ምዕራፍ 1

1 ጌታ አምላካችን ስለ ኤዶም ሕዝብ ለእኔ ለአብድዩ የሰጠኝ መልእክት ይህ ነው፤ ጌታ አምላካችን ስለ ኤዶም ሕዝብ የሚከተለውን ነገረኝ፦ “እኔ ጌታ እግዚአብሔር ተዘጋጅተው እንዲሄዱና በኤዶም ላይ አደጋ እንዲጥሉ የሚነግራቸው መልእክተኛ ወደ ሌሎች ሕዝቦች ልኬአለሁ። 2 ”ጌታ እግዚአብሔርም ለኤዶም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ፈጥኜ በምድር ላይ ደካማና እጅግ በጣም የተናቅህ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” 3 ዋና ከተማህ በከፍተኛው አለታማ ገደል ላይ ይገኛል፣ አንተም በጣም ታብየሃል፤ ሊያጠቃህ የሚችል ሠራዊት ስለሌለ ደኅንነቴ የተጠበቀ ነው ብለህ አስበሃል፣ነገር ግን ራስህን አታለሃል። 4 ክንፍ ኖሮህ ከንስር ይልቅ ከፍ ብለህ መብረር ብትችል እንኳ መኖሪያህንም በከዋክብት መካከል ብታደርግ፣ ከዚያ ተንኮታኩተህ እንድትወርድ አደርግሃለሁ። 5 ሌቦች በሌሊት የሰውን ቤት ሰብረው በሚገቡበት ጊዜ፣ የሚፈልጓቸውን ነገሮች ብቻ ይሰርቃሉ፤ የወይን ፍሬንም የሚሰበስቡ ሁልጊዜ በግንዱ ላይ ቃርሚያ ያስቀራሉ፤ የአንተ አገር ግን ፈጽሞ ይደመሰሳል! 6 ከፍተኛ ዋጋ ያለው ማንኛውም ነገር ይወሰድብሃል፤ ጠላቶችህ አንተ የደበቅሃቸውን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች እንኳ ፈልገው ይወስዳሉ። 7 አጋሮችህ የነበሩ ሁሉ ይነሡብሃል፤ ክአገርህም እንድትመጣ ያስገድዱሃል፤ አሁን ከአንተ ጋር ሰላም መሥርተው አብረውህ ያሉት ያታልሉሃል ያሸንፉሃልም’ አሁን ከአንተ ጋር እንጀራ የሚበሉ ወጥመድ ሊዘረጉብህ ዕቅድ ያወጣሉ፤ ከዚያም “ነኝ ብለህ እንዳሰብኸው ብልኅ አይደለህም!” ይሉሃል። 8 ኤዶምን በማጠፋበት በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በእርግጠኝነት እናገራለሁ፤ ከፍ ባለው አለታማ ስፍራ የሚኖሩትን ብልኆች ነን ብለው ያሰቡትን ሰዎች እቀጣለሁ። 9 በቴማን ከተማ የሚኖሩ ወታደሮች ይፍራሉ፤ እናንተ የዔሳው ዝርያዎች የሆናችሁ ሕዝብ ሁሉ ተጠራርጋችሁ ትወጣላችሁ።” 10 “የቀድሞው አባትህ የዔሳው መንትያ በነበረው በያዕቆብ ዝርያዎች፣ በዘመዶችህ ላይ ግፍ ስለ ሠራህ፣ አሁን ትዋረዳለህ፤ ለዘላለምም ትደሰሰሳለህ። 11 ባዕዳን በኢየሩሳሌም በሮች ገቡ ያገኙአቸውንም ዋጋ የሚያወጡ ነገሮች ለመከፋፈል ዕጣ ተጣጣሉ፤ አንተ ግን እዚያ ቆመህ እስራኤላውያንን ስላልረዳህ፣ የእነዚያ ባዕዳን ያህል አንተም ክፉ ነበርህ። 12 በእስራኤላውያን ላይ በደረሰው መከራ መደሰት አይገባህም ነበር፤ ከተሞቻቸው በፈራረሱ ጊዜ ሐሔት ልታደርግ ባልተገባህም ነበር፤ መከራ በደረሰባቸውም ጊዜ ልትሳለቅባቸው አይገባህም ነበር። 13 እነርሱ የእኔ ሕዝብ ናቸው፤ ስለዚህ በመከራቸው ጊዜ ወደ ከተማቸው በር መግባት አይገባህም ነበር፤ ልትስቅባቸውም አይገባህም ነበር፤ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ንብረቶቻቸውንም ቀምተህ መውሰድ አይገባህም ነበር። 14 ለመሸሽ የሚሞክሩትን ለመያዝ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መቆም አልነበረብህም፤ በመከራቸው ጊዜ ይዘህ ለጠላት አስልፈህ ልትሰጣቸው አይገባህም ነበር።” 15 እኔ እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ የምፈርድበት ጊዜ ፈጥኖ ይደርሳል፤ እናንተም የኤዶም ሕዝብ ሆይ፣ በሌሎች ላይ ያደረሳችሁት መከራ በእናንተም ላይ ይደርሳል፤ በሌሎች ላይ የፈጸማችሁት ክፋት በእናንተም ላይ ይፈጸማል። 16 በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን እጅግ የመረረ ጽዋ የጠጣችሁ ያህል ነበር፤ ነገር ግን ሌሎቹን አሕዛብ ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ክፉኛ እቀጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም እንዲጠፋ አደርጋቸዋለሁ። 17 በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አንዳንዶች ግን ያመልጣሉ፤ ኢየሩሳሌምም በጣም የተቀደሰች ስፍራ ትሆናለች፤ ከዚያ በኋላ የያዕቆብ ዝርያዎች በእውነት የራሳቸው የሆነችውን ምድር እንደ ገና ድል አድርገው የራሳቸው ያደርጓታል። 18 የያዕቆብና የልጁ የዮሴፍ ዝርያዎች እንደ እሳት፣ የኤዶምም ሕዝብ በዚያ እሳት ፈጽሞ እንደሚቃጠል ገለባ ይሆናሉ፤ አንድም ሰው አይተርፍም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና ይህ በእርግጥ ይሆናል።” 19 ኤዶምን ማርከው የሚይዙት በደቡቡ የይሁዳ በረሓ የሚኖሩት እስራኤላውያን ይሆናሉ፤ በምዕራቡ ተራራዎች ግርጌ የሚኖሩትም የፊንቄን ክፍለ አገርና የኤፍሬምን እንዲሁም የሰማርያን አካባቢዎች ይይዛሉ፤ የብንያም ነገድ ሕዝብም የገለዓድን ክፍለ አገር ድል አድርገው ይይዛሉ። 20 በባቢሎን በስደት ላይ የነበሩት ወደ ምድራቸው ይመለሳሉ፤ በሜዴትራኒያን ባሕር ጠረፍ ወደ ሰሜን እስከ ሰራጵታ ያለውን የፊንቄን ክፍለ አገር ይይዛሉ፤ የልድያ ክፍለ አገር ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ሰርዴስ ተይዘው የተወሰዱት የኢየሩሳሌም ሕዝብ በደቡብ ይሁዳ በረሓ ያሉትን ከተሞች ይይዛሉ። 21 የኢየሩሳሌም ሠራዊት በኤዶም ላይ ጥቃት አድረሰው ይይዙታል፤ ጌታ እግዚአብሔርም ንጉሣቸው ይሆናል።