1 የክርስቶስ አገልጋይ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ይህንን ደብዳቤ በሮሜ ከተማ ለምትገኙ አማኞች በሙሉ ጽፌላችኋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ሐዋርያ እንድሆን መረጠኝ ደግሞም ከእርሱ የተቀበልኩትን መልካሙን የምስራች ለሰዎች ሁሉ እንድናገር ሾመኝ፡፡ 2 ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ ከረዥም ጊዜ በፊት ነቢያቱ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደጻፉት ይህንን መልካም የምሥራች እንደሚገልጥ እግዚአብሔር ተስፋ ሰጥቶ ነበር፡፡ 3 ይህ መልካም የምሥራች የሚናገረው ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም በሥጋ ከንጉስ ከዳዊት ዘር የተወለደ ነው፡፡ 4 ልጁ በመለኮታዊ ባህርዩ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በሃይል የተገለጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን እውነት የገለጠው መንፈስ ቅዱስ ከሙታን እንዲነሳና ሕያው እንዲሆን ባደረገበት ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ 5 እርሱ ለእኛ ታላቅ ቸርነቱንና ጸጋውን በመግለጥ ሐዋርያ እንድንሆን ሾመን፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው ከአይሁድ ወገን ያልሆኑ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን እንዲያምኑና እንዲታዘዙ ነው፡፡ 6 ከእነዚህ መካከል ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ እግዚአብሔር የመረጣችሁ በሮም የምትኖሩ አማኞች ትገኙበታላችሁ፡፡ 7 ይህንን ደብዳቤ የጻፍሁት የእርሱ ሕዝብ ልትሆኑ በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ለተመረጣችሁ ለእናንተ ነው፡፡ እግዚአብሔር አባታችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋንና ሰላም እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፡፡ 8 ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ በጀመርሁበት ጊዜ በሮም ስላላችሁት አማኞች በሙሉ እግዚአብሔር አምላኬን አመሰግናለሁ፡፡ ይህንን ማድረግ የቻልኩት ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ከሰራው ስራ የተነሳ ነው፡፡ በሮሜ ግዛት የሚገኙ ሰዎች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስላላችሁ እምነት እየተናገሩ በመስማቴ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ 9 ስለ ልጁ መልካሙን የምስራች ለሰዎች ሁሉ በምናገርበት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ስጸልይ ስለ እናንተ ሳላቋርጥ አሳስባለሁ፤ ለዚህ ደግሞ በሙሉ ልቤ በመሰጠት የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፡፡ 10 የእርሱ ፈቃድ ቢሆን እግዚአብሔርን አብልጬ የምጠይቀው እናንተን መጥቼ እንድጎበኛችሁ ነው፡፡ 11 ይህን የምጸልየው ክርስቶስን እያመናችሁና እያከበራችሁ እንድትኖሩ ለማየት ስለምናፍቅ ነው፡፡ 12 ይህም እያንዳንዳችን በኢየሱስ ባለን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው፡፡ 13 ወንድሞቼ ሆይ፣ ይህንን እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ ብዙ ጊዜ እናንተን ለመጎብኘት አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ እናንተ መምጣት ያልቻልሁት እንዳልመጣ የከለከለኝ ነገር ስላለ ነው፡፡ ሌሎች አይሁድ ያልሆኑ ሕዝብ በጌታ እንዳመኑ እንደዚሁ ወደ እናንተ መጥቼ ወንጌልን በመስበክ ሰዎች እንዲያምኑ ፈልጌ ነበር፡፡ 14 አይሁድ ላልሆኑት፣ ለግሪክ ተናጋሪዎች፣ ግሪክ ለማይናገሩ፣ ለተማሩና ላልተማሩትም ወንጌልን የመስበክ ግዴታ አለብኝ፡፡ 15 ከዚህ የተነሳ በሮም ለምትኖሩትም መልካሙን የምስራች በጉጉት ልሰብክ እፈልጋለሁ፡፡ 16 እኔ ወንጌልን ይኸውም ክርስቶስ ያደረገውን ስራ በድፍረት እሰብካለሁ ምክንያቱም ይህ ወንጌል ክርስቶስ ለሰዎች የሰራውን ስራ ለሚያምኑ ሁሉ እግዚአብሔር ማዳኑን የሚገልጥበትና ሰዎችን የሚያድን የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ እግዚአብሔር በመጀመርያ በእርሱ ያመኑትን አይሁዳውያን ያድናል፣ ከዚያም አይሁድ ያልሆኑ ሕዝቦችን ያድናል፡፡ 17 በዚህ ወንጌል አማካኝነት እግዚአብሔር ሰዎችን እንዴት እንደሚያጸድቅ ገለጠ፡፡ ይህም ነቢዩ ከዘመናት በፊት በቅዱሳት መጻሕፍት “ጻድቅ በእምነት በሕይወት ይኖራል” ብሎ እንደጻፈው ነው፡፡ 18 በሰማይ ያለው እግዚአብሔር እርሱን በማያከብሩና አመጻን በሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ላይ እንደሚፈርድ ግልጽ አድርጓል፡፡ እነርሱም ለፈጸሙት አመጻ ፍርድ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያሳያል፡፡ እነዚህ ሰዎች በክፋታቸው እውነትን አፍነው በመያዝ ሌሎችም ስለ እግዚአብሔር እውነት አውቀው እንዳይድኑ ስለሚከለክሉ ነው፡፡ 19 እግዚአብሔር ለሁሉም ይህንን ነገር ግልጽ ስላደረገ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል አይሁድ ያልሆኑ ሕዝቦች ማወቅ ይችላሉ፡፡ 20 ሰዎች እግዚአብሔር ምን እንደሚስል በተፈጥሮ አይናቸው አይተው ሊረዱት አይችሉም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ ጀምሮ በፍጥረት ውስጥ ያሉት ነገሮች ስለ እርሱ መለኮታዊ ባህርይ ማለትም ዘላለማዊ ኃይሉንና ሁሉንም ነገሮች መፍጠር መቻሉን ይመሰክሩልናል፡፡ ሌላው የእርሱን ማንነት የሚያሳየው ነገር እርሱ የፈጠራቸው ፍጡራን ሁሉ ልዩ መሆናቸውን ሁሉም ሰው ማወቁ ነው፡፡ ስለዚህም ማንም ሰው “እግዚአብሔርን አላወቅሁትም” ብሎ በድፍረት መናገር አይችልም፡፡ 21 አይሁድ ያልሆኑ ሕዝቦች አምላክነቱን እያወቁ ነገር ግን አላከበሩትም፣ ለሰራውም ታላቅ ስራ ምስጋናን አልሰጡም፡፡ ይልቁንም ስለ እርሱ ከንቱ ነገር ማሰብ ጀመሩ፤ ከዚህ የተነሳ ስለ እርሱ ሊያውቁ የሚገባቸውን ነገር ማወቅ አልቻሉም፡፡ 22 ጠቢባን ነን ቢሉም ሞኞች ሆኑ፤ 23 የእግዚአብሔርን ክብርና ዘላለማዊነት ክደው በሚሞቱ ሰዎች፣ በወፎች፣ አራት እግር ባላቸውና በተሳቢ እንስሳት የተሰሩ አማልክትን አመለኩ፡፡ 24 ስለዚህም እግዚአብሔር አይሁድ ያልሆኑ ሕዝቦች ሊያደርጉት አጥብቀው ይመኙት የነበረውን አስነዋሪ የወሲብ ተግባር እንዲፈጽሙ ተዋቸው፡፡ ይህን ያደረገው እርሱን በመካድ ይህን አስነዋሪ ነገር ለማድረግ ጥልቅ ምኞት ስለነበራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለባህርያቸው በማይገባ የወሲብ ድርጊት ሰውነታቸውን በከንቱ አረከሱ፡፡ 25 ከዚህ በተጨማሪ ስለ እግዚአብሔር ያለውን እውነት ከመቀበል ይልቅ ሐሰተኛ አማልክትን ለማምለክ መረጡ፡፡ ሊመለክ የሚገባውንና ሁሉን ነገር የፈጠረውን እግዚአብሔርን ትተው እርሱ የፈጠራቸውን ፍጡራን ማምለክን መረጡ፡፡ እርሱ ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ነው! አሜን፡፡ 26 ከዚህ የተነሳ እግዚአብሔር የተመኙትን አሳፋሪ የሆነ ወሲባዊ ድርጊት እንዲፈጽሙ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ለእንዲህ ዓይነት አእምሮ ታልፈው በመሰጣቸው ምክንያት ሴቶች ከሌሎች ሴቶች ጋር ከተፈጥሮ ስርዓት ውጭ የሆነ ወሲብ መፈጸም ጀመሩ፡፡ 27 በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ ወንዶችም ተፈጥሮአዊ የሆነውን ከሴቶች ጋር መተኛት ትተው አሳፋሪና ለባህርያቸው በማይገባ መልኩ ከሌሎች ወንዶች ጋር ተኙ፡፡ ወንዶች ከወንዶች ጋር አሳፋሪ ግብረሰዶማዊ ተግባር ፈጸሙ፡፡ እግዚአብሔር ለፈጸሙት ድርጊት የሚገባቸውን ፍርድ እንዲያገኙ አካላቸውን በእንግዳ በሽታ በመምታት ቀጣቸው፡፡ 28 በተጨማሪም እግዚአብሔርን ማወቅ ባልፈለጉ መጠን በማይረባና በከንቱ ሃሳባቸው ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ አደረጋቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ማንም ሊያደርገው የማይገባውን ክፉ ድርጊት መፈጸም ጀመሩ፡፡ 29 ማንኛውንም ጽድቅ የሌለበትን ነገር ለመፈጸም ራሳቸውን ሰጡ፡፡ በሌሎች ላይም ክፋትን ሁሉ አደረጉ፣ በተለያዩ መንገዶች በሌሎች ላይ ጉዳት አደረሱ፡፡ የሌሎችን ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ ተመኙ፣ ሌሎችንም በተለያዩ መንገዶች ለመጉዳት አሰቡ፡፡ ብዙዎቹም በሌሎች ላይ ጥልቅ ቅናት አደረባቸው፣ ነፍሰ ገዳዮችም ሆኑ፣ ጥልና ክርክርንም የሚወድዱ ሆኑ፣ ሌሎችንም ለማሳት ፈለጉ፣ በሌሎችም ላይ ክፋትን ተናገሩ፡፡ 30 ብዙዎቹም ሐሜተኞች፣ የሌሎችንም ስም የሚያጠፉ፣ እግዚአብሔርንም የሚጠሉ፣ አመጸኞች፣ ሰዎችንም የሚያንገላቱ፣ በትዕቢት የተሞሉና ክፋትን የሚፈልጉ ሆኑ፡፡ ልጆችም ወላጆቻቸውን የማይታዘዙና የማያከብሩ ሆኑ፡፡ 31 እግዚአብሔርን የሚያስከፉ፣ ለሌሎች የገቡትን ቃል የሚያፈርሱ፣ ቤተሰቦቻቸውን የማይወድዱና ለሰዎችም ምሕረት የሌላቸው ሆኑ፡፡ 32 እግዚአብሔር ለሚያደርጉት ነገር በሞት እንደሚቀጣቸው እያወቁ እንኳ ክፋት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፣ ክፋት ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሚያደርጉትንም ያደፋፍራሉ፡፡