ምዕራፍ 1
1
መሳፍንት እስራኤልን ይገዙ በነበረ ዘመን በዚያ አገር ራብ ሆነ፡፡
2
በእስራኤል ይኖር የነበረ አቤሜሌክ የሚባል ሰው ነበር፤ እርሱም ለተወሰነ ጊዜ ለመኖር ወደ ሞዓብ አገር ሄደ፡፡ የሄደው ከሚስቱ ኑኃሚንና ከሁለት ወንዶች ልጆቹ ከመሐሎንና ከኬሌዎን ጋር ነበር፡፡ አቤሜሌክ በትውልዱ ኤፍራታዊ ሲሆን፣ በይሁዳ አውራጃ ባለችው ቤተ ልሔም ከተማ ይኖር ነበር፡፡ ወደ ሞዓብ አገር ሄደው በዚያ ኖሩ፡፡
3
የኑኃሚን ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ ኑኃሚን ከሁለት ልጆቿ ጋር ብቻዋን ቀረች፡፡
4
ልጆቿም ሞዓባውያን ሴቶች አገቡ፡፡ የአንዷ ስም ዖርፋ ሲሆን፣ የሌላዋ ሩት ይባል ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያ አገር አሥር ዓመት ያህል ከኖሩ በኃላ
5
መሐሎንና ኬሌዎን ሞቱ፡፡ ስለዚህ ኑኃሚን ሁለት ልጆቿንና ባልዋን አጥታ ብቻዋን ቀረች፡፡
6
ኑኃሚን ሞዓብ አገር እያለች ያህዌ ሕዝቡን እንደ ጐበኘና በእስራኤል የተትረፈረፈ ምግብ መኖሩን ሰማች፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ምራቶችዋን ይዛ ወደ ቤተልሔም ለመሄድ ተነሣች፡፡
7
ይኖሩበት የነበረውን አገር ትተው ወደ ይሁዳ ምድር ጉዞ ጀመሩ፡፡
8
እየተጓዙ እያለ ኑኃሚን ሁለቱን ምራቶችዋን፣ ‹‹እያንዳንዳችሁ ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ፡፡ ለሞቱት ባሎቻችሁና ለእኔ ቸር እንደ ነበራችሁ ያህዌ ለእናንተም ቸር ይሁንላችሁ፡፡
9
እያንዳንዳችሁ በምታገቡት ባል ቤት ውስጥ ሰላም ይስጣችሁ›› አለቻቸው፡፡ ከዚያም ሳመቻቸው፣ ተያይዘውም ተላቀሱ፡፡
10
እነርሱም፣ ‹‹አይሆንም፣ ከአንቺ ጋር ወደ ወገኖችሽ አገር እንሄዳለን›› አሏት፡፡
11
ኑኃሚን ግን እንዲህ አለቻቸው፣ ‹‹ልጆቼ ሆይ፣ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፡፡ ከእኔ ጋር መምጣታችሁ ጥቅም የለውም፡፡ ከእንግዲህ ባሎች የሚሆኗችሁ ልጆች መውለድ አልችልም፡፡››
12
ወደ ቤታችሁ መመለስ ይሻላችኃል፡፡ ከእንግዲህ ሌላ ባል ማግባት አልችልም፡፡ እንደው ለነገሩ ዛሬ ባል አግብቼ ልጆች ብወልድ እንኳ እነርሱ
13
እስኪያድጉ ድረስ ሳታገቡ ትኖላችሁን? ልጆቼ፣ እንዲህ መሆን የለበትም! ሁኔታው ከእናንተ ይበልጥ እኔን ያሳዝነኛል፤ ምክንያቱም ያህዌ በጣም ብዙ መከራ እንዲደርስብኝ አድርጓል፡፡››
14
ከዚያም ሩትና ዖፍራ እንደ ገና ማልቀስ ጀመሩ፡፡ ዖፍራ አማቷን ስማ ተሰናበተቻት፤ ሩት ግን ከኑኃሚን መለየት አልፈለገችም፡፡
15
በዚህ ጊዜ ኑኃሚን ሩትን፣ ‹‹እነሆ፣ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ዘመዶቿና ወደ አማልክቷ ሄዳለች፤ አንቺም አብረሻት ሄጂ›› አለቻት፡፡
16
ሩት ግን፣ ‹‹አይሆንም፣ እባክሽን ተለይቼሽ እንድሄድ አትንገሪኝ፤ አንቺ ወደምትሄጅበት እሄዳለሁ፡፡ ዘመዶችስ ዘመዶቼ ይሆናሉ፤ አንቺ የምታመልኪውን አምላክ አመልካለሁ፡፡
17
አንቺ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ አንቺ በምትቀበሪበት እቀበራለሁ፡፡ ከአንቺ ተለይቼ ብሄድ ያህዌ ይፍረድብኝ፤ ከዚህ የከፋም ያድርግብኝ፡፡ አንዳችን እስክንሞት በፍጹም አንለያይም›› አለቻት፡፡
18
ሩት ከእርሷ ጋር ለመሄድ መቁረጧን ኑኃሚን ስትረዳ እንድትመለስ መወትወቷን ተወች፡፡
19
ከዚያም ሁለቱ ሴቶች እስከ ቤተልሔም ድረስ ተጓዙ፡፡ እዚያ ሲደርሱ የሰፈሩ ሰው ሁሉ እነርሱን በማየቱ ተደሰተ፡፡ የሰፈሩም ሴቶች፣ ‹‹መቼም ይህቺ ኑኃሚን ልትሆን አትችልም!›› ተባባሉ፡፡
20
ኑኃሚንም፣ ‹‹እባካችሁ ኑኃሚን ብላችሁ አትጥሩኝ፤ ኑኃሚን ‹አስደሳች› ማለት ነው፡፡ ይልቁንም፣ ‹መራራ› ማለት ስለሆነ ማራ በሉኝ፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጐታል፡፡
21
ከዚህ ስሄድ ቤተ ሰብ ስለ ነበረኝ ሕይወቴ ሙሉ ነበር፡፡ ያህዌ ግን ያለ ቤተ ሰብ ባዶዬን ወደዚህ መለሰኝ፡፡ ስለዚህ ኑኃሚን አትበሉኝ፡፡ ያህዌ ቀጥቶኛል፡፡ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ታላቅ መከራ እንዲደርስብኝ አድርጓል›› አለቻቸው፡፡
22
ኑኃሚን ከምራቷ ከሩት ጋር ከሞዓብ ወደ አገሯ የተመለሰችው በዚህ ሁኔታ ነበር፡፡ እነርሱ ቤተልሔም በደረሱ ጊዜ የገብስ መከር መሰብሰብ መጀመሩ ነበር፡፡