ምዕራፍ 1

1 የእግዚአብሔርን ወንጌል በሐዋርያነት እንዲያገለግል ተለይቶ ከተጠራው ከኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከጳውሎስ። 2 ወንጌሉም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በነቢያቱ አስቀድሞ ተስፋ የሰጠው ነው። 3 ይህም ወንጌል በስጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደው ስለ ልጁ ነው። 4 እርሱም በቅድስና መንፈስ ኃይል ከሙታን በመነሳት የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ የተነገረለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። 5 በስሙ ምክንያት ከእምነት የሚገኝ መታዘዝ በሕዝቦች ሁሉ መካከል እንዲሆን በእርሱ በኩል ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን። 6 እናንተም በእነዚህ ሕዝቦች መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ለመሆን ተጠራችሁ። 7 ይህ መልዕክት የተጻፈው በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱስ ሕዝብ ለመሆን ለተጠራችሁ በሮም ላላችሁት ሁሉ ነው። ከእግዚአብሔር ከአባታችንና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 8 ስለ እምነታችሁ በመላው ዓለም በመነገሩ ምክንያት አስቀድሜ ስለሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አምላኬን አመሰግናለሁ። 9 ባለማቋረጥ እንደማስባችሁ የልጁን ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። 10 አሁን በተቻለኝ መጠን በእግዚአብሔር ፈቃድ ተሳክቶልኝ ወደ እናንተ እንድመጣ ሁልጊዜ በጸሎቴ እለምናለሁ። 11 የሚያበረታችሁን ጥቂት መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁ፥ 12 ይኸውም የእኔና የእናንተ በሆነ የእርስ በርሳችን እምነት አማካይነት እንድንበረታታ ስለምጓጓ ነው። 13 ወንድሞች ሆይ፥ ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ለመምጣት እንደ ሞከርኩኝና እስካሁን እንደተስተጓጎልኩኝ ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም። ወደ እናንተ መምጣት የፈለግሁበት ምክንያት ከተቀሩት አሕዛብ እንዳገኘሁት ሁሉ ከእናንተ ደግሞ ጥቂት ፍሬ እንዳገኝ ነው። 14 ለግሪኮችና ግሪኮች ላልሆኑት፥ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ ዕዳ አለብኝ። 15 ስለዚህ፥በበኩሌ በሮም ለምትገኙት ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ለመስበክ ተዘጋጅቻለሁ። 16 በወንጌል አላፍርም! ምክንያቱም እርሱ አስቀድሞ ለአይሁድ ደግሞም ለግሪኮች የሚያምኑትን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ኃይል ስለሆነ ነው። 17 "ጻድቅ በእምነት ይኖራል" ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ በወንጌል ከእምነት ወደ እምነት ተገልጧልና። 18 በአመጻቸው እውነትን በሚያፍኑ አመጸኞችና ክፉዎች ሰዎች ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ተገልጧል። 19 ይኽውም እግዚአብሔር ስላስታወቃቸው ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚገባው ነገር ለእነርሱ ግልጥ ነው። 20 የማይታዩት ገጽታዎቹ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ግልጥ ሆነው ይታያሉ። እነዚህም በተፈጠሩት ነገሮች አማካይነት ይታወቃሉ። ገጽታዎቹም የዘላለም ኃይሉና የመለኮት ባህርዩ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች የሚያመካኙት አይኖራቸውም። 21 ምክንያቱም ስለ እግዚአብሔር ቢያውቁም እንደ እግዚአብሔርነቱ ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት ነው። ይልቁንም በሀሳባቸው ሞኞች ሆኑ፥ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ። 22 ጥበበኞች ነን ቢሉም የማያስተውሉ ሆኑ። 23 የማይጠፋውን የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰው አምሳል፥በወፎች፥ አራት እግር ባላቸው አራዊትና በደረታቸው በሚሳቡ ፍጥረታት መልክ ለወጡ። 24 ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሰውነታቸውን እንዲያዋርዱ እግዚአብሔር ለልባቸው የክፋት ምኞት ለእርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው። 25 እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት የለወጡና በፈጣሪ ፈንታ ፍጥረትን ያመለኩና ያገለገሉ ናቸው፤እርሱ ግን ለዘላለም የተመሰገነ ነው።አሜን። 26 ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔር ለአስነዋሪ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፥ ሴቶቻቸውም ለተፈጥሮአቸው የሚገባውን ተግባር ተገቢ ባልሆነው ለወጡ። 27 እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለተፈጥሮአቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወተ-ሥጋ ምኞት ተቃጠሉ። እነዚህ ወንዶች የማይገባውን ነገር ከወንድ ጋር በማድረጋቸው ስለ ነውራቸው ቅጣትን የተቀበሉ ናቸው። 28 እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈቀዱ እነዚያን ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች እንዲያደርጉ ለማይረባ አዕምሮ አሳልፎ ሰጣቸው። 29 እነርሱ በአመጻ ሁሉ፥በጨካኝነት፥በክፉ ምኞትና በምቀኝነት፥በቅናት፥በነፍስ መግደል፥በጸብ፥በማታለልና በክፉ ሃሳብ የተሞሉ ናቸው። 30 ሐሜተኞች፥የሰው ስም አጥፊዎችና እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ቁጡዎች፥ዕብሪተኞችና ትዕቢተኞች ናቸው። ክፉ ነገሮችን የሚያመነጩና ለወላጆቻችው የማይታዘዙ፥ 31 ማስተዋል የሌላቸው፤እምነት የማይጣልባቸው፥ፍቅር የሌላቸውና የማይምሩ ናቸው። 32 እንደዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ሞት እንደሚገባቸው የሚናገረውን የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ያውቃሉ፥እነርሱ ግን እነዚህኑ ነገሮች ራሳቸው የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆኑ የሚያደርጉትን ሌሎችን የሚያበረታቱ ናቸው።