ምዕራፍ 1

1 ይህ ፈጥኖ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ራእይ ነው። እርሱም ይህን ራእይ መልአኩን ወደ አገልጋዩ ወደ ዮሐንስ በመላክ እንዲታወቅ አድርጓል። 2 ዮሐንስም የእግዚአብሔርን ቃል በሚመለከት ስላየው ማንኛውንም ነገር እና ክርስቶስን በሚመለከት ስለተሰጠው ምስክርነት ተናግሯል። 3 ዘመኑ ስለ ቀረበ ፥ የዚህን የትንቢት ቃል የሚያነብ የተባረከ ነው፤እንዲሁም የሚሰሙት ሁሉ በውስጡም የተጻፈው ን ነገር የሚፈጽሙ የተባረኩ ናቸው። 4 ከዮሐንስ፥በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ካለው፥ከነበረው፥ወደፊትም ከሚመጣውና በዙፋኑ ፊት ካሉት ከሰባቱ መንፈሶች 5 እንዲሁም ታማኝ ምስክር፥ከሙታን በኩርና የምድር ነገሥታት ገዥ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለሚወደንና ከኀጢአታችንም በደሙ ነጻ ላወጣን፥ 6 አባቱ ለሆነው እግዚአብሔር መንግሥትና ካህናት እንሆን ዘንድ ላደረገን ለእርሱ ክብርና ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤አሜን። 7 እነሆ፤እርሱ በደመና ይመጣል፤የወጉትን ጨምሮ ዐይን ሁሉ ያየዋል። የምድርም ነገዶች ሁሉ በእርሱ ምክንያት ያለቅሳሉ፤እንደዚያም ይሆናል፤አሜን። 8 ጌታ እግዚአብሔር፥« አልፋና ኦሜጋ፥ ያለሁና የነበርሁ፥ወደፊትም የምመጣው ሁሉን ቻይ እኔ ነኝ» ይላል። 9 እኔ ከእናንተ ጋር በመከራው፥በመንግሥቱና በኢየሱስ በሚገኘው ትዕግሥት ተካፋይ የሆንሁ ወንድማችሁ ዮሐንስ፥ በእግዚአብሔር ቃልና በኢየሱስ ምስክርነት ምክንያት ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ። 10 በጌታም ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤በኋላዬም የመለከትን ድምጽ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። 11 ድምፁም እንዲህ የሚል ነበር፤«የምታየውን በመጽሓፍ ጻፈው፤ ከዚያም በኤፌሶን፥ በሰምርኔስ፥ በጴርጋሞን፥ በትያጥሮን፥ በሰርዴስ፥ በፊለደልፍያና በሎዶቅያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላከው። 12 ይናገረኝ የነበረው የማን ድምፅ እንደ ሆነ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወር በምልበትም ጊዜ ሰባት የወርቅ መቅረዞችን አየሁ። 13 በመቅረዞቹም መካከል እስከ እግሩ ድረስ የሚደርስ ረጅም ልብስ የለበሰና ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ የሰው ልጅ የሚመስለው ነበር። 14 ራሱና ጸጉሩ እንደ ነጭ የበግ ጸጉር ማለትም እንደ በረዶ ነጭ ነበሩ፤ዐይኖቹ የእሳት ነበልባል፥ 15 እግሮቹም በእቶን እሳት እንደ ነጠረ የጋለ ናስ፥ ድምፁም እንደ ብዙ ወራጅ ውኃ ድምፅ ነበር። 16 በቀኝ እጁ ሰባት ከዋክብት ይዞ ነበር፤ከአፉም በሁለት በኩል የተሳለ ስለታም ሰይፍ ይወጣ ነበር፤ፊቱም ጸሐይ በሙሉ ኀይልዋ ስታበራ የምታበራውን ያህል ያበራ ነበር። 17 ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ሥር ወደቅሁ፤ እርሱም ቀኝ እጁን በእኔ ላይ በመጫን እንዲህ አለኝ፤ «አትፍራ፤እኔ የመጀመሪያውና የመጨረሻው 18 ሕያውም ሆኜ የምኖር ነኝ። ሞቼ ነበር፤እነሆም ለዘላለም ሕያው ነኝ፤የሞትና የሲዖል መክፈቻም አለኝ። 19 ስለዚህ ያየኽውን፥አሁን ያለውን ሁኔታና ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ነገር ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ያሉት አንተም ያየሃቸውን የሰባቱን ከዋክብትና የሰባቱን የወርቅ መቅረዞች ምስጢር በተመለከተ ትርጉሙ ይህ ነው፤ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ሲሆኑ፥ ሰባቱ መቅረዞች ደግሞ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።