34

1 ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ሴት ልጅ ዲና፤ አንድ ቀን የዚያን አገር ሴቶች ለማየት ወጣች። 2 የአገሩ ገዥ የኤዊያዊ የኤሞር ልጅ ሴኬም ባያት ጊዜ ያዛት በማስገደድም ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ። 3 ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ልጅቷንም በጣም ወደዳት፤ በጣፈጠም አንደበት አናገራት። 4 ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፣ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው። 5 ያዕቆብ የልጁን የዲናን ክብረ-ንጽሕና ሴኬም እንደደፈረ ሰማ፤ ነገር ግን ወንዶች ልጆቹ የከብት መንጋ ይዘው ተሰማርተው ስለነበር፣ እነርሱ እስኪመጡ ዝም ብሎ ቆየ፤ 6 ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ። 7 የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም የያዕቆብን ልጅ ስለደፈረ አዘኑ እጅግም ተቆጡ። 8 ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዶአታል፤ ስለዚህ እንዲያገባት ፍቀዱለት፤ 9 በጋብቻ እንተሳሰር፣ ሴት ልጃችህን ስጡን፣ የእኛንም ሴቶች አግቡ። 10 አብራችሁንም መኖት ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፣ ኑሩባት፤ ነግዱባት፣ ሀብት ንብረትም አፍሩባት። 11 ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትን ወንድሞች እንዲህ አላቸው። “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤ 12 ለሙሽራዋም ጥሎሽ የፈለጋችሁትን ያህል ጠይቁኝ፤ እርሷን እንዳገባ ፍቀዱልኝ እንጂ፣ የፈለጋችሁትን ሁሉ ለመጠት ዝግጁ ነኝ።” 13 ሴኬም እኅታቸውን ዲናን አስነውሮ ስለነበር የያዕቆብ ልጆች ለእርሱና ለአባቱ በተንኮል እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፣ 14 እንዲህ አሉአቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። 15 ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይኸውም አንተና በእናንተ ዘንድ ያሉት ወንዶች ሁሉ እንደኛ የተገረዛችሁ እንደሆነ ነው። 16 እንዲህ ከሆነ እናንተ የእኛን ሴቶች ልጆች ታገባላችሁ፣ እኛም የእናንተን ሴቶች ልጆች እናገባለን፣ አንድ ሕዝብ ሆነንም አብረን እንኖራለን። 17 ዐሳባችንን ባትቀበሉና ባትገረዙ ግን እኅታችንን ይዘን እንሄዳለን። 18 ያቀረቡትም ዐሳብ ለኤሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው። 19 ከአባቱ ቤተሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረው ይህ ወጣት የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወዶአት ስለነበር፣ ያሉትን ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም። 20 ስለዚህ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ይህንኑ ለወገኖቻቸው ለመንገር ወደ ከተማቸው በር ሄዱ፤ 21 እንዲህም አሏቸው፤ “እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር የሚኖሩት በሰላም ነው፣ በምድሪቱ ላይ አብረው ይቀመጡ፣ ተዘዋውረውም እንዲነግዱ እንፍቀድላቸው፤ ምድሪቱ እንደሆን ለእኛም ለእነርሱም ትበቃለች። ሴቶች ልጆቻቸውን እናገባለን፤ እነርሱም የእኛን ሴቶች ልጆች ያገባሉ፤ 22 ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋር እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው አብረውን ለምኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት፣ የእኛ ወንዶች እንደ እነርሱ የተገረዙ እንደሆነ ብቻ ነው። 23 ታዲያ እንዲህ ብናደርግ ከብታቸው ንብረታቸው፣ እንስሶቻቸውም ሁሉ የእኛው ይሆኑ የለምን? ስለዚህ ባሉት እንስማማ፣ እነርሱም አብረውን ይኑሩ።” 24 የከተማይቱ ነዋሪዎች ሁሉ ኤሞርና ሴኬም ባቀረቡት ዐሳብ ተስማምተው ወንዶቹ ሁሉ ተገረዙ። 25 በሦስተኛውም ቀን የሁሉም ቁስል ገና ትኩስ ሳለ ከያዕቆብ ልጆች ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዓንና ሌዊ፣ ሰይፋቸውን መዘው ሳይታሰብ ወደ ከተማይቱ ገብተው ወንዶቹን በሙሉ ገደሏቸው። 26 ኤሞርንና ሴኬምንም በሰይፍ ገድለው፣ እኅታቸውን ዲናን ከሴኬም ቤት አውጥተው ይዘዋት ተመለሱ። 27 የቀሩትም የያዕቆብ ልጆች እኅታቸውን ስለደፈሩባቸው ወደ ሞቱት ሰዎች ቤት እየገቡ ከተማይቱን በሙሉ ዘረፉ። 28 የበግና የፍየል መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማይቱና በአካባቢው የሚገኘውን ንብረታቸውን ሁሉ ወሰዱባቸው፤ 29 ሀብታቸውን ሁሉ ዘርፈው ሴቶቻቸውንና ሕፃናቶቻቸውን ሁሉ ማርከው በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ይዘው ሄዱ። 30 ያዕቆብ ስምዖንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በእኔ ላይ ከባድ ችግር አመጣችሁብኝ፤ እነሆ፣ በዚህ ድርጊት የተነሣ በዚህች ምድር የሚኖሩ ከነዓናውያንና ፌርዛውያን ይጠሉኛል፤ እኛ በቁጥር አነስተኞች ነን፣ እነርሱ ተባብረው ቢያጠቁን እኔና ቤተሰቤ እንጠፋለን።” 31 ስምዖንና ሌዊ ግን፣ “ታዲያ ሴኬም እኅታችንን እንደዝሙት አዳሪ ይድፈራትን?” አሉት።