39

1 ዮሴፍ ወደ ግብፅ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖንም ሹማምንት አንዱ የነበረውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብፃዊው ጴጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። 2 እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ስለነበረ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። 3 አሳዳሪው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወነለት ባየ ጊዜ፣ 4 ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፣ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፣ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኃፊነት ሰጠው። 5 ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር የግብፅዊውን ቤት ባረከ፣ የእግዚአብሔርም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። 6 ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፣ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፣ ማናቸውንም ጉዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ-መልካም ነበር፤ 7 ከጊዜ በኋላ የጌታው ሚስት ዮሴፍን ተመልክታ ስላፈቀረችው፣ “ና ከእኔ ጋር አብረን እንተኛ” አለችው። 8 እርሱ ግን ይህን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኃላፊነት ስለሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላልው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። 9 በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኃላፊነት ያለው ማንም የለም፣ ከአንቺ በቀር በእኔ ቁጥጥር ሥር ያላደረገው ምንም ነገር የለም፤ ይኸውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት በእግዚአብሔር ፊት እንዴት እፈጽማለሁ?” 10 ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርሷ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም። 11 አንድ ቀን ዮሴፍ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤት ሲገባ በቤት ውስጥ አንድም ሠራተኛ አልነበረም፤ 12 እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ፣ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጅዋ ላይ ትቶላት ከቤት ሸሽቶ ወጣ። 13 እርሷም ልብሱን በእጅዋ ላይ ትቶ ከቤት ሸሽቶ መውጣቱን በተመለከተች ጊዜ፣ 14 አገልጋዮችዋን ጠርታ እንዲህ አለቻቸው፣ “እነሆ፣ ባለቤቴ ያመጣው ይህ ዕብራዊ ሊያዋርደኝ ነበር፤ ወዳለሁበት ክፍል ገብቶ ሊደፍረኝ ሞከረ፤ እኔ ግን ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽሁ። 15 ዕርዳታ ለማግኘትም መጮኼን በሰማ ጊዜ ልብሱን በአጠገቤ ትቶ ከቤት ሸሽቶ ወጣ።” 16 የዮሴፍ አሳዳሪ እስኪመጣ ድረስ ልብሱን በእርስዋ ዘንድ አቆየችው። 17 በመጣም ጊዜ የሆነውን ታሪክ እንዲህ ስትል ዘርዝራ ነገረችው፤ “አንተ ወደዚህ የመጣኸው ዕብራዊ አገልጋይ ወዳለሁበት ክፍል ገብቶ ሊያዋርደኝ ነበር። 18 ነገር ግን ድምፄን ከፍ አድርጌ በጮኽሁ ጊዜ ልብሱን በአጠገቤ ትቶ ከቤት ሸሽቶ ወጣ።” 19 “የአንተ አገልጋይ እንዲህ አደረገኝ” ብላ የነገረችውን ታሪክ በሰማ ጊዜ የዮሴፍ አሳዳሪ እጅግ ተቆጣ። 20 ዮሴፍንም ወስዶ፣ የንጉሥ እስረኞች ወደታሠሩበት እስር ቤት አስገባው። 21 እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅሩን ዐሳየው፣ በእስር ቤት አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው። 22 ስለዚህ የእስር ቤቱ አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤት ላለውም ነገር ሁሉ ኃላፊ ሆነ። 23 እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ሆኖ የሚያደርገው ነገር ሁሉ እንዲቃናለት ስላደረገ የእስር ቤት አዛዥ በዮሴፍ ቁጥጥር ሥር በነበረው ነገር ምንም ዐሳብ አልነበረበትም።