ምዕራፍ 1

1 ያህዌ በሲና ምድረ በዳ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን ተናገረው፡፡ ይህ የሆነው የእስራኤል ህዝብ ከግብጽ ምድር በወጣበት በሁለተኛው አመት በሁለኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ነበር፡፡ ያህዌ እንዲህ አለ፣ 2 “በየነገዱ፣ በየአባቶቻቸው ቤተሰቦች የእስራኤል ወንዶች ቆጠራ ይደረግ፡፡ በስም ቁጠራቸው፡ እያንዳንዱ ወንድ፣ በሰው ቁጠር፣ 3 ሀያ አመት የሞላው ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ወንድ ሁሉ ይቆጠር፡፡ ለእስራኤል ወታደር ሆኖ ሊዋጋ የሚችለውን ሁሉ ቁጠር፡፡ አንተና አሮን በታጣቂ ቡድኖቻቸው የወንዶችን ቁጥር መዝግቡ፡፡ 4 ከእያንዳንዱ ጎሳ አንድ ሰው፣ የነገድ አለቃ ከአንተ ጋር የጎሳው መሪ ሆኖ ያገልግል፡፡ እያንዳንዱ መሪ ለጎሳው የሚዋጉትን ወንዶች ይምራ፡፡ 5 ከአንተ ጋር ሆነው መዋጋት ያለባቸው መሪዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፡ ከሮቤል ጎሳ፣ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፣ 6 ከስምዖን ጎሳ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤ 7 ከይሁዳ ጎሳ፣ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፤ 8 ከይሳኮር ጎሳ የሶገር ልጅ ናትናኤል፤ 9 ከዛብን ጎሳ፣ የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤ 10 ከኤፍሬም ጎሳ፣ የዮሴፍ ልጅ፣ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤ ከምናሴ ጎሳ፣ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤ 11 ከብንያም ጎሳ የዮሴፍ ልጅ፣ የጌዲዮን ልጅ አቢዳን፤ 12 ከዳን ጎሳ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፣ 13 ከአሴር ጎሳ፣ የኤክራን ልጅ ፉግኤል፣ 14 ከጋድ ጎሳ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤ 15 እና ከንፍታሌም ጎሳ፣ የዔናን ልጅ አኪሬ” ናቸው፡፡ 16 ከሕዝቡ የተመረጡት ወንዶች እነዚህ ነበሩ እነርሱ የአባቶቻቸውን ጎሳዎች ይመራሉ፡፡ በእስራኤል የነገዶች መሪዎች ነበሩ፡፡ 17 ሙሴና አሮን በስም የተመዘገቡትን እነዚህን ወንዶች ወሰዱ፣ 18 ከእዚህ ወንዶች ጋር በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን የእስራኤል ወንዱን ሁሉ ሰበሰቡ፡፡ ከዚያም ሃያ አመት የሞላውና ከዚያ በላይ የሆነ እያንዳንዱ ወንድ የትውልድ ሐረጉን ተናገረ፡፡ እያንዳንዱ የነገዱን ስም እና የትውልድ ሐረጉን መጥራት ነበረበት፡፡ 19 ከዚያም ሙሴ በሲና ምድረ በዳ ያህዌ እንዲያደርገው ባዘዘው መሠረት ቁጥራቸውን መዘገበ፡፡ 20 የእስራኤል በኩር ከሆነው ከሮቤል ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉት ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 21 ከሮቤል ጎሳ 46500 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 22 ከስምኦን ትውልዶች ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉት ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 23 ከስምዖን ጎሳ 59300 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 24 ከጋድ ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 25 ከጋድ ጎሳ 45650 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 26 ከይሁዳ ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስም ተቆጠሩ፡፡ 27 ከይሁዳ ጎሳ 7460 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 28 ከይሳኮር ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 29 ከይሳኮር ጎሳ 54400 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 30 ከዛብሎን ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 31 ከዛብን ጎሳ 57400 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 32 ከዮሴፍ ልጅ ከኤፍሬም ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 33 ከኤፍሬም ጎሳ 40500 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 34 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፤ 35 ከምናሴ ጎሳ 32200 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 36 ከብንያም ትውልዶች ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፤ 37 ከብንያም ጎሳ 35400 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 38 ከዳን ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 39 ከዳን ጎሳ 62700 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 40 ከአሴር ትውልዶች፣ ወደ ጦርት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 41 ከአሴር ጎሳ 41500 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 42 ከንፍታሌም ትውልዶች፣ ወደ ጦርነት መሄድ የሚችሉ ሃያ አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ከየጎሳቸውና፣ ከየቤተሰባቸው መዛግብት እያንዳንዳቸው በስማቸው ተቆጠሩ፡፡ 43 ከንፍታሌም ጎሳ 53400 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡ 44 ሙሴና አሮን እነዚህን ወንዶች ሁሉ አስራ ሁለቱን የእስራኤል ጎሳዎች ከሚመሩ አስራ ሁለት ሰዎች ጋር ሆነው ቆጠሩ፡፡ 45 ስለዚህም ሃያ አመትና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ለጦርነት መውጣት የሚችሉ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ በየቤተሰባቸው ተቆጠሩ፡፡ 46 የቆጠሯቸው ወንዶች 603550 ናቸው፡፡ 47 ከሌዊ ትውልድ የሆኑት ግን አልተቆጠሩም፣ 48 ምክንያቱም ያህዌ ሙሴን እንዲህ ብሎት ነበር፣ 49 “የሌዊን ጎሳ አትቆጥርም ወይም እነርሱን በእስራኤል ህዝብ ቆጠራ ውስጥ አታስገባቸው፡፡ 50 ይልቁንም፣ ሌዋውያንን የቃልኪዳኑን ስርዓቶች በቤተመቅደስ እንዲፈጽሙ መድባቸው፣ እንደዚሁም በቤተመቅደስ ውስጥ የሚገኙ መገልገያዎችንና ማናቸውንም ነገሮች እንዲንከባከቡ ሹማቸው፡፡ ሌዋውያን ጽላቱን ይሸከሙ፣ እንዲሁም የቤተመቅደሱን ዕቃዎች ይሸከሙ፡፡ 51 ቤተመቅደሱ ወደ ሌላ ስፍራ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ፣ ሌዋውያኑ ይንቀሉት፡፡ ቤተመቅደሱ ሲተከል፣ ሌዋውያን ይትከሉት፡፡ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚጠጋ ማናቸውም እንግዳ ይገደል፡፡ 52 እስራኤላውያን ድንኳኖቸውን ሲተክሉ፣ እያንዳንዱ ሰው ወደ ራሱ የጦር ቡድን ዐርማ አጅግ ቀርቦ ይስራ፡፡ 53 ሆኖም፣ ሌዋውያኑ ቁጣዬ በእስራኤላውያን ላይ እንዳይሆን ድንኳናቸውን በቃል ኪዳኑ ማደሪያ ዙሪያ ይትከሉ፡፡ ሌዋውያኑ የቃልኪዳኑን ማደሪያ ሀላፊዎች ናቸው፡፡” 54 እስራኤላውያን እነዚህን ሁሉ ነገሮች አደረጉ፡፡ ያህዌ በሙሴ በኩል ያዘዛቸውን ነገሮች ሁሉ አደረጉ፡፡