ ሐቤርና መልኪኤል ናቸው፤ 18 እነዚህ ዐሥራ ስድስት ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለልያ ከሰጣት ከዘለፋ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። 19 የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍና ብንያም ናቸው፤ 20 በግብፅም የኦን ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት፣ ምናሴንና ኤፍሬምን ለዮሴፍ ወለደችለት። 21 የብንያም ልጆች፦ቤላ፣ ቤኬር፣ አስቤል፣ ጌራ፣ ንዕማን፥ አኪ፣ ሮስ፥ ማንፌን፣ ሑፊምና አርድ ናቸው። 22 እነዚህ ዐሥራ አራቱ፣ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። 23 የዳን ልጅ፦ ሑሺም ነው፤ 24 የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፣ ጉኒ፣ ዮጽርና ሺሌም ናቸው፤ 25 እነዚህ ሰባቱ ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። 26 ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የሄዱት የገዛ ዘሮቹ ብዛት ስድሳ ስድስት ሲሆን የልጆቹን ሚስቶች አይጨምርም። 27 ዮሴፍ በግብፅ የወለዳቸውን ሁለት ልጆች ጨምሮ ወደ ግብፅ የወረደው የያዕቆብ ቤተ ሰብ ቁጥር ሰባ ነበር። 28 ያዕቆብም ወደ ጌሤም ለመሄድ መመሪያ ይቀበል ዘንድ፣ ይሁዳን አስቀድሞ ወደ ዮሴፍ ላከው። እርሱም ጌሤም ሲደርሱ፣ 29 ዮሴፍ ሠረገላውን አዘጋጅቶ፤ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጌሤም አመራ። ዮሴፍ አባቱ ዘንድ እንደደረሰ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ለረጅም ጊዜ አለቀሰ። 30 እስራኤልም ዮሴፍን፣ “በሕይወት መኖርህን ስላየሁ፣ ከእንግዲህ ብሞትም አይቆጨኝም” አለው። 31 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ እነግረዋለሁ፤ እንዲህም እለዋለሁ፣ ‘በከነዓን ምድር የሚኖሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል። 32 ሰዎቹ ከብት የሚጠብቁ ስለሆኑ እረኞች ናቸው፣ ሲመጡም በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውንና ከብቶቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል። 33 ፈርዖን አስጠርቶአችሁ፣ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፤ 34 እናንተ፣ ‘እኛ አገልጋዮችህ ሥራችን ከልጅነታችን ጀምሮ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት ማርባት ነው’ ብላችሁ መልሱለት። ከብት አርቢዎች በግብፃውያን ዘንድ እንደ ጸያፍ ስለሚቆጠሩ፣ በጌሤም ምድር እንድትኖሩ ይፈቅድላችኋል።”