ምዕራፍ 8

1 ህዝቡ ሁሉ በውሃ በር አጠገብ በሚገኘው አደባባይ በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ የሚነገረውን መረዳት የሚችሉ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ልጆች በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ እነርሱም ህግጋቱንና ትዕዛዛቱን ይጠብቁ ዘንድ፣ ያህዌ ለእስራኤል ህዝብ መመሪያ አድርጎ የሰጠውን ሙሴ የፃፈውን የህግ ጥቅልል መጽሐፍ እንዲመያጣ ዕዝራን ጠየቁት፡፡ 2 በቤተ መቅደስ መስዋዕቶችን በማቅረብ እግዚአብሔርን የሚያገለግለው ዕዝራ፣ ለወንዶችና ለሴቶች እንዲሁም ለማናቸውም የሚነበበውን መረዳት ለሚችሉ ህጉን አውጥቶ በህዝቡ ሁሉ ፊት አነበበ፡፡ ይህንን በዚያ አመት በሰባተኛው ወር በወሩ በመጀመሪያው ቀን አደረገ፡፡ 3 ስለዚህም መጽሐፉን አውጥቶ ለህዝቡ አነበበ፡፡ ጠዋት ከማለዳ አንስቶ እስከ እኩለ ቀን ድረስ የህጉን መጽሐፍ አነበበ፡፡ ወንዶና ሴቶች እንዲሁም የሚያነበውን መረዳት የሚችሉ ሁሉ ሰሙት፡፡ ዕዝራ ከህጉ መጽሐፍ የሚያነበውን፣ ህዝቡ በታላቅ ፍላጎት አደመጠ፡፡ 4 ዕዝራ ለዚህ ተግባር በህዝቡ በተዘጋጀ ከፍ ያ የእንጨት መድረክ ላይ ቆመ፡፡ ከእርሱ በስተቀኝ መቲትያ፣ ሽማዕ፣ ዓናያ፣ ኦርዮ፣ ኬልቅያስ እና መዕሤያ ቆመው ነበር፡፡ በስተግራው በኩል ደግሞ ፈዳያ፣ ሚሳኤል፣ መልክያ፣ ሐሱም፣ ሐሽበዳ፣ ዘካርያስና ሜሱላም ቆመው ነበር፡፡ 5 ዕዝራ በመድረኩ ላይ ሁሉም ሰዎች ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ቆሞ ጥቅልሉን ተረተረው፣ እርሱ መጽሐፉን ሲከፍት ህዝቡ ሁሉ ተነስቶ ቆመ፡፡ 6 ከዚያም ዕዝራ ታላቁን አምላክ ያህዌን አመሰገነ፣ ህዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን አንስተው፣ “አሜን! አሜን!” አሉ፡፡ ከዚያም ሁሉም በግምባራቸው ወደ ምድር እየሰገዱ ያህዌን አመለኩ፡፡ 7 ኢያሱ፣ ባኒ፣ ሰራብያ፣ ያሚን፣ ዓቁብ፣ ሳባታይ፣ ሆዲያ፣ መዕሤያ፣ ቆሊጣስ፣ ዓዛርያስ፣ ዮዛባት፣ ሐናን እና ፌልያ ሁሉም ሌዋውያን ነበሩ፡፡ እነርሱም የሙሴን ህግጋት ትርጉም በዚያ ቆመው ለነበሩ ህዝቦች አብራሩ፡፡ 8 እንደዚሁም እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ህግ ከመጽሐፉ ጥቅልሎች አነበቡ፣ ደግም ወደ አረማይክ ቋንቋ እየተረጎሙ ህዝቡ ሊረዱት እንዲችሉ ትርጉሙን ግልጽ አደረጉ፡፡ 9 ከዚያ አገረ ገዥው ነህምያ እና ጸሓፊውና ካህኑ ዕዝራ፣ እንዲሁም የተነበበውን ለህዝቡ ይተረጉሙ የነበሩ ሌዋውያን፣ እንዲህ አሏቸው፣ “ያህዌ አምላካችሁ ይህን ቀን ከሌሎች ቀናት ለይቶታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ቀን አትዘኑ ወይም አታልቅሱ!” ይህን የተናገሩት፣ ዕዝራ ህጉን ሲያነብ፤ የሚሰሙት ሁሉ ያለቅሱ ስለነበር ነው፡፡ 10 ከዚያም ነህምያ እንደዚህ አላቸው፣ “አሁን ወደየቤታችሁ ሄዳችሁ መልካም ምግብ ተመገቡ ደስ የሚያሰኝ ጣፋጭ መጠጥም ጠጡ፡፡ ከምትበሉትና ከምትጠጡት የሚበሉትና የሚጠጡት ለሌላቸው አካፍሉ፡፡ ይህ ቀን፣ ጌታችንን ለማምለክ የተለየ ቀን ነው፡፡ ሀዘን አይሙላባችሁ! ያህዌ የሚሰጣችሁ ደስታ ብርቱ ያደርጋችኋል፡፡” 11 ሌዋውያኑም ህዝቡን “ዝም በሉ አታልቅሱ፣ ይህ ቀን ለያህዌ የተለየ ቀን ነው፡፡ አትዘኑ!” በማለት ፀጥ አሰኙ፡፡ 12 ስለዚህም ህዝቡ ተነስቶ ሄደ፤ በሉም ጠጡም፣ እንዲሁም ምንም ለሌላቸው ከምግባቸው አካፈሉ፡፡ የተነበባላቸውን ቃላት ትርጉሙን ስለተረዱ በጣም ደስተኞች ነበሩ፡፡ 13 በማግስቱ፣ የየቤተሰቡ አባወራዎች እና ካህናቱ እንዲሁም ሌዋውያኑ የህጉን ቃላት ይበልጥ ለመረዳት በአንድነት ወደ ዕዝራ መጡ፡፡ 14 አያቶቻቸው በበረሃ ሲጓዙ በዳሶች ውስጥ እንደኖሩ ያስታውሱ ዘንድ፣ በእነዚያ ወራት ሁሉ የእስራኤል ህዝብ እንዴት በጊዜያዊ ዳሶች ውስጥ መኖር እንደሚገባቸው ያህዌ ለሙሴ የሰጠውን ተዕዛዝ በህጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፡፡ 15 እንደዚሁም ህዝቡ ወደ ኮረብቶች ሄዶ፤ ከወይራ ዛፎች ቅርንጫፎችን፣ ከበረሃ ወይራ ዛፎችና ከባርሰነት ዛፎች፣ ከዘንባባ ዛፎችና ሰፊ ጥላ ከሚሰጡ ዛፎች ዝንጣፊዎችን እየቆረጡ እንዲያመጡና በኢየሩሳሌምና በሌሎች ከተሞች ማወጅ እንዳለባቸው ተረድተዋል፡፡ ሙሴ እንደፃፈው፣ በበዓላቱ ወቅቶች ለመኖሪያነት የሚገለገሉባቸውን እነዚህን ዳሶች ከእነዚህ ዛፎች ቅርንጫፎች ማበጀት አለባቸው፡፡ 16 ስለዚህም ህዝቡ ከከተማ ወጥቶ ቅርንጫፎችን ቆርጦ ዳሶችን ለመስራት ተጠቀመባቸው፡፡ ዳሶችንም በየቤቶቻቸው ሰገነቶችች በየአደባባዮቻቸው፣ በቤተ መቅደስ አደባባዮች፣ እና በውሃ በር አጠገብ በሚገኘው አደባባይና በኤፍሬም መግቢያ ሰሩ፡፡ 17 ከባቢሎን የተመለሱ እስራኤላዊያን ሁሉ ዳሶችን ገንብተው ለአንድ ሳምንት ኖሩባቸው፡፡ እስራኤላዊያን ያንን በዓል ከኢያሱ ዘመን አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንዲህ አላከበሩም፡፡ ህዝቡ በጣም ተደስቶ ነበር፡፡ 18 ዕዝራ በዚያን ሳምንት በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ህግ ለህዝቡ ያነብ ነበር፡፡ ከዚያ በስምንተኛው ቀን፣ ድንጋጌውን ተከትለው ህዝቡ እንዲሰበሰብ አደረጉ፣ ይህም የበዓሉ ፍጻሜ ነበር፡፡