24

1 በዚህ ጊዜ አብርሃም ሸመገለ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉ ነገር ባረከው። 2 አብርሃምም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ የቤቱ ሁሉ አዛዥ የሆነውን አገልጋይ እንዲህ አለው፤ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ 3 እኔም በመካከላቸው ከምኖረው ከከነዓናዊያን ለልጄ ሚስት እንዳታጭለት በሰማይና በምድር አምላክ እግዚአብሔር አስምልሃለሁ። 4 ነገር ግን ወደ ገዛ ሀገሬ እና ወደ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስትን ታጭለታለህ። 5 አገልጋዩም «ምናልባት የምመርጥለት እጮኛ ከእንይ ጋሬ ወደዚህ አገር ለመምጣት እምቢ ብትልስ? ልጅህን ቀድሞ አንተ ወደ ነበርክበት አገር እንዲመለስ ላድርገው?» ብሎ ጠየቀ። 6 አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ «በምንም ዓይነት ምክንያት ቢሆን ልጄን ወደዚያ አገር መልሰህ እንዳትወስድ ተጠንቀቅ፤ 7 የሰማይ አምክክ እግዚአብሔር ከአባቴ ቤትና ከትውልድ አገሬ አውጥቶ አምጥቶኛል፤ ይህንንም ምድር ለዝርያዎቼ እንደሚሰጥ በመሃላ ቃል ገብቶልኛል፤ ከዚያ ለልጄ ሚስት ማግኘት እንድትችል እግዚአብሔር መልአኩን በፊትህ ይልካል። 8 ልጅትዋ ከአንተ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንከዚህ መሓላ ነፃ ትሆናለህ፤ ልጄን ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ ወደዚያ አትመልሰው።» 9 ከዚህ በኋላ አገልጋዩ እጁን በጌታው በአብርሃም ጉልበት ላይ አድርጎ አብርሃም ያዘዘውን ሁሉ እንደሚፈፅም በመሐላ ቃል ገባ። 10 የአብርሃም ንብረት ኀላፊ የነበረው መጋቢ ከጌታው ቤት ምርጥ የሆኑ የስጦታ ዕቃዎችን በዕሥር ግመሎች ጭኖ በሰሜን መስጴጦምያ ናኮር ወደሚኖርበት ከተማ ሄደ። 11 እዚያ በደረሰ ጊዜ ከከተማው ውጭ ባለ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ግመሎቹ ተንበርክከው እንዲያርፉ አደረገ፤ ሰዓቱም ሊመሽ ተቃርቦ፣ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበትን ጊዜ ነበር፤ 12 አገልጋዩ እንዲህ ብሎ ጸለየ፣ "የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ዛሬ የእኔን አሳብ በመፈፀም ለጌታዬ ለአብርሃም ዘላለምዊ ፍቅርህን ግለጥ። 13 እነሆ፣ እኔ በዚህ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማይቱም ልጃገረዶች ውሃ ሊቀዱ ወደዚህ ይመጣሉ፤ 14 ከእነሱም አንድዋ ልጃገረድ 'እንስራሽን ዘንበል አድርገሽ ውሃ አጠጪኝ' እላታለሁ፤ 'አንተም ጠጣ፤ ግመሎችህም እንዲጠጡ ውጃ ቀድቼ አመጣለሁ' ካለችኝ ለአገልጋይህ ለይስሐቅ ፍቅርህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።" 15 ገና ጸሎቱን ሳፅቸርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ መጣች፤ የዚህችም ልጅ አባት ባቱኤል ይባል ነበር፤ እርሱም የአብርሃም ወንድም ናኮር ከሚስቱ ከሚልካ የወለደው ነው። 16 ርብቃ ገና ወንድ ያልደረሰባት በጣም ቆንጆ ልጃገረድ ነበረች፤ እርስዋ ወደ ውሃው ጉድጓድ ወርዳ በእንስራዋ ውሃ ከቀዳች በኋላ ተመለሰች። 17 አገልጋዩም ወደ እርስዋ ሮጦ ሄዳና "እባክሽ ከእንስራሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ"አላት። 18 እርስዋም "እሺ ጌታዬ ጠጣ" አለችና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ ዘንበል አድርጋ ያዘችለት። 19 ጠጥቶም ከረካ በኋላ "ለግመሎችህም ውሃ እቀዳላቸዋለሁ፤ እስኪበቃቸውም ድረስ ይጠጡ" አለችው። 20 ወዲያውኑ፤ በእንስራዋ የያዘችውን ውሃ ግመሎቹ በሚጠጡበት ገዳን ላይ ገልብጣ ግመሎቹ ሁሉ ጠጥተው እስከሚረኩ ድረስ እየተጣደፈች ከጉድጓድ ውሃ መቅዳት ቀጠለች። 21 ሰውየውም እግዚአብሔር የሄደበትን ተልእኮ አቃንቶለት እንደሆን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሁሉ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር። 22 ግመሎቹ ጠጥተው በኋላ ሰውየው አምስት ግራም ያህል የሚመዝን የወርቅ ጎታቻ አውጥቶ በጆሮዋ ላይ አደረገላት፤ መቶ ዐሥር ግራም ያህል የሚመዝን ሁለት የወርቅ አምባሮችንም አውጥቶ በእጆችዋ ላይ አደረገላትና፤ 23 "የማን ልጅ ነሽ? እስቲ እባክሽ ንገሪኝ፤ ለእኔና አብረውኝ ቤት ይገኛልን?" ብሎ ጠየቃት። 24 እርስዋም "የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ የባቱኤል አባት ናኮር፣ እናቱም ሚልካ ይባላሉ፤ 25 በቤታችን ብዙ ገለባና ድርቆሽ አለ፤ ለእናንተም ማደሪያ ቦታ ይገኛል" አለችው። 26 ሰውየምውም በመንበርከክ ለእግዚአብሔር ሰግዶ፣ 27 "ለጌታዬ የገባውን ቃል ኪዳንና ዘላለማዊ ፍቅሩን የጠበቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በቀጥታ መርቶ ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት ያመጣኝ እርሱ ነው" አለ። 28 ልጅትዋ ወደ ቤት ሮጣ ሄደችና የሆነውን ሁሉ ለእናትዋና ለእርስዋ ጋር ላሉት ሁሉ ነገረቻቸው። 29 ርብቃ ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱ የአብርሃም አገልጋይ ወዳለበት ውሃ ጉድጓድ እየሮጠ ሄደ። 30 ላባ ወደ ሰውየው የሄደው እኅቱ በጆሮዋ ላይ ያደረገችውን ጉትቻና በእጆችዋ ላይ ያደረገቻቸውን አንባሮች ስላየና ርብቃ ሰውየው ጉድጓድ አጠገብ ከግመሎቹ ጋር ቆሞ አገኘው። 31 ስለዚህ ላባ "አንተ እግዚአብሔር የባረከህ ሰው! ና ወደ ቤት እንሂድ፤ በውጭ የቆምኸው ለምንድን ነው? በቤታችን ለአንተ ማደሪያ የተዘጋጀ ቦታ አለ" አለው። 32 ከዚህ በኋላ ሰውየው ወደ ቤት ሄደ፤ ላባም በግመሎቹ ላይ የነበረውን ጭነት አረግፎ ገለባና ድርቆሽ አቀረበላቸው፤ ቀጥሎም የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩት ሰዎች እግራቸውን የሚታጠቡበትን አመጣላቸው። 33 ገበታ በቀረበው ጊዜ ጊዜ ሰውየው "የተላክሁበትን ጎዳይ ከመናገሬ በፊት እህል አልቀምስም" አለ። ላባም "ይሁን ተናገር" አለው። 34 እርሱም "እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነን፤ 35 እግዚአብሔር ጌታዬ እጅግ ባርኮል፤ ባለጸጋም አድርጎታል፤ ብዙ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ፣ ብርና ወርቅ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል። 36 የጌታዬ ሚስት ሣራ በእርጅናዋ ዘምን ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለዚሁ ልጅ አውርሶታል። 37 ጌታዬ አብርሃም 'እኔ በመካከላቸው ከምኖረው ከከነዓናዊያን ሴቶች ልጆች መካከል ለልጄ ሚስት እንዳላጭለት፤ 38 ነገር ግን ወደ አባቴ ቤተሰብና ወደ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት እጭለት' ሲል በመሐላ ቃል ኪዳን አስገብቶኛል።' 39 እኔም ጌታዬን 'ልጅቷ ከእኔ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ ምን ላድርግ?' ብዬ ጠየኩት። 40 እርሱም እንዲህ አለኝ 'ዘውትር የማገለግለው እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤ ጉዞህም የተቃና እንዲሆን ያደርጋል፤ በዚህ ሁኔታ አንተም ከአባትቴ ቤተሰብና ከዘመዶቼ መካከል ለልጄ ሚስት ልታጭለት ትችላለህ፤ 41 ከመሐላህ ነፃ የምትሆነው ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ልጅትዋን አንሰጥም ብለው የከለከሉህ እንደሆነ ብቻ ነው።' 42 "ከዚያም በኋላ ዛሬ ወደ ውሃው ጉድጓድ ስመጣ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ 'የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ የመጣሁበት ጉዳይ እንዲቃና አድርግልኝ፣ 43 እነሆ በዚህ ውሃ ጉድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ አንዲት ልጃገረድን ውሃ ልትቀዳ ስትመጣ፣ 'እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ' ብዬ እጠይቃታለሁ፤ 44 እርስዋም 'እሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳቸዋለሁ'የምትለኝ ብትሆን፣ ለጌታዬ ልጅ ሚስት እንድትሆን አንተ የመረጥሃት እርስዋ ትሁን። 45 የኅሊና ጸሎትን ገና ሳልጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ ብቅ አለች፤ ወደ ጉድጓዱም ሄዳ ውሃ ቀዳች፤ እኔም 'እባክሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ አልኋት። 46 እርስዋም እንስራዋን በፍጥነት ከጀርባዋ አወረደችና ዘንበል አድርጋ 'እሺ ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ' አለችኝ፤ ስለዚህ እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቼንም አጠጣችልኝ። 47 እኔም 'የማን ልጅ ነሽ?' ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም 'የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ የባቱኤል አባት ናኮር እናቱም ሚልካ ይባላሉ' አለችኝ። ከዚህ በኋላ ጉትቻ በጆሮዋ ላይ፣ አንባሮቹንም በእጅዎችዋ ላይ አደረግሁላት፤ 48 ከዚህ በኋላ በጉልበቴ ተንበርክኬ ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ የጌታዬን የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር አመሰገንሁ፤ ምክንያቱም ለጌታዬ ልጅ ሚስት የምትሆነዋን ሴት ወዳገኘሁበት ወደ ጌታዬ ወንድም ቤት በቀና መንገድ የመራኝ እርሱ ነው። 49 እንግዲህ የጌታዬን ዐደራ በእውነት ተቀብላችሁ እርሱን ደስ ለማሰኘት የምትፈቅዱ እንደሆነ ንገሩኝ፤ የማትፈቅዱም እንደሆነ ቁርጡን ነገሩኝ፤ እኔም እግዚአብሔር ወደሚመራኝ እሄዳለሁ።" 50 ላባና ባቱኤልም "ይህ ነገር ከእግዚአብሔር የመጣ ስለሆነ፣ መከልከል አልችልም፤ 51 ርብቃ ይችውልህ፤ እነሆ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር ራሱ እንደተናገረው ለጌታዬ ልጅ ሚስት ትሁን" አሉት። 52 የአብርሃም አገልጋይ ይህን በሰማ ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ 53 ከውርቅና ከብር የተሠሩ ጌጣጌጦችን፣ እንዲሁም ልብስ አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ለወንድምዋና ለእናትዋም በጣም ውድ የሆኑ ስጦታዎችን አውጥቶ ሰጣቸው። 54 ከዚህ በኋላ የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩ ሰዎች በልተው ጠጥተው እዚያው አደሩ፤ ጠዋት በተነሡ ጊዜ የአብርሃም አገልጋይ "እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ ፍቀዱልኝ" አለ። 55 ነገር ግን የርብቃ ወንድምና እናትዋ "ልጅትዋ ዐሥር ቀን ያህል ከእኛ ጋር ትቆይ፤ ከዚህ በኋላ ከአንተ ጋር ልትሄድ ትችላለች" አሉት። 56 እርሱ ግን "እባካችሁ አታቆዩኝ፤ እግዚአብሔር የመጣሁበትን ጉዳይ ስላቃናልኝ ቶሎ ብፄ ወደ ጌታዬ ልመለስ" አላቸው። 57 እነርሱም "እስቲ ልጅቷን እንጥራትና እርስዋ የምትለውን እንስማ" አሉ። 58 ስለዚህ ርብቃን ጠሩና "ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈልጊያለሽ?" ብለው ጠየቅዋት። እርስዋም "አዎ እሄዳለሁ"አለች። 59 ስለዚህ ርብቃ ሞግዚትዋን አስከትላ፣ ከአብርሃም አገልጋይና ከእርሱ ሰዎች ጋር እንድትሄድ ፈቀዱላት። 60 "አንቺ እኅታችን የብዙ ሺ ሕዝብ እናት ሁኚ፤ ዝርያዎችሽም የጠላቶችሽን ከተሞች ይውረሱ" ብለው ርብቃን መረቁአት። 61 ከዚህ በኋላ ርብቃ ከተከታዮችዋ ጋር ለመሄድ ተነሣች፤ በግመሎቹ ላይ ተቀምጠው ከአብርሃም አገልጋይ ጋር ለመሄድ ተዘጋጁ። በዚህ ዐይነት የአብርሃም አገልጋይ ርብቃን ይዞ ሄደ። 62 በዚህ ጊዜ ይስሐቅ "ብኤር ላሐይ ሮኤ ወይም የሚያየኝን ሕያው አምላክ"የተባለው ኩሬ ወዳለበት በረሓ መጥቶ በኔጌብ ተቀምጦ ነበር። 63 ከለዕታት አንድ ቀን ወደ ማታ ጊዜ እያሰላሰለ በመስክ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ ግመሎች ሲመጡ በሩቅ አየ። 64 ርብቃ ይስሐቅ ባየች ጊዜ ከግመሏ ወረደችና፣ 65 "ያ በመስክ ውስጥ ወደ እኛ የሚመጣው ሰው ማን ነው?" ስትል የአብርሃምን አገልጋይ ጠየቀችው። አገልጋዩም "እርሱ ጌታዬ ነው!" አላት። ስለዚህ በጥፍነት በሻሽ ፊትዋን ሸፈነች። 66 አገልጋዩም ያደረገውም ነግር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67 ከዚህ በኋላ ይስሐቅ እናቱ ሣራ ትኖርበት ወደነበረው ድንኳን ርብቃን ይዞአት ገባ፤ ሚስትም ሆነችው፤ ይስሐቅ ርብቃን ወደዳት፤ በእናቱ ሞት ምክንያት ከደረሰበትም ሐዘን በዚህ ሁኔታ ተጽናና።