13

1 ስለዚህ አብራም ሚስቱንና ያለውን ንብረት ሁሉ ይዞ ከግብፅ ወደ ኔጌብ ሄደ። ሎጥም ከእነርሱ ጋር ነበረ። 2 በዚህ ጊዜ አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ በልጽጎ ነበር። 3 ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ፤ ቀድሞ ድንኳን ተክሎበት ወደ ነበረው በቤቴልና በጋይ መካከል ወደ ነበረው ቦታ ደረሰ። 4 ይህ ቀድሞ መሠዊያ የሠራበት ቦታ ሲሆን በዚያ ያህዌን ጠራ። 5 ከአብራም ጋር ይጓዝ የነበረው ሎጥ የራሱ በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት። 6 ሁለቱ አንድ ላይ ይኖሩ ስለ ነበር ስፍራው አልበቃቸውም፤ በዚህ ላይ ንብረታቸውም በጣም ብዙ ስለ ነበር አብረው መኖር አልቻሉም። 7 ይህም በመሆኑ በአብራምና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተፈጠረ። በዚያ ዘመን ከነኣናውያንና ፌርዛውያን በዚያው አገር ይኖሩ ነበር። 8 አብራም ሎጥን እንዲህ አልው፤ “በእኔና በአንተ፣ በእኔ እረኞችና በአንተ እረኞች መካከል ግጭት መኖር የለበትም፤ በዚህ ላይ ደግሞ ቤተ ሰብ ነን። 9 ይኸው እንደምታየው ምድሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ ወይም አንተ ቀኙን ብትመርጥ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ። 10 ስለዚህ ሎጥ ዙሪያውን ሲመለከት እስከ ዞዓር ድረስ ያለው የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ ሁሉ እንደ ያህዌ ገነት እንደ የግብፅ ምድር በጣም ለም ሆኖ አገኘው። እንዲህ የነበረው እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን ከማጥፋቱ በፊት ነበር። 11 ሎጥ የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ ሁሉ መርቶ ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ በዚህ ሁኔታ ዘመዳሞቹ ተለያዩ። 12 አብራም መኖሪያውን በከነዓን ምድር አደረገ፤ ሎጥ ግን በረባዳው ሜዳ ባሉት ከተሞች መካከል ኖረ። እስከ ሰዶም ድረስ ባለው ቦታ ድንኳኖቹን ተከለ። 13 የሰዶም ሰዎች በጣም ዐመፀኞችና በያህዌም ፊት እጅግ ኀጢአተኞች ነበሩ። 14 ሎጥ ከእርሱ ከተለየው በኋላ ያህዌ አብራምን እንዲህ አለው፤ “ካለህበት ቦታ ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ምዕራብ ተመልከት። 15 ይህን የምታየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ። 16 ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ፤ የምድር ትቢያ ሊቆጠር እንደማይቻል ሁሉ የአንተም ዘር ሊቆጠር አይችልም። 17 እንግዲህ ምድሪቱን ስለምስጥህ ተነሣና በርዝመትና በስፋቱ ተመላለሰባት።” 18 ስለዚህ አብራም ድንኳኑን ነቀለና በኬብሮን ወዳሉት የመምሬ ወርካ ዛፎች መጥቶ ኖረ፤ እዚያም ለያህዌ መሠዊያ ሠራ።