ምዕራፍ 1

1 ከመዝሙሮች የሚበልጥ የሰለሞን መዝሙር። ልጃገረዲቱ ፍቅረኛዋን እንዲህ ትለዋለች፥ 2 ኦ በአፍህ መሳም በሳምከኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይሻላልና። 3 ሽቶህ አስደሳች መዓዛ አለው፤ ስምህ እንደሚፈስ ሽቶ ነው፥ ስለዚህ ልጃገረዶች ወደዱህ። 4 ካንተ ጋር ውሰደኝ፥ አብረንም እንሮጣለን። ሴቲቱ ለራሷ ትናገራለች፥ ንጉሡ ወደ ቤቱ ውስጥ አስገባኝ። ሴቲቱ ፍቅረኛዋን እንዲህ ስትል ትናገረዋለች፥ ደስ ብሎኛል፤ ስለ አንተ ደስ ይለኛል፤ በፍቅርህ ሐሴት ላድርግ፤ እርሱ ከወይን ጠጅ ይሻላል። ሌሎቹ ሴቶች ቢያደንቁህ ተፈጥሮአዊ ነው 5 አንደኛዋ ሴት ለሌላይቱ ስትናገር፥ እኔ ጥቁር ነኝ፥ ቢሆንም ውብ ነኝ፥ እናንተ ከኢየሩሳሌም ወንዶች የተወለዳችሁ ሴቶች ልጆች፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች ጥቁር፥ እንደ ሰለሞንም መጋረጃዎች ውብ ነኝ። 6 ጥቁር ስለ ሆንኩ ትኩር ብላችሁ አትመልከቱኝ፥ ምክንያቱም ፀሐይ አጥቁሮኛል። የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ተቆጡኝ፥ የወይን አትክልት ጠባቂም አደረጉኝ፥ የራሴን የወይን ቦታ ግን አልጠበቅሁም። ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥ 7 ንገረኝ የምወድህ፥ መንጋህን የምታሰማራው የት ነው? በቀትር ጊዜስ መንጋህን የምታሳርፈው የት ነው? ከባልንጀሮችህ መንጋ ኋላ እንደሚቅበዘበዝ ሰው ለምን እሆናለሁ? ፍቅረኛዋ ሲመልስላት፥ 8 ከሴቶች ሁሉ እጅግ የተዋብሽው ሆይ፥ አታውቂ እንደሆነ፥ የመንጋዬን ኮቴ ተከተይ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞቹ ድንኳን አጠገብ አሰማሪ። 9 የኔ ፍቅር፥ በፈርዖን የሰረገላ ፈረሶች መካከል ካለችው ባዝራ ጋር አመሳሰልሁሽ። 10 ጉንጮችሽ በማስዋቢያ ተውበዋል፥ አንገትሽም በዕንቁ ሐብል። 11 የብር ፈርጥ ያለበት የወርቅ ማጌጫ እሠራልሻለሁ። ሴቲቱ ለራስዋ ስትናገር፥ 12 ንጉሥ ማዕዱ ላይ እያለ፥ የናርዶስ ሽቶዬ መዓዛውን ናኘው። 13 ውዴ ለእኔ ልክ ሌሊቱን ሙሉ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። 14 ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ የወይን ቦታ ውስጥ እንደ ሂና የአበባ ዕቅፍ ነው። ፍቅረኛዋ ሲናገራት፥ 15 ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ አንቺ ውብ ነሽ፤ እነሆ ያማርሽ ነሽ፤ ዓይኖችሽ እርግቦችን ይመስላሉ። ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥ 16 ውዴ ሆይ፥ እነሆ አንተ መልከ መልካም ነህ፥ ያማርክም ነህ። የለመለመው ሣር እንደ አልጋ ያገለግለናል። 17 የቤታችን የማዕዘን ተሸካሚ የዝግባ እንጨት፥ የጣሪያችን ማዋቀሪያም የጥድ እንጨት ነው።