11

1 በዚያ ዘመን መላው ዓለም የሚናገረውና የሚግባባው በአንድ ቋንቋ ነበር። 2 ወደ ምሥራቅ ሲጓዙ፣ በሰናዖር አንድ ሜዳማ ቦታ አግኝተው በዚያ ሰፈሩ። 3 እርስ በርሳቸውም፣ “ኑ፣ ጡብ እንሥራና እስከበቃው ድረስ በእሳት እንተኩሰው” ተባባሉ። በድንጋይ ፈንታ ጡብ ተጠቀሙ፤ ጡቡን እርስ በርስ ለማያያዝም ቅጥራን ተጠቀሙ። 4 ከዚያም፣ “ለስማችን መጠሪያ እንዲሆን ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ። ያንን ካላደረግን በምድር ሁሉ ፊት መበታተናችን ነው” አሉ። 5 የአዳም ልጆች የሠሩትን ለማየት ያህዌ ወደ ከተማውና ወደ ግንቡ ወረደ። 6 ያህዌም፣ “አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ሕዝብ በመሆናቸው ይህን ማድረግ ችለዋል! ከእንግዲህ ማድረግ የፈለጉትን ለማድረግ ምንም የሚያቅታቸው አይኖርም። 7 ኑ እንውረድ፤ አርስ በርስ እንዳይግባቡም ቋንቋቸውን እንደበላልቀው” አለ። 8 ስለዚህ ያህዌ ከዚያ ቦታ ወደ መላው ዓለም በታተናቸው፣ እነርሱም ከተማዋን መሥራት አቋረጡ። 9 በዚያ የዓለምን ቋንቋ ስለ ደበላለቀ የከተማዋ ስም ባቤል ተባለ። ከዚያም ያህዌ በመላው ዓለም በተናቸው። 10 የሴም ትውልድ ይህ ነው። የጥፋት ውሃ ከመጣ ሁለት ዓመት በኋላ ሴም መቶ ዓመት ሲሆነው አርፋድሰድን ወለደ። 11 አርፋድሰድን ከወለደ በኋላ ሴም አምስት መቶ ዓመት ኖረ። ሌሎች ወንዶች እና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 12 አርፋክሰድ በሰለሣ አምስት ዓመቱ ሰላን ወለደ፤ 13 ሰላን ከወለደ በኋላ አርፋክሰድ አራት መቶ ሦስት ዓመት ኖረ፤ እርሱም ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 14 ሳላ ሰላሣ ዓመት ሲሆነው ዔቦርን ወለደ፤ 15 ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሳላ አራት መቶ ሦስት ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 16 ዔቦር አራት ዓመት ሲሆነው ፋሌቅን ወለደ፤ 17 ፋሌቅን ከወለደ በኋላ ዔቦር አራት መቶ ሰላሣ ዓመት ኖረ፤ እርሱም እንዲሁ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 18 ፋሌቅ ሰለሣ ዓመት ሲሆነው፣ ራግውን ወለደ፤ 19 ራግውን ከወለደ በኋላ ፋሌቅ ሁለት መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፤ እርሱም እንዲሁ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 20 ራግው ሰለሣ ሁለት ዓመት ሲሆነው፣ ሴሮሕን ወለደ፤ 21 ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ራግው ሁለት ሞት ሰባት ዓመት ኖረ፤ እርሱም እንዲሁ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 22 ሴሮሕ ሰለሣ ዓመት ሲሆነው፣ ናኮርን ወለደ፤ 23 ናኮርን ከወለደ በኋላ ሴሮሕ ሁለት መቶ ዓመት ኖረ፤ እርሱም እንዲሁ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 24 ናኮር ሃያ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነው ታራን ወለደ፤ 25 ታራን ከወለደ በኋላ ናኮር አንድ መቶ አሥራ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፤ እርሱም እንዲሁ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ። 26 ታራ ሰባ ዓመት ሲሆነው አብራምን፣ ናኮርንና ሐራንን ወለደ። 27 የታራ ትውልድ ይህ ነው። ታራ፣ አብራምን፣ ናኮርንና ሐራን ወለደ። ሐራን ሎጥን ወለደ። 28 ሐራን አባቱ ታራ በሕይወት እያለ በተወለደበት ከተማ በከለዳውያን ዑር ሞተ። 29 አብራምና ናኮር ሁለቱም ሚስት አገቡ። የአብራም ሚስት ሦራ ስትባል፣ የናኮር ሚስት ደግሞ ሚልካ ትባል ነበር፤ ሚልካ የሐራን ልጅ ስትሆን፣ ሐራን የሚልካና የዮሳካ አባት ነበር። 30 ሦራ ምንም ልጅ ያልነበራት መካን ነበረች። 31 ታራ ልጁ አብራምን፣ የልጅ ልጁን ሎጥንና የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነዓን ለመሄድ በከለዳውያን ምድር ከምትገኘው ዑር አብረው ወጡ። ሆኖም፣ ካራን በደረሱ ጊዜ በዚያ ተቀመጡ። 32 ታራ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖሮ በካራን ሞተ።