ምዕራፍ 1
1
መሳፍንት ይገዙ በነበረበት ዘመን በምድሪቱ ላይ ራብ ነበረ። አንድ ከበተልሔም ይሁዳ የሆነ ሰው ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር ወደ ሞአብ አገር ሄደ፡፡
2
የሰውዮው ስም አቤሜሌክ ይባል ነበር፣ የሚስቱም ስም ኑኃሚን ይባላል፡፡ የሁለቱም ወንዶች ልጆቹ ስም መሐሎንና ኬሌዎን፣ የይሁዳ ቤተልሔም ኤፍራታውያን ነበሩ፡፡ እነርሱም ወደ ሞዓብም አገር ደረሱና በዚያ ተቀመጡ፡፡
3
የኑኃሚንም ባል አቤሜሌክ ሞተ እርስዋም ከሁለቱ ወንዶች ልጆችዋ ጋር ቀረች፡፡
4
እነዚህ ወንዶች ልጆች ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስቶችን ወሰዱ፤ የአንዷ ስም ዖርፋ ነበር፣ የሌላኛዋ ስም ደግሞ ሩት ነበረ። በዚያም ለአሥር ዓመታት ያህል ተቀመጡ፡፡
5
ከዚያም መሐሎንና ኬሌዎን ሁለቱም ሞቱ፣ ኑኃሚንም ያለ ባልዋና ያለ ሁለቱ ልጆችዋ ብቻዋን ተለይታ ቀረች፡፡
6
በዚያን ጊዜ ኑኃሚን ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ሞአብን ለመልቀቅና ወደ ይሁዳ ለመመለስ ወሰነች፡፡ እርስዋም በሞዓብ ምድር ሳለች እግዚአብሔር የተቸገሩትን ሕዝቡን እንደረዳቸውና መብልን እንደ ሰጣቸው ሰማች፡፡
7
ስለዚህ እርስዋ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከነበረችበት ስፍራ ለቀቀች፣ ከዚያም ወደ ይሁዳ ምድር ለመመለስ መንገዱን ይዘው ወደታች ሄዱ፡፡
8
ኑኃሚን ለምራቶችዋ “ሂዱ፣ እያንዳንዳችሁ ወደ እናታችሁ ቤት ተመለሱ፡፡ ለሞቱትና ለእኔ ታማኝነት እንዳሳያችሁን ሁሉ፣ እግዚአብሔር ለእናንተ ታማኝነቱን ያሳያችሁ፡፡
9
ጌታ እያንዳንዳችሁን በሌላ ባል ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ” አለቻቸው፡፡ ከዚያም ሳመቻቸው፣ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፡፡
10
እነርሱም “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን” አሉአት፡፡
11
ኑኃሚን ግን “ልጆቼ ሆይ፣ ተመለሱ! ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ ይሆኑ ዘንድ ለእናንተ የሚሆኑ ወንዶች ልጆች በማሕጸኔ አሁን አሉን?
12
ልጆቼ ሆይ፣ ተመለሱ፣ በራሳችሁ መንገድ ሂዱ፤ ባል ለማግባት በጣም አርጅቻለሁና፡፡ ዛሬ ማታ ባል አገኛለሁ ብየ እንኳ ተስፋ ባደርግና ወንዶች ልጆችን ብወልድ፣
13
እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትጠብቃላችሁን? እየጠበቃችሁ አሁን ባል ሳታገቡ ትቀራላችሁን? አይሆንም፣ ልጆቼ ሆይ! ከእናንተ ይልቅ ሁኔታው እኔን እጅግ በጣም ያስመርረኛል፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ወጥቶአልና፡፡
14
በዚያን ጊዜ ምራቶችዋ ድምፃቸውንም ከፍ አደረጉና እንደገና አለቀሱ፡፡ ዖርፋም አማትዋን ሳመቻትና ተሰናበተቻት፣ ሩት ግን ተጠግታ ያዘቻት፡፡
15
ኑኃሚንም “አድምጪኝ፣ እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፡፡ ከባልሽ ወንድም ሚስት ጋር አንቺም ተመለሽ” አለቻት፡፡
16
ነገር ግን ሩት “ከአንቺ ርቄ እንድሄድ አታድርጊኝ፣ ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፤ በምትቆይበትም እቆያለሁና፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ ይሆናል፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፡፡
17
በምትሞችበትም እሞታለሁ፣ በዚያም እቀበራለሁ፡፡ ከሞት በቀር እኛን አንድም ነገር ቢለየን እግዚአብሔር ይቅጣኝ፣ ከዚህም በላይ ያድርግብኝ” አለቻት፡፡
18
ኑኃሚን ሩት ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ወሰነች ባየች ጊዜ፣ ከእርስዋ ጋር መከራከር አቆመች፡፡
19
ስለዚህ ሁለቱም ወደ ቤተ ልሔም ከተማ እስኪመጡ ድረስ ተጓዙ፡፡ ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ፣ ከተማው በሙሉ ስለ እነርሱ እጅግ በጣም ተደነቁ፡፡ ሴቶችም “ይህች ኑኃሚን ናትን?” አሉ፡፡
20
እርስዋ ግን “ኑኃሚን ብላችሁ አትጥሩኝ፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጎታልና፣ ማራ በሉኝ” አለቻቸው፡፡
21
በሙላት ሄድሁ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ ቤቴ ባዶዬን እንደገና መለሰኝ፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አዋርዶኝ፣ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኝ እያያችሁ ለምን ኑኃሚን ትሉኛላችሁ?” አለቻቸው፡፡
22
ስለዚህ ኑኃሚንና ምራትዋ ሞአባዊት ሩት ከሞዓብ አገር ተመለሱ፡፡ እነርሱ የገብስ መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ፡፡