4

1 አዳምም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ። እርሷም ፀነሰች። ቃየንንም ወለደች። “በእግዚአብሔር ዕርዳታ ወንድ ልጅ ወለድሁ” አለች። 2 ከዚያ በኋላም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ ሲሆን ቃየን ግን ገበሬ ሆነ። 3 ከዕለታት አንድ ቀን ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መባ አቀረበ። 4 አቤል ደግሞ መጀመሪያ ከተወለዱ በጎች መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር በአቤልና በመሥዋዕቱ ደስ ተሰኘ፣ 5 በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን ደስ አልተሰኘም። ስለዚህ ቃየን በጣም ተቆጣ፣ ፊቱም ተኮሳተረ። 6 እግዚአብሔር አምላክ ቃየንን፦ “ለምን ተቆጣህ፣ ፊትህስ ለምን ተኮሳተረ? 7 መልካም ብታደርግ ፊትህ ያበራ አልነበረምን? ያደረግኸው መልካም ካልሆን ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባች ናት፣ ልትቆጣጠርህም ትፈልጋለች፣ አንተ ግን በቁጥጥርህ ሥር አድርጋት” አለው። 8 ቃየን ወንድሙን አቤልን፦ “ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፣ በዚያም ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ በቁጣ ተነሳበት፣ ገደለውም። 9 ከዚያ በኋላም እግዚአብሔር ቃየንን፦ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው። እርሱም፦ “አላውቅም፣ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” አለ። 10 እግዚአብሔርም፦ “ያደረግኸው ምንድን ነው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” አለው። 11 “አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። 12 ምድርንም በምታርስበት ጊዜ ፍሬዋን በሙላት አትሰጥህም። በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች ትሆናለህ” አለው። 13 ቃየንም ለእግዚአብሔር፦ ቅጣቴ ከምችለው በላይ ነው። 14 በእርግጥም ዛሬ ከምድሪቱ አባርረኸኛል፣ እኔም ከፊትህ እሸሸጋለሁ። በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፣ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” አለው። 15 እግዚአብሔርም፦ “ቃየንን የሚገድል ማንኛውም ሰው ሰባት እጥፍ የበቀል እርምጃ ይወሰድበታል” አለ። ከዚያ በኋላም የሚያገኘው ማንኛውም ሰው እንዳይገድለው እግዚአብሔር በቃየን ላይ ምልክት አደረገበት። 16 ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ፣ ከኤደን በስተምሥራቅ በነበረው ኖድ በተባለው ምድር ኖረ። 17 ቃየንም ከሚስቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ፣ እርሷም ፀነሰች፣ ሄኖክንም ወለደች። ቃየን ከተማን መሠረተ፣ የመሠረታትንም ከተማ በልጁ ስም ሄኖክ ብሎ ጠራት። 18 ሄኖክም አራድን ወለደ። አራድም መሑያኤልን ወለደ። መሑያኤልም መቱሳኤልን ወለደ። መቱሳኤልም ላሜክን ወለደ። 19 ላሜክም ዓዳና ጺላ የተባሉ ሁለት ሚስቶችን አገባ። 20 ዓዳ ያባልን ወለደች፣ እርሱም በድንኳን ለሚኖሩ ለከብት አርቢዎች አባት ነበር። 21 የእርሱ ወንድም ዩባልም የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት ነበር። 22 ጺላም ከነሐስና ከብረት መሣሪያዎችን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እህት ናዕማ ትባል ነበር። 23 ላሜክ ለሚስቶቹ፦ “አዳና ጺላ ስሙኝ፣ እናንተ የላሜክ ሚስቶች የምላችሁን ስሙኝ ስለጎዳኝና ስላቆሰለኝ አንድ ሰው ገድያለሁ። 24 ቃየንን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል እርምጃ የሚወሰድበት ከሆነ የላሜክ ገዳይማ ሰባ ሰባት እጥፍ የበቀል እርምጃ ይወሰድበታል” አላቸው። 25 አዳም ከሚስቱ ጋር እንደገና የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ፣ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። “ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ምትክ ሰጠኝ” በማለት ስሙን ሤት ብላ ጠራችው። 26 ለሤትም ወንድ ልጅ ተወለደለት፣ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ።